የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ቅዳሜ መጋቢት 3/ 2008 ዓ.ም.
ለእግዚአብሔር የተለዩ ነገሮች ሁሉ ቅዱስ ወይም ቅድስት የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል፡፡ የቅድስና መሠረታዊ ሕጉም ለእግዚአብሔር መለየት፣ ከእርሱ ጋር ፍጹም መወገን፣ የሌላ እስከማይሆኑ ድረስ ለእርሱ በቃል ኪዳን መለየት በማኅተመ ደም ለእግዚአብሔር መቆጠር ነው፡፡
ለእግዚአብሔር የተለየ ሰው፣ ለእግዚአብሔር የተለየ ዕቃ፣ ለእግዚአብሔር የተለየ ቀንና ለእግዚአብሔር የተለየ ገንዘብ የተቀደሰ ይባላል፡፡ ለእግዚአብሔር ከተቀደሰ በኋላም ለምድራዊ አገልግሎት ዳግመኛ አይውልም፡፡ በቅዱስ ያሬድ ስያሜ መሠረት የዐቢይ ጾም ሁለተኛው እሑድ ቅድስት በመባል ይጠራል፡፡ ጾመ ኢየሱስ ዐርባ ቀኑም ከቅድስት እሑድ ማግሥት ይጀምራል፡፡ ዐቢይ ጾም ከሌላው ጊዜ ይልቅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና አገልግሎቱ የሚታወስበት ወራት ነው፡፡ ይኸውም፡–
· ከሰማይ ወደ ምድር መውረዱ የሚታወስበት ነው፡፡ እኛ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጠፈር ስለወጡ ሳይንቲስቶች ብዙ እንናገራለን፡፡ የጠፈር ማዕከላትም እነዚህን ወገኖች በየዕለቱ ያስባሉ፡፡ ከሰማይ ወደ ምድር የወረደው ብቸኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በየዕለቱ ሊታሰብ ይገባዋል፡፡፡ እርሱ ራሱ በቃሉ፡– ‹‹ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው›› ብሏል (ዮሐ. 3÷13)፡፡
· የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስለ መስጠት የሚነገርበት ነው፡፡ ለእግዚአብሔር የምንሰጠው ዓሥራት መባ ብቻ አይደለም ጊዜያችንን፣ ሕይወታችንን፣ አገልግሎታችንን መስጠት እንደሚገባን ጌታችን ማስተማሩን እናስባለን፡፡
· ለብዙ ዘመናት እግዚአብሔርን ደጅ የጠኑ ሕሙማን እግዚአብሔር እንደሚያስባቸው የምናውጅበት ሰሞን ቢኖር ዐቢይ ጾም ነው፡፡
· ጌታችን ወደ ሰማይ ያረገ ብቻ ሳይሆን ዳግመኛም የሚመጣ ነው፡፡ መምጣቱም ለቤተ ክርስቲያን የተስፋዋ ሙላት ነው፡፡ አማንያን ለጌታ መምጣት ዘወትር ማዘጋጀት ቢገባም በተለየ ሁኔታ በደብረ ዘይት እሑድ በማሰብ የጌታን ትንቢት እንሰብካለን፡፡
· የእግዚአብሔር ፍርድ ለኃጢአት ዋጋ የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ለአገልግሎትም መልካም ዋጋ የሚሰጥም ነው፡፡ ይህ ወራት የአገልጋዮች ሽልማት ከላይ መሆኑን የምንተርክበት ወር ነው፡፡
· ሊቅነት ጌታን እንደማያገኝ በእምነት አሰሳ የሚገኝ አምላክ መሆኑን የምናብራራበት ሰሞን ነው፡፡
· ያመሰገነች ዓለም ብትራገምም ጌታ ግን ከተቀበርንበት ያስነሣል ብለን የምንሰብክበት ጊዜ ቢኖር ዐቢይ ጾም ነው፡፡
· ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን የዘወትር ርእስ ቢሆንም በዐቢይ ጾም ግን በተለየ ሁኔታ ይሰበካል፡፡ ወደ ምድር ከመውረዱ እስከ ትንሣኤው በልዩ ይታወሳል፡፡ ፍቅሩ፣ ፍለጋው፣ ትምህርቱ፣ ተአምራቱ፣ ሕይወቱ፣ ለሰው ልጆች የከፈለው ዋጋ ይታሰባል፡፡ በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚውሉትን እሑዶችና ስያሜአቸውን ስናይ ወንጌልን እንድናስታውስ ያደርገናል፡–
የመጀመሪያ እሑድ ዘወረደ ይባላል፡፡ ጌታ ከሰማይ መውረዱን ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም መወለዱን የምናስብበት ነው፡፡ ልደቱ ለመዳን የተከፈለው የመጀመሪያው ዋጋ ነው፡፡ እግዚአብሔር ተብሎ የሚመለከው የሰው ልጅ ተብሎ በበረት መወለዱ፣ መላእክት ከበውት ይኖር የነበረው በከብቶች ተከቦ በግርግም መገኘቱ፣ ሁሉን የሚመግብ ከእናቱ ድንግልናዊ ወተት መለመኑ፣ የዘላለም አባት ሕጻን ሆኖ መወለዱ ይህ ሰብኬዋለሁ ተብሎ የማይታለፍ የዘወትር ርእስ /ድንቅ/ ነው፡፡ አንድ ንጉሥ ከዙፋኑ በፈቃዱ ዝቅ ብሎ ከለማኝ ጋር ኖረ ቢባል በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ቀርፀን ትውልድን እናስተምርበት ነበር፡፡ ራቁቱን የተወለደ ንጉሥ ከለማኞች መካከል ቢገኝ አይደንቅም፡፡ መሠረቱ ጌትነት የሆነው ጌታ ክብሩን ጥሎ ከእኛ ከለማኞቹ መካከል መገኘቱ እጅግ ይደንቃል!!
የዘወረደ ሳምንት የመዘጋጃ ሳምንት ነው፡፡ ቀጥሎ ያለው የቅድስት ሳምንት ደግሞ የጽሞና ሳምንት ነው፡፡ ጌታ ከሰማይ ከወረደ በኋላ ለሠላሣ ዓመታት በእናቱ ብቻ ሰማያዊነቱ እየታወቀ በስውር ኖሯል፡፡ በሠላሣ ዓመቱ ከተገለጠ በኋላ ግን በቀጥታ የሄደው ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ለጽሞና ነው፡፡ የታላቅ ተግባር መነሻ ጽሞና ነው፡፡ ይልቁንም የቅድስት ሳምንት ስለ ቅድስና አስፈላጊነት የሚሰበክበት ሳምንት በመሆኑ ከአገልግሎት በፊት የቅድስና ዝግጅት ወሳኝ እንደሆነ እናያለን፡፡
“ከአገልግሎት በፊት አንተን ልወቅህ
መሥዋዕት ከማቅረብ ልታዘዝልህ” ተብሎ የተዘመረው ለዚህ ነው፡፡
ሦስተኛው እሑድ ምኩራብ ተብሎ ይጠራል፡፡ ምኩራብ ቃሉ የሚሰበክበት የመንፈሳዊ አዋጅ አደባባይ ነው፡፡ ከምስክርነት በፊት ጽሞና ካለ ምስክርነት ኃይል ያለው ይሆናል፡፡ ዐራተኛው እሑድ መጻጉዕ ነው፡፡ ሠላሳ ስምንት ዓመት ከአልጋ ጋር ተጣብቆ የኖረው በሽተኛ መዳኑን የምናስብበት ነው፡፡ ይህ የሚሳየን የበጎ ምስክርነት ፍሬው ወይም በጎ ምስክርነትን የሚከተለው ፈውስ መሆኑን ነው፡፡ ፈውስ ሁለት
ዓይነት ነው፡፡ የሥጋና የነፍስ ፈውስ ብለን እንጠራዋለን፡፡ ምስክርነት ከፈውስ ነጻ ስላልሆነ ወይ በሥጋ ወይ በነፍስ ፈውስ ማምጣቱ የማይቀር ነው፡፡
ዓይነት ነው፡፡ የሥጋና የነፍስ ፈውስ ብለን እንጠራዋለን፡፡ ምስክርነት ከፈውስ ነጻ ስላልሆነ ወይ በሥጋ ወይ በነፍስ ፈውስ ማምጣቱ የማይቀር ነው፡፡
ከመጻጉዕ ቀጥሎ የምናገኘው አምስተኛውን እሁድ ደብረ ዘይት ተብሎ የተሰየመውን ነው፡፡ በዚህ ዕለት ጌታችን ዳግመኛ እንደሚመጣ በዚያን ቀንም የእምነትና የመታዘዝን ዋጋ እንደሚሰጥ ዳግመኛም የዘመን መጨረሻ ምልክቶች ምን እንደሆኑ ይተረካል፡፡ በወንጌል አምኖ የዳነ ሰው የሚጠብቃቸው ብዙ የጸሎት መልሶች ቢኖሩ እንኳ በዋነኝነት የሚጠብቀው የክርስቶስን መምጣት ነው፡፡ ከመጻጉዕ ቀጥሎ ደብረ ዘይት መባሉ ትክክል ነው፡፡ የዳነ ሰው የክርስቶስን መምጣት ይናፍቃልና፡፡ ለቤተ ክርስቲያንም የቀረላት ተስፋዋ የክርስቶስ መምጣት ነው፡፡ የዘወትር ልመናዋም ማራናታ ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና የሚል ነው (ራእ. 22፡20)፡፡
ከደብረ ዘይት ቀጥሎ ያለው ስድስተኛው እሑድ ገብር ኄር ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ከጌታው ዘንድ የሚጠብቀውን ምስጋና የሚተነተንበት ቀን ነው፡፡ ጌታችን ሲመጣ ሲተጉ የሚያገኛቸውን አገልጋዮች በልዩ ይሸልማቸዋል፡፡ ስለዚህ ከደብረ ዘይት ቀጥሎ ገብር ኄር መባሉ ተርታውን የጠበቀ ነው፡፡
ከገብር ኄር ቀጥሎ ያለው ሰባተኛው እሑድ ኒቆዲሞስ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ የማታ ተማሪ ነው፡፡ ብዙ ቢያውቅም ላወቀው ነገር ዋጋ መክፈል የማይፈልግ የሊቅ ፈሪ ነበር፡፡ ጌታ ግን አልነቀፈውም፣ እንደ አዲስ አማኒ በፍቅር አገለገለው፡፡ የሚገለጥበትና የአደባባይ ዋጋ የሚከፍልበት ቀን እንዳለ ጌታ አሰበ (ዮሐ. 3፡1-5፤19፡39)፡፡ እምነቱን በትዕግሥት አሳደገለት፡፡ የዘመናት ፈተና የቤተ ክርስቲያን የሁልጊዜ ሕመም የማታ ተማሪዎች መብዛት ነው፡፡ ይልቁንም ሊቃውንቱ የማታ ተማሪ ናቸው፡፡ የአገራችን ነገሥታት ያለሙያቸው እየገቡ ንጉሥ ወካህን ነኝ እያሉ ሊቃውንቱን ሲያስቃዩ ስለኖሩ ሊቃውንቱ ሁሉ በስውር የሚያምኑ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ኒቆዲሞሶችን እንድናበረታታ ሰባተኛው እሑድ ተሰይሟል፡፡ እግዚአብሔር ለምእመናን ብቻ ሳይሆን ለሊቃውንቱም ይራራል፡፡ ሊቃውንቱም መገልገል እንዳለባቸው ያሳስበናል፡፡
ከኒቆዲሞስ ቀጥሎ የምናገኘው እሑድ ሆሳዕና ነው፡፡ ጌታ የከበረበትና ንጉሣዊ አክብሮት የተቀበለበት ቀን ነው (ማቴ. 21፡1-13)፡፡ ከሆሳዕና ቀጥሎ ግን ሰሙነ ሕማማት አለ፡፡ ይህ የዓለምን ጠባይ የምናውቅበት ነው፡፡ ይንገሥ ያለች ዓለም ይሰቀል ትላለችና፡፡ ይህንን እንድናስብ የዜማና የሥነ መለኮት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሥርዓቱን መሥራቱ ይደንቃል፡፡
እነዚህ እሑዶች የመንፈሳዊ አገልግሎት ተርታን የሚገልጡ ናቸው፡፡ ቀጥሎ ምን እንደሚሆን ለማወቅ እንጨነቃለን፡፡ ጽሞና ካለ አገልግሎት፣ አገልግሎት ካለ ፈውስ እንደሚኖር ስያሜዎቹ ያስረዱናል፡፡ እሑዶቹ ስለ አገልጋዮች ብዙ ትንታኔ የያዙ ናቸውና አገልጋዮች በልዩ መልክ ወራቱን ሊዘጋጁባቸው ይገባል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ብሉይን ከሐዲስ እያስማማ፣ ወንጌልን በኦሪት ላይ እያከበረ ያዜማል፡፡ ድጓው የሥነ መለኮት ትምህርት ቤት እንጂ ተራ ጩኸት አይደለም፡፡ ይህን የሚያስተውሉ ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡
ቅድስት
ቅድስት የሚላት እሑድ ሰንበትን ሲሆን ሰንበት የአምልኮ የማስተዋል የመቀደስ ቀን ተብላ ለእግዚአብሔር የተለየች ቀን ስለሆነች የጾሙን መጀመሪያ ስለ ቅድስና እንድናስብ ብሎ ቅዱስ ያሬድ የሳምንቱን ስያሜ ቅድስት ብሎ አውጥቷል፡፡ ቅድስት የሚለውም ስም፡–
በጾመ ድጓ፡–
‹‹ዛቲ ዕለት ቅድስት ይእቲ
ለውሉደ ሰብ መድኃኒት
ትኩነነ መርሖ በፍኖተ በኩሉ ጊዜ
ወበኩሉ ሰዓት ቀደሳ እግዚአብሔር ለሰንበት››
ትርጉሙም፡–
‹‹ይህች ዕለት የተለየች የተቀደሰች ናት፡፡
ለሰው ልጅም መድኃኒት ናት፡፡
በመንገዱ ሁሉ በጊዜው ሁሉ በሰዓቱ ሁሉ
መሪ ትሆነን ዘንድ እግዚአብሔር ሰንበትን አከበራት፡፡››
ብሎ ከተናገርው ቃል የወጣ ነው፡፡
ሰንበት መልካም ሥራ፣ የተቀደሰ ሥራ የሚሠራበት ቀን ስለሆነ መድኃኒት ወይም መልካም ሲል ጠርቷታል፡፡
የድጓው መዝሙር፡–
‹‹ግነዩ ለእግዚአብሔር
ወጸውዑ ስሙ
ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ
ሀቡ ስብሐት ለስሙ››
ትርጉሙም፡–
‹‹ለእግዚአብሔር ተገዙ
ሥራውንም ሁሉ ለአሕዛብ ንገሩ
ለስሙም ምስጋናን ስጡ፡፡››
እያለ ቅዱሱን ጌታ እያከበረ፣ ሥራውን እያደነቀ፣ በመልካምነቱ እየተደመመ አምልኮ የሚያቀርብበትም ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ባህረ ሐሳብ መሠረት የጌታ ጾም ለእግዚአብሔር ብቻ ምስጋና የሚቀርብበት በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተገኘው ድኅነት የሚወሳበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እኛን ለማዳን ስለ እኛ ኃጢአት የከፈለው መሥዋዕትነት የሚታወስበት ወር ነው፡፡
ቅዱስ ያሬድ የቅዱስ ጳውሎስን ቃል;- ‹‹በላይ ያለውን አስቡ በላይ ያለውን እሹ በምድር ያለውን አይደለም …›› እያለ በቅድስት ሣምንት የሚባለውን ዝማሬ እያብራራ ይቀጥላል (ቆላ. 3፡1)፡፡
የ40 ቀኑ ጾም የወንጌሉን ታሪክ ይዞ ነው የተሠራው፡፡ ስለዚህ ዐርባው ቀን ወንጌሉ የሚታሰብበት ወር ነው፡፡
ጸጋና ሰላሙ ከእኛ ጋር ይሁን!