የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ

“ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ”
                                          /ዮሐ. 1፡6/፡፡
ወንጌላዊው ዮሐንስ እየተናገረ ያለው ስለ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ነው፡፡ ዮሐንስ መጥምቅን ለሦስት ጊዜ ያህል ያነሣዋል፡፡ የሚያነሣበት ምክንያትም ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ መጨረሻ ብርሃን ተቀብሎት ነበርና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፀሐይ ብርሃን፣ ዮሐንስ ግን የጨረቃ ብርሃን መሆኑን ለመግለጥ ነው /ዮሐ. 1፡6-8/፡፡ ሁለተኛ ዮሐንስ በአባቱ በዘካርያስ ፋንታ ሊቀ ካህናት የሚሆን ነበር፡፡ እርሱ ግን አዲሱን ኪዳን ለመስበክ በረሃ ገብቷል፡፡ በወራሽ ሊቀ ካህንነቱና ዓለምን በመናቁ ተከብሮ የሚኖር ነው፡፡ ወንጌላዊው የሚጽፈው ዮሐንስን ካከበራችሁ እርሱ ያከበረውን ክርስቶስ አክብሩ ለማለት ነው /ዮሐ. 1፡19-37/፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ጸሐፊው ለመጥቀስ የፈለገው ዮሐንስን የሚደግፉ ክርስቶስን አሳንሰው ለማቅረብ ሲፈልጉ ዮሐንስ ግን እኔ ሚዜ ነኝ እርሱ ግን ሙሽራው ነው በማለት ሙሽሪት ምእመንና ክርስቶስን አገናኝ ነው ለማለት ነው /ዮሐ. 3፡22-30/፡፡ ሙሽሪትና ሙሽራ ሲገናኙ ደስ የማይለው ሚዜ የለም፡፡ የዮሐንስ መጥምቅ ደስታው እናንተና ክርስቶስ ስትገናኙ ነው ለማለት ይጠቅሰዋል፡፡ በርግጥም ይህ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ራሱ፡- “ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምጽ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ” ብሏል /ዮሐ. 3፡29-30/፡፡
መጥምቁ ዮሐንስ የተለያዩ ስያሜዎች አሉት፡፡ ነቢይና ሐዋርያ ይባላል፡፡ የነቢያት መጨረሻ፣ የሐዋርያት መጀመሪያ ነውና፡፡ ደግሞም ክርስቶስ እንደሚመጣ የተናገረ ነቢይ፣ ክርስቶስ ከመጣ በኋላም “እነሆ የእግዚአብሔር በግ” ብሎ ያስተዋወቀው ሐዋርያ ነውና /ዮሐ. 1፡29/፡፡ ካህንም ይባላል፡፡ ሕዝቡን እያናዘዘ ያጠምቅ ነበርና /ማቴ. 3፡6/፡፡ ሰማዕትም ይባላል፡፡ ስለ እውነት መስክሮ አንገቱን ተሰይፏልና /ማቴ. 14፡1-12/፡፡ ባሕታዊም ይባላል፡፡ በበረሃ የሚኖር ነበርና /ማቴ. 3፡1-2/፡፡ የምድረ በዳ ድምፅም ተብሏል /ማቴ. 3፡3/፡፡ የሚኖርበትን ስፍራ ለማመልከት ብቻ ሳይሆን ከነቢዩ ሚልክያስ ጀምሮ ነቢይ ሳይነሣ ለ400 ዓመታት ቆይቷል፡፡ ይህ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ ያለው 400 ዓመታት የጸጥታ ዘመን ይባላል፡፡ ዮሐንስ ይህን የጸጥታ ዘመን የሻረ ድምፅ ነው፡፡ ስለዚህ በነቢዩ የምድረ በዳ ድምፅ መሆኑን አስቀድሞ ትንቢት ተነግሯል /ኢሳ. 40፡3/፡፡ ዮሐንስ መንገድ ጠራጊም ተብሏል /ሚል. 3፡1/፡፡ በጥንት ዘመን ነገሥታት በሚያልፉበት መንገድ ከመንፈቅ ጀምሮ መንገድ ይጠረጋል፡፡ የሰማዩ ንጉሥ ክርስቶስ ግን የሚያልፈው በአውራ ጎዳናው ሳይሆን በሰው ልብ ነውና ዮሐንስ ይህን ልብ በትምህርት፣ በተግሣጽ፣ በንስሐ፣ በእምነት ይጠርግ ነበር፡፡ አራት ዓይነት መንገዶች እንዳሉ አራት ዓይነት ልቦችም ገጥመውታል፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ፡- “በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል መጽሐፍ። የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፥ ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን፥ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይሁን” በማለት ዘግቦለታል /ሉቃ. 3፡3-6/፡፡
አዘቅት የተባለው አልችልም ባይ አስተሳሰብ ነው፡፡ ተራራ የተባለው ትዕቢት ነው፡፡ ጠማማ የተባለው ተንኮለኛ ማንነት ነው፡፡ ሸካራ የተባለው ቂመኛነት ነው፡፡ እነዚህ አራት ችግሮች ንጉሡ በልባችን እንዳያልፍ መሰናክል ናቸው፡፡ ስለዚህ አልችልም ባይነት በእምነት፣ ትዕቢት በትሕትና፣ ጠማማነት በቅንነት፣ ቂመኛነት በይቅርታ ሊስተካከሉ ይገባል፡፡ አልችልም ባይነት በእምነት፣ ትዕቢት በንስሐ፣ ጠማማነት በትምህርት፣ ቂመኛነት በተግሣጽ እንዲወገዱ ይጮህ ነበር፡፡
እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ