የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ(36)

አትጣሉ
“በመንገድ እርስ በርሳችሁ አትጣሉ” (ዘፍ.45፡24)።

የዕድሜ ብዛት ብቻውን ጥበብ አያመጣም። የዘመን ርዝማኔም አዋቂ ያደርገኛል ብለን መቀመጥ የለብንም። የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ በዕድሜ ትንሽ ቢሆንም ከወንድሞቹ ይልቅ ጠቢብና አስተዋይ ነበር። ከላይ ያለውን ምክር የመከረ እርሱ ነው። እርሱም ባለማስተዋል በልጅነት አእምሮ ሕልሙን ለወንድሞቹ ነገረ። ለሚያግዙት ሳይሆን ለሚያደናቅፉት፣ ለሚወዱት ሳይሆን ለሚጠሉት ራእዩን በመንገሩ መከራ መጣበት። ራእይ ያለቦታውና ያለጊዜው ከተዘራ የመከራ መገኛ ይሆናል። ወንድሞቹም ወደ ግብፅ ሸጡት። ከራእዩ እናስቀራለን ብለው ወደ ራእዩ ፍጻሜ ገፉት። ዮሴፍ ከአባቱ ቤት ይልቅ በግብፅ ተወዳጅ ሆነ። መንደር ነፍገውት አገር አወረሱት። ወንድም ሲጠላ ባዕድ ዘመድ ይሆናል። ወንድሞቹ ቢወዱት ኖሮ የከነዓን በግ ጠባቂ ሆኖ ይቀር ነበር፣ ቢገፉት የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ። በመንደር ተረስተን የምንቀረውን ዓለም አቀፍ ሰው የሚያደርጉን ገፊዎች ናቸው።

ታዲያ በከነዓን ረሀብ ተነሥቶ የዮሴፍ ወንድሞች እህል ለመግዛት ወደ ግብፅ ወረዱ። ረሀቡ በግብፅም.መጥቶአል። የዮሴፍ ብልሃት ግን ረድቷል። ከደህናው ቀን ለክፉ ቀን ሰብስቦ ሕዝቡን አተረፈ። መላው ዓለም እንዲተርፍ እግዚአብሔር ምክንያት ያደረገው ዮሴፍን ነው። የዮሴፍ ወንድሞች እህል ለመግዛት ወደ ግብፅ ወረዱ። የገደሉት ወንድማቸው ሕይወት አድን ሆኖ ተቀምጧል። እነርሱ አላወቁትም፣ ዮሴፍ ግን አወቃቸው። ገዳይ ይረሳል፣ ሟች ግን አይረሳም። ዮሴፍ ግን እንኳን ገፋችሁኝ ለበጎ ነው በሚል አሳብ ተቀበላቸው። እግዚአብሔር ካልጣለ በሰው ማዘን ከንቱ ነው። እህልና ስጦታ ሰጥቶ ሲሸኛቸው፦ “በመንገድ እርስ በርሳችሁ አትጣሉ” አላቸው። ከእህሉና ከስጦታው በላይ ምክርን ሰጣቸው። የድህነት ሥር ግጭት ነውና።

ትንሽ ቢሆንም የዓለሙ አማካሪ ሆኖ ነበር። እነዚህ ወንድሞቹ በረሀብ ዘመንም ከመጣላት እንደማያርፉ ያውቃል። ልብ ካልተሰበረ ሰው የጠብ ሱስ አይለቀውም። እኔነት ሲሞት ብቻ ጠብ ይገሰጻል። አለመጣላት የሚቻል አይመስላቸውም ነበር።

በአንድ ገዳም ተጣልተው የማያውቁ ሁለት መነኮሳት ነበሩ። ጠብ ምንድነው? ብለው ሲመራመሩ አንደኛው ይህን ዕቃ የእኔ ነው ስሎት እርሶም የእኔ ነው በሉ በዚያ ጠብ ይመጣል አሏቸው። አንደኛው የእኔ ነው ሲሉ ሁለተኛው አዎ የእርስዎ ነው ሲሏቸው መጣላት አቃታቸው። የጠብ መነሻው የእኔ ነው የሚል ስሜት ነው። ይህ ብቻ አይደለም ጠብ የሰላምን ዋጋ ከማያውቅ ያልበሰለ ማንነት ይወጣል። የታወከ አእምሮም ያውካል። የውጫዊ ጦርነት ሥሩ ውስጣዊ ጦርነት ነውና።

ጠብ ካልሰለጠነ አእምሮን ይወጣል። ሁሉንም እንደ ሎሌው የሚያስብ፣ ራሱን ያነገሠ፣ መብቴ እስከ የት ነው? የማይል ሰው ጠብ ማፍያ ይሆናል። ይልቁንም በአገራችን ሌላውን መድፈር ስለምንወድ ጠብ ሥራችን ነው። ተረታችንም፦ “ሥራ ከምፈታ ልጄን ላፋታ” የሚል ነው። መብትና ግዴታን መለየት ከጠብ ይታደጋል።

ጠብ የቀኑን ደስታ ያበላሻል። የትዳርን ጣዕም ይነሣል። የልጆችን ሥነ ልቡና ይጎዳል። አካባቢን ይረብሻል። ጠላት አለኝ የሚል ንግግር የሚያስደስታቸው ጠብን በስእለት ይፈልጓታል። ግን ለምን? ማስደሰት ስንችል ማሳዘን፣መቀበል ስንችል መግፋት ምን ይሠራል? በማይከለስ ዕድሜ፣ በቀረን ትንሽ ዘመን መልካም ብንሠራ መታደል ነው። ያለን ዕድሜ እንኳን ለጠብ ለፍቅርም አይበቃም። በሕይወት መንገድ ላይ በፍቅር መኖርን ያድለን!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ