የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ (30)


ከንቱ ክብርን አትቀባበሉ

“እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፣ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?” (ዮሐ. 5፡44)።

አይሁድ እግዚአብሔር ያስፈልገናል ከማለት ለእግዚአብሔር እኛ እናስፈልገዋለን ወደሚል አስተሳሰብ ገብተዋል። በርግጥ ለእግዚአብሔር እናስፈልገዋለን። ነገር ግን በመጀመሪያ እግዚአብሔር ለእኛ ያስፈልገናል። ለክብሩ ለመቆም በእርሱ መሠራትና መለወጥ አለብን።

አይሁድ ለእግዚአብሔር እናስፈልገዋለን የሚለው አስተሳሰባቸው ትዕቢተኛ እንዲሆኑ ክርስቶስን እንዲገፉ አደረጋቸው። ክርስቶስን የክብሩን ጌታ አቃለው እርስ በርሳቸው ለመከባበር ይሞክራሉ። የእርስ በርስ ክብራቸውም ማንንም እንዳያዩ በተቃራኒው እንዲገፉ አደረጋቸው። እግዚአብሔር አይሁድ ተጠቃለው ከገቡ በኋላ የመንግሥቱን በር የሚዘጋ መሰላቸው። መላውን ዓለም ከማገልገል መናቅና መስደብ ያዙ። የእግዚአብሔር ዓላማው እነርሱን አድኖ በእነርሱ ዓለሙን ማዳን ነው። አይሁድ ግን እግዚአብሔርን በሰፈራቸው መጠን አጠበቡት። እንደ እርሱ ከማሰብ እንደ እኛ ወርደህ አስብ አሉት። ሌሎች አሕዛብ ወደ ይሁዲ እምነት ቢመጡም ከእነርሱ ጋር አብሮ ለማምለክ ፈቃደኛ አልነበሩም። በመቅደሱ ግንብ ከልለው የአሕዛብ አደባባይ ብለው በመሰየም ያርቋቸው ነበር። እግዚአብሔር ግን የሁሉ ነው፣ ለዓለምም እቅድ አለው።

አይሁዳዊነት ዘር ሳይሆን አስተሳሰብም ነው። ዛሬም፦ “ከእኛ በላይ ፉጨት አፍ ማሞጥሞጥ” እንዲሉ ያለ እኛ ማንም የለም በሚል አስተሳሰብ ልንያዝ እንችላለን። ማኅበራዊ ከበሬታን ብቻ የሚፈልግ መንግሥተ ሰማያትን ግን የማይፈልግ ሃይማኖታዊነት ሊሰማን ይችላል። ይህ ብቻ አይደለም የጠፉትን ከመመለስ እንዲጠፉ በደንብ እየገፋን ይሆናል። እርስ በርሳችንም ምድራዊ ክብር እየተሰፋፈርን፣ ዛሬ አሞግስሃለሁ አንተ ደግሞ ነገ ስሜን አንሣልኝ እያልን ይሆናል። በከንቱ ክብር ስለተሞላን መሳደብ እንጂ ማስተማር እያቃተን ነው። የሚያስተምረውን ያልተማረው የሚተቸው፣ የሚጽፈውን የማይጽፈው የሚሰድበው በዚህ ምክንያት ነው። የምንሠራውንና የምንናገረውን ደግመን ብናስበው መንግሥተ ሰማያት ለመግባት አሳብ ያለን አይመስልም። ከምድራዊ ሕግ ከሰማያዊ ተስፋ ውጭ እየሆንን ይመስላል። ሰውን መድፈር የማይበቃን ተሳድበን የማንረካ፣ በእኛ ማንነት ትልቋን ቤተ ክርስቲያን የምናስተች ሆነናል። “ሞኝ ባያፍር ዘመዱ ያፍራል” እንዲሉ ሊቃውንቱ ተሸማቀውብን ቁጭ ብለዋል።  ጥራዝ ነጠቆችን የልብ ልብ እየሰጠን ጳጳስ የሚያዋርዱ፣ አገልጋይን የሚያቃልሉ ምእመናንን እያመረትን ነው። ያቺ የክብር ቤት እንዲህ አባወራ እንዳጣ ቤት መጫወቻ ስትሆን ያሳዝናል።

ብዙ የነገረ መለኮት ምሥጢር እያለን የምንታወቀው በስድብ ነው። ለአፍሪካውያን ወንጌልን የማድረስ አደራ የእኛ ሆኖ ሳለ ከዋና ከተማችን እንኳ አልወጣንም። ከዛሬ አንድ ሺህ ዓመት በፊት የተነሡት ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት የወንጌል ዱካቸው እስከ ታንዛንያ ደርሷል። ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ ያለን ግን ሥራውን እልፍ አላደረግንም። በአሕዛብ ተከበን ሳለ እርስ በርሳችን ገበናችንን አልተሸፋፈንም። መንፈሳዊነት ቢርቀን እንኳ ስልቱ ለምን ጠፋን? ካቶሊክ የሉተራውያን እንቅስቃሴ በአንድ ወር መላው ጀርመንን ሲያሳጣት ወዲያው ኢየሱሳውያን የሚል ማኅበር አቋቁማ ስለ ክርስቶስ መናገር ጀመረች። ሉተራውያኑ ሳይመጡ ሉተራውያን የሚሉትን ለሕዝብ ጆሮ አደረሰች። ሉተራውያኑ ሲመጡ ይንንማ ሰምተናል እያለ ሕዝቡ ገፋቸው። ይህ ስልት ነው።  ይህ የዛሬ 400 ዓመት የተከናወነ ነው። እኛ በ21ኛ ክፍለ ዘመን ተደባዳቢ እናሰለጥናለን። ወይ ከስልቱ ወይ መንፈሳዊነቱ አልሆንም። አንድ በግ ፍለጋ የመጣውን ጌታ ባለማስተዋላችን፦ “ከሣር ክዳን ቤት አንድ ቢመዘዝ አያፈስም” እያልን የጭካኔ ተረት እንተርታለን። ከአሥር ሚሊየን በላይ ሕዝብ ማጣት አንድ ሣር ነው ወይ? የዚህ ሁሉ መፍትሔው በወንድነት ሳይሆን በማስተማር ሃይማኖታችንን ማስከበር ነው።

የእርስ በርስ ክብራችን የእግዚአብሔርን ክብር እንዳናይ ሌሎችን ለማትረፍ እንዳንራራ አድርጎን ይሆን? በቅዱስ መንፈሱ ይምራን!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ