የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ (29)

ተነጋገሩ

“የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም አደመጠ፥ሰማም፥ እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ” (ሚልክ. 3፡16)።

እርስ በርስ መነጋገር ልብ ለልብ ለመቀራረብ ይረዳል። ከሰው ጋር ያለን ግንኙነት ከአንደበታችን የሚጀምር ነው። ካልተነጋገርን መተዋወቅ አንችልም። በመነጋገር ውስጥ ግምቶቻችን፣ ቅሬታዎቻችን ይወገዳሉ። እስካልተነጋገርን ራሳችንን እያመነው እንጠፋለን። መነጋገር ብቻውንም ወደ መግባባት አያደርስም። አንዳንድ ንግግሮች የበለጠ ከድጡ ወደ ማጡ የሚሰዱ ናቸው። ይቅር ለመባባል ተገናኝተን የምንወራወረው ቃላት የበለጠ ቅሬታውን ሊያሰፋው ይችላል። አብረን የምንቀጥል ከሆነ እስከ መጨረሻው መነጋገር ተገቢ አይደለም፣ አብረን የማንቀጥል ከሆነም እስከ መጨረሻው መነጋገር ተገቢ አይደለም። እርስ በርስ ተነጋግረን ለመግባባት ፈሪሃ እግዚአብሔር አስፈላጊ ነው።

የእግዚአብሔር ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ሥራ ሲነጋገሩ እግዚአብሔር ይገኛል። ያቺ ቀንም በእግዚአብሔር ፊት ትመዘገባለች። እግዚአብሔር በሚሠራበት ቀንም እነዚያ ሰዎች የክብሩ መገልገያዎች ይሆናሉ። ዛሬ ተገናኝተን ስለ ወንጌል ሥራ የምንመክረው ዋጋ አለው። ዋጋው የእግዚአብሔር ህልውና በመካከላችን ይሆናል፣ እግዚአብሔር በሚሠራበት ቀንም ገንዘቡ ያደርገናል። ስለ እግዚአብሔር ሥራ መነጋገር እጩ ሠራዊት መሆን ነው። ከውሳኔአችን ጋር ጌታ ይወስናል።

ብዙ ስብስቦች ጣዕም የሚያጡት ፈሪሃ እግዚአብሔር ስለሌላቸው ነው። የሚበጅ ንግግር ሲደረግ ሁሉም ይተኛል። ስድብና ውርደት ሲኖር ይነቃል። እኛና መንፈስ ቅዱስ ወስነናል የሚል ስብሰባ እየጠፋ ነው። የሌሎች አጀንዳ አስፈጻሚ በሆኑ፣ እገሌን ምቱልኝ ስደቡልኝ በሚል ጉቦ በተቀበሉ መካከል መታሰቢያ ያለው ጉባዔ አይደረግም። ምነው ባለቀ የሚባል ይሆናል። እግዚአብሔር በመፍራት ብንመካከር ብዙ ተራራዎች ዝቅ ባሉ ነበር።

እስልምና የመቶና የአምስት መቶ ዓመት እቅድ ይዞ ይንቀሳቀሳል። ክርስቲያኖችስ የአምስትና የሃያ ዓመት እቅድ አላቸው? አለን እያልን እንዳንጠፋ መነጋገር ያስፈልገናል። ሕዝባችንን በመስቀልና በጥምቀት ቀን እየለካን ውስጥ ውስጡን ተበልቶ እንዳያልቅ ማሰብ ያስፈልጋል። የፍቅርን ወንጌል እንዴት ማድረስ እንዳለብን መምከር ግድ ነው። በአንድ ስብሰባ ላይ “በአፍሪካ አንደኛ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ማነጽ አለብን” ሲባል አንድ አባት፦ “በአፍሪካ አንደኛ ሰው ስለመገንባትም መነጋገር አለብን” ብለዋል። ዛሬ በአውሮፓና በአሜሪካ ትልልቅ አብያተ ክርስቲያናት ወደ መስጊድነትና ወደ ጭፈራ ቤት የተለወጡት ሕዝብን ችላ ብለው ሕንጻን ብቻ ሲያንጹ ስለኖሩ ነው። ዛሬ ካላሰብን እኛም ዕጣችን ይኸው ነው። እግዚአብሔር ይርዳን!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ