በሰላም ሁኑ
“ወንድሞች ሆይ በመካከላችሁ የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁን ታውቁ ዘንድ ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ ታከብሩአቸው ዘንድ እንለምናችኋለን። እርስ በርሳችሁ በሰላም ሁኑ” (1ተሰ. 5፡12-13)።
አገልጋዮች ስጦታዎቻችን ናቸው። እኛ መሸከም የከበደንን ጭንቀታችንንና ኃጢአታችንን አሸክመናቸው የምንሄድ፣ ከመቃብር ይልቅ ከድነው የሚይዙን ናቸው። ማን የማንን ጭንቀት ይሰማል? በዚህ ዘመን ማን የማንን ኃጢአት ይደብቃል? አገልጋዮች በጸሎት የሚያስቡን፣ በቃሉ የሚያጽናኑን ናቸው። ከትዳራችን፣ ከቤተሰባችን ደብቀን የምናማክራቸው የውሳኔአችን አጋሮች ናቸው። በእግዚአብሔር ፊት የከበሩ ናቸው። ዘላለማዊ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። እነዚህ አገልጋዮች እግዚአብሔር በላያችን የሾማቸው ሹመኞች ናቸው። በዓለም ላይ ካሉ ከባድ ሥራዎች አንዱ አገልጋይነት ሲሆን ያለ ጸጋው እልፍ የማይል ነው። የሚገሥጸን ማግኘት ከባድ ነው። መገሠጽ ትልቅ ፍቅርና ሥልጣን ነው። የሚገሥጹን አገልጋዮች ናቸው። እነዚህን ስጦታዎቻችንን እንድናውቅ ሐዋርያው ያስገነዝበናል።
በፍቅር ከመጠን ይልቅ ልናከብራቸው ይገባል። የፍቅር አክብሮት ስስት ያለበት አክብሮት ነው። እነዚህ አገልጋዮች ከሥጋ ወላጆቻችን የሚበልጡ፣ ስለ ዘላለማዊ ሕይወታችን የሚተጉ ናቸው።
[ ማክሰኞ ፣ ኦክተውበር 13 ቀን 2015 8:38 ጡዋት ] ቲደስታ: በዓለም ላይ ይላሉ አጥኚዎች፦ “በዓለም ላይ እጅግ ብቸኞች አገልጋዮች ናቸው” ይላሉ። ሌሎችን ያጽናናሉ፣ እነርሱን የሚያጽናና የለም። የሌሎችን ጉድለት ይሸፍናሉ፣ የእነርሱ ጉድለት ነጋሪት ይጎሰምበታል። ስለ ሌሎች መቸገር ያዝናሉ፣ የእነርሱ መጎዳት ግን አዛኝ የለውም። በሌሎች መልካም ዕድል ይደሰታሉ፣ እነርሱ ጫማ ሲቀይሩ ግን ሁሉም ይናደድባቸዋል። ስለዚህ አገልጋዮች ብቸኞች ናቸው። ዛሬ በየውጭ አገሩ የእኛ ሰው አገልጋዮቹን እንደ ቤት ሠራተኛ ልዘዝ ሲል ያሳፍራል። ቅጣቱም እየመጣ የገዛ ልጆቻቸው ባላጋራ ሆነውባቸዋል። ትዳሩም ተናግቷል፣ ደስታም ጠፍቷል። የእግዚአብሔርን ቤት የሚያፈርስ ቤቱ ይፈርሳልና።
እውነተኞቹን አገልጋዮች የሚገፋው ሕዝብ የሚነግዱበትን፣ በሽታውንና ንስሐውን ሳይቀር እያሰራጩ የግፍ እንጀራ የሚበሉበትን ሐሰተኞች ደግሞ አቅፎ ይኖራል። ቋሚዎቹን አገልጋዮች እያስራበ ለመንገደኞቹ ሲቀልብ ይኖራል። እውነተኞቹን ካላወቅን ለክፉዎች ተላልፈን እንሰጣለን።
እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ይበተናሉ እንደሚለው አገልጋዩ ሲመታ መንጋው እየተመታና እየተበተነ ይመጣል። ለዚህ ነው፦ “እርስ በርሳችሁ በሰላም ሁኑ” የሚለው። የእርስ በርስ ሰላም የሚኖረው የሚደክሙልንን፣ ጌታ በላያችን የሾማቸውንና ስለ እኛ የሚቆጩልንን በማወቅ ደግሞም በማክበር ነው። የምእመናን ሰላም ያለው እዚህ ላይ ነው። የእግዚአብሔር ቤት የጎራና የቡድን ቤት እንዳይሆን ተዋረድ መከበር አለበት። ሥልጣን በሌለበት ውሳኔና ክብር የለም። ውሳኔና ክብር በሌለበትም ሰላም የለም።
እርስ በርሳችን ሰላም የምንሆንበት መንገድ ቀላል ነው። እግዚአብሔርም ሰላማችን ነው። የሚደክሙልንን በጌታም የሚገዙንን፣ ማወቅና ማክበር አማራጭ የሌለው የሰላም መንገድ መሆኑን ሐዋርያው ይናገራል። ጸጋው ያግዘን!