ዓርብ ሐምሌ ፳፬/ ፳፻፯ ዓ/ም
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምናገኛቸው ጠጋኝ ጥቅሶች አንዱ እንዲህ ይላል፡- “በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ÷ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥምህም& በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም& ነበልባሉም አይፈጅህም” (ኢሳ. 43÷2)፡፡
ብዙዎች በብዙ ነገሮች ብቸኝነት ይሰማቸዋል፡፡ እየከፈሉ የሚማሩ ትምህርቱን የምማረው ያለማንም ረዳት ነው፣ ለእኔ ያለሁት እኔ ብቻ ነኝ በማለት ዕንባ ቀረሽ ንግግር ይናገራሉ፡፡ ለልፋታቸው የደስታ ምላሽ በማይሰጠው ትዳራቸው ያዘኑ የምለፋው ለማን ነው? ብለው ሁሉን በትነው ለመሄድ ይዘጋጃሉ፡፡ ለሥራ እየጠፉ ለደመወዝ ቀን በማይጠፉ ሠራተኞች ያዘኑ ሰው እንዴት ለምኖ ያገኘውን ነገር እንደ ቀላል ይበትነዋል? በማለት ይተክዛሉ፡፡ በአገልግሎት ወንበር ተቀምጠው ሲያፌዙ በሚውሉ ያዘኑ ብቻዬን የመኸሩን ሥራ እንዴት እገፋዋለሁ? ይላሉ፡፡ የስብሰባ ጀግና የተግባር ሽባዎች በሆኑ ሰዎች ያዘኑ የሚያወራ ሳይሆን የሚሠራ ማን ነው? ይላሉ፡፡ ስለአገር ጥቅም የሚለፉ እነርሱ የገነቡትን ሌሎች ሲያፈርሱት ይህች አገር የእነርሱስ አይደለችም ወይ? በማለት ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ሕመሙ ቢለያይም ሕመም ግን ባለበት ዘመንና ዓለም መጽናናትን የሚሰጠን ድምፅ “ከአንተ ጋር እሆናለሁ” የሚለው ነው፡፡
የብቸኝነት ስሜት፣ ብቻዬን ነኝ የሚለውን ነገር አምኖ መቀበል ምን ያህል ስቃይ እንዳለው ያለፉበት ያውቁታል፡፡ ብቸኝነት ከከተማ በመውጣት፣ በዱር ውስጥ በመቀመጥ የሚወጣ ስሜት አይደለም፡፡ ብቸኝነት ጸጥታ የሚወልደው ሳይሆን በትዳር ውስጥ በደማቅ ከተማም የሚሰማ የስቃይ ድምጽ ነው፡፡
ከእኛ ጋር የሚወስኑ፣ ከእኛ ጋር ሥራ የሚጀምሩ፣ ከእኛ ጋር የሚጓዙ ብዙዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከእኛ ጋር የሚሆኑ ግን ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ከአሳባችን ጋር ማሰብ የማይችሉ፣ ከቃላችን ጋር መናገር የሚሳናቸው፣ ከተግባራችን ጋር መሥራት የማይችሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከእኛ ጋር ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ለሥራችን ሞራል ለመስጠት “አይዟችሁ በአሳብ ከእናንተ ጋር ነን” የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ቃል የቋንቋ ማሳመሪያ እንጂ ብዙ እውነትነት የለውም፡፡ በሩቅ የሚያስቡን ሳይሆን በሩቅ የሚጸልዩልን ለእኛ ዋጋ አላቸው፡፡ እግዚአብሔር ግን ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡ የምናመልከው አምላካችን ሁሉ በሁሉ ነው፡፡ ከለማኝ ጋር የሚለምን፣ ከሰጪ ጋር የሚሰጥ፣ ከተከሳሽ ጋር የሚከሰስ፣ ከዳኛ ጋር ሆኖ የሚፈርድ፣ ከመንገደኛ ጋር የሚጓዝ፣ ቀድሞ ደርሶ የሚቀበል፣ ከአልቃሾች ጋር የሚያዝን በአጽናኞች አንደበት የሚያረጋጋ፣ ከነቢያት ጋር የሚተነብይ፣ ፍጻሜውን ከሐዋርያት ጋር የሚሰብክ፣ በሰባኪ አፍ የሚናገር፣ በአማንያን ልብ የሚያትም. . . ሁሉ በሁሉ የሆነ አምላክ ነው፡፡ ይህ አምላክ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ ይላል፡፡
የመናገር፣ የማቀድ፣ የማደፋፈር ችሎታ ያላቸው የመሆን ግን ችሎታ የሌላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ሁሉ በሁሉ የሆነው አምላክ ግን መልካምን በልባችን የሚመኝ፣ ያንንም ሊፈጽም የሚተጋ አምላክ ነው፡፡ ስለዚህ መልካም ሥራችን ብቻ ሳይሆን መልካም አሳባችንም የእኛ አይደለም ማለት ነው/ፊልጵ. 2፡13/፡፡ እርሱ በውስጣችን ያቅዳል፣ መከናወንንም ይሰጣል፡፡
በምናልፍበት ብርቱ ጎዳና ብዙ እሴቶቻችን ተንጠባጥበዋል፡፡ ገንዘብ፣ ጉልበት፣ ጤና፣ ወዳጅ፣ … ተለይተውናል፡፡ ጥቁር ቀን ያልለየን ሰው፣ ያልለየን ወዳጅ የለም፡፡ ሰዎች የሚወዱን እንደ አየር ንብረቱ ነው፡፡ ፍቅራቸው በእውነታ ላይ ሳይሆን በሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በዚህ መውጣትና መውረድ፣ መከበርና መዋረድ በበዛበት ዓለም ላይ ከእኛ ያልተለየ አንድ ወዳጃችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ሰዎች ከእኔ ጋር ናቸው ብሎ መናገር ከባድ ነው፡፡ የእኛ ልብ ከሰዎቹ ጋር ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎቹ ግን ቀስ ብለው አሳርፈው ሸርተት ብለው ለመውጣት እየተሰናዱ ሊሆን ይችላል፡፡ የዓለም ታሪክ የምንለው እንዲህ ያለው የፈረሰ ፍቅር ታሪክም ነው፡፡ ለምን እንደተወደድን ለምን እንደተጠላን ምክንያቱን ባጣንለት ዓለም ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ መልሳችን ነው፡፡
እርሱን የሚጠራጠር ልብ፣ እርሱን የሚያማ አንደበት፣ ከእርሱ የሚሸሽ እግር የሌለን ለዚህ ነው፡፡ የእርሱ ፍቅር አይጠረጠርም፡፡ እንደ ህልውናው የፀና ነው፡፡ ፍቅሩ የማይጠረጠረው፡-
§ ስለወደድነው ሳይሆን የወደደን በራሱ ፍቅር ላይ ተመሥርቶ በመሆኑ
§ ስለመልካምነታችን ሳይሆን መልካም መሥራት ሳንጀምር ገና ሳንፈጠር ያፈቀረን በመሆኑ
§ ፍቅሩ ሽልማት ሳይሆን ስጦታ በመሆኑ
§ ፍቅሩ ዘላለማዊ ነው ተብሎ በመጻፉ ነው፡፡
ሰዎች የማይገኙበት የሕይወት ቀጠና አለ፡፡ ቢገኙም ሊረዱ የማይችሉበት ከባድ ቀን ይጋረጥብናል፡፡ እያለቀሱልን እያዘኑልን ምን ላድርጋችሁ? እያሉልን በችግር ውስጥ እናልፋለን፡፡ ምነው እናቴ ምነው አባቴ ዛሬ አብረውኝ በኖሩ ያልንበት ስደት፣ እስራትና ጭንቀት አሳልፈን ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ባናየውም እያየን፣ ባንጠራውም እየጠበቀን ነበር፡፡ ምክንያቱም ያን ቀን ለማማረር እንኳ የበቃነው ያን ቀን በጌታ ስላለፍን ብቻ ነው፡፡ ጉልበት የማያልፈውን ቀን አልፈን ስናይ፣ ጥበብና ዘመድ የማያሳልፈውን ቀን አልፈን ስናይ ምክንያቱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
ሰዎች የሚወዱን የሚወደድ ነገራችንን እንደ ቀብድ ይዘው ነው፡፡ ዓይናችንን፣ እጃችንን፣ ቁመናችንን፣ ትምህርታችንን ሀብታችንን ዓይተው ሊወዱን ይችላሉ፡፡ ደም ሳይረጋ፣ ጅማት ሳይተሳሰር፣ አጥንት ሳይሰካካ የወደደን ግን እግዚአብሔር ነው፡፡ በዚህ ጌታ ፍቅር ካላረፍን የትኛውም አፍቃሪ ቢመጣ ዕረፍት የለንም፡፡ ማንም በማይገኝበት ስፍራ ስለሚገኘው አምላክ ማሰብ ያስደስታል፡፡ የጠበቅናቸው እንዳልጠበቅናቸው ሲሆኑ ጀርባችንን የሰጠነው ጌታ ግን ፊቱን አሳይቶናል፡፡ በውኃ ውስጥ ማለፍ ቀላል አይደለም፡፡ ውኃ ዋና ለሚችሉ ደስታ ነው፡፡ ለማይችሉ ግን መቃብር ነው፡፡ ውኃ ደስታ የሚሆነው ለዋናተኞች ሲያጥር ብቻ ነው፡፡ የውቅያኖስ ውኃ ዋና በመቻልም የሚያቋርጡት አይደለም፡፡ በውኃ ውስጥ ማለፍ ከባድ ነው፡፡
እንደ ውኃ ለሕይወታችን አስፈላጊ የሆኑ፣ ብዙ የመሰከርንላቸው፣ የእኔ ናቸው ብለን የተናገርንላቸው ወዳጆቻችን ናቸው፡፡ የወረት ፍቅር ደስ ይላል፡፡ ቶሎ ቶሎ መገናኘቱ፣ የሆድ የሆድ ማውራቱ፣ መሳሳቁ ከቃላት በላይ ነው፡፡ ሲከርም አይስክሬሙ ያልቅና እሬቱ ይመጣል፡፡
እግዚአብሔር የሚያሻግር አምላክ ነው፡፡ በማሻገርም የታወቀ አምላክ ነው፡፡ ኖኅን በጥፋት ውኃ ውስጥ ያሻገረ ነው፡፡ አብርሃምን በብዙ ፈተና ውስጥ ራስ ወዳድነት ከሚያመጣው ጥፋት ያዳነ አምላክ ነው፡፡ ዮሴፍን በእስር ቤት የጠበቀ፣ በባዕድ አገር ከፍ ከፍ ያደረገ ጌታ ነው፡፡ እስራኤልን በደረቅ መሬት በባሕር ውስጥ የመራ፣ ኢያሪኮን አፍርሶ ለሕዝቡ ያከፋፈለ አምላክ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ባሕረ እሳትን በመስቀሉ ከፍሎ ያሻገረን የነፍሳችን መድኅን ነው፡፡
“በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ” (ኢሳ. 43÷2)
የወዳጅ ፈተና፣ የትዳር ፈተና፣ የልጅ ፈተና ብዙ ጎበዞችን የጣለ ነው፡፡ የገዛ ጥላን ማመን እስኪያዳግት ድንጉጥ ያደርጋል፡፡ የመውጫው በር እስኪጠፋ ለመዋጥ ቃጠሎ፣ ለመትፋት የሚቆጭ ይሆናል፡፡ የትዳር ፈተና፣ ብዙ የተመኙለት ልጅ እንደ እኛ አሳብ ሳይሆን እንደራሱ አሳብ ሲሆን ነገ አይታይ ብሎ ይጨልማል፡፡ በውኃ ውስጥ ማለፍ ከባድ ነው፡፡ በዓለም ላይ የምናምናቸው እነዚያው ሰዎች የማይታመኑ ከሆኑ፣ የሌሎችን ጉዳት ያስረሱን እነርሱ አቊሳይ ከሆኑ ወደ ማን ይኬዳል? እግዚአብሔር ግን ተስፋ ሰጥቶናል፡- “በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ” (ኢሳ. 43÷2)።
ወዳጅ ሄዶ የሚቀር ወዳጅ አለ፣ ትዳር ፈርሶ የሚፀና ትዳር አለ፣ ልጅ ክዶ የሚቀር ልጅ አለ፣ ሀብት በኖ የሚቀር ሀብት አለ፡፡ እርሱም እግዚአብሔር ነው፡፡ በብርጭቆ የሚጠጣው ሕይወት ሰጪ የሆነው ውኃ አደጋ ሆኖ በመጣ ጊዜ የያዝነውን ሳይሆን ራሳችንን ጭምር ይዞን ይጠፋል፡፡ ያለመድናቸውና ዋጋ የከፈልንላቸው፣ ከሕይወቴ ክፍል አንዱ ናቸው ብለን የመሰከርንላቸው፣ ወደ ሳሎናችን ሳይሆን ወደ ልባችን ያስጠጋናቸው፣ ያለንን ሁሉ ሰጥተናቸው ቅርሴ እናንተ ናችሁ ያልናቸው፣ የምናገረውን ሳይሆን የማስበውንም አውቀው ይረዱኛል ያልንላቸው፣ ተራቁተንላቸው ሁለመናችንን እንዲያውቁ የፈቀድንላቸው … እነርሱ አደጋ ሆነው የመጡ ቀን መቋቋም ይከብደን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከወዳጅ ይልቅ የሚጠጋጋ ትልቁ ወዳጃችን፡- “በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ” ብሎናል፡፡ እርሱ ከእኛ ጋር ሆኖ ታግሎ የሚጥለን፣ ገፍፎ የሚያራቁተን፣ ነሥቶ የሚያስርበን፣ ከሶ የሚረታን፣ ተናግሮ የሚሰብረን ማን ነው? ሁሉም ሄዷል በምንልበት ሰዓት ሳይሆን ሁሉም አለኝ በምንልበት ጊዜም ያለንና የነበረን የሚኖረን እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ያፈሰስነውን ዕንባ፣ የምንሰማውን መቋቋም አቅቶን የተሰበረውን ልባችንን እርሱ ዓይቶታል፡፡ እንዲህ ቆመን የሄድነው፣ እንዲህ ተጽናንተን ሌላ ማቀድ የጀመርነው፣ ቶሎ ረስተን ከነበርንበት ስሜት መውጣት ስለምንችል አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ስላሻገረን ነው፡፡ ታዲያ በደንብ ያለቀስነው እኛ ምነው በደንብ አናመሰግንም?
“ባለፍህ ጊዜ” እግዚአብሔር እንዳናልፍ አድርጎ አይረዳንም፣ የሚያሰጥመው ባሕር መንገድ እንዲሆንልን ግን ይረዳናል፡፡ ማለፍ ግድ ነው፡፡ የዓለምን ከዳተኝነት፣ የእግዚአብሔርን አጋዥነት የምናየው በማለፍ ነው፡፡ ያለፍንበት ውኃ ከእግዚአብሔር ጋር ይበልጥ አጣበቀን እንጂ አልጎዳንም፡፡ ለጊዜው ቢያሳዝነንም እውነተኛ አለኝታ እግዚአብሔር እንደሆነ አየንበት፡፡ ሁሉንም ይኸው አየን፡፡ አምላካችን ብቻ ታላቅ እንደሆነ ተረዳን፡፡
እንደ ሞተ ሰው ተበላሽተዋል የተባሉ፣ መቃብር እንደ ገባ ከእንግዲህ ዘመድ አይሆኑም የተባሉ፣ ተዝካራቸው እንደወጣ ወደ ኋላ የቀሩ፣ ብቻቸውን በሙታን ሰፍር የተጣሉ እንደ ገና በክርስቶስ ሰው ይሆናሉ፡፡ እግዚአብሔር ለዝናው ሲያበቃቸው ይታየኛል፡፡ ለከሰሱአቸው ዳኛ፣ ላስራቡአቸው መጋቢ፣ ለረገጡአቸው አለቃ፣ ላቆሰሉአቸው ሐኪም ሆነው በመልካም ሲበቀሉ ይታየኛል፡፡ ይህ የሰው ራእይ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል፡፡
“በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም”
(ኢሳ. 43÷2)
የሚያሰጥመው ነገር ማስጠም የማይችለው በማን ከልካይነት ነው? ስንል በእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ ወንዝ በኃይል፣ በስፋት፣ በፍጥነት ከፊቱ ያገኘውን እየጠረገ፣ ከጎኑ የነካውን እየሳበ፣ ለጊዜው አሳስቆ ቆይቶ ገድሎ የሚጓዝ ነው፡፡ ቢጮኹ አይታገድ፣ በዳኛ፣ በሹም፣ በሕግ አምላክ ቢሉት አይፈራም፡፡ በሕይወት ላይ እንደ ወንዝ ያለ ቀን ይመጣል፡፡ ሁሉም ነገር በድንገት ያልቃል፣ የከበቡን በአንዴ ይበተናሉ፡፡ ተባብረው የሸለሙን ዘርፎናል ለፍርድ ይቅረብልን ይላሉ፡፡ በአንድ ቃል ያመሰገኑን በአንድ ቃል ይሙት በቃ ብለው ይፈርዱብናል፡፡
በላይ በላይ እንዳልጎረስን፣ በአፋችን ያለውን ሳንውጥ ቀጣዩ ጉርሻ በአፋችን እንዳልቀረበልን በላይ በላዩ ክስረትን እንሰማለን፡፡ በላይ በላዩ እንዳልደረብን በካባ ላይ ቀፀላ በቀፀላ ላይ የወርቅ ፈርጥ እንዳላስቀመጥን ሁሉም ነገር ተቀዶ ራቁታችንን እንቀራለን፡፡ በምሥጢር የሚመክሩን የነበሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጡብናል፡፡ ብቻቸውን የወደዱን ብዙዎችን አስተባብረው ይጠሉናል፡፡ መከራ እንደ አክንባሎ በላያችን ላይ ይጫናል፡፡ ወዳጆቻችን፣ የትላንት ሎሌዎቻችን ራሳቸውን ሊቆጣጠሩት እስኪያቅታቸው በእኛ ላይ ይነሣሉ፡፡ ስንዴ ዘርቻለሁ ስንል መኸሩ እንክርዳድ ይሆናል፡፡ አሸንፌአለሁ ስንል ተማርከሃል እጅ ወደ ላይ እንባላለን፡፡ እንደ ወንዝ ፈሳሽ ያለው ቀን እንዲህ ያለው መርዶ የሚሰማበት ቀን ነው፡፡
ቀትሩ ወዲያው ሌሊት የሆነበት፣ ፍጥነቱን ባለሥልጣን ዘመድ፣ ይገባሃል የሚል ዳኛ የማያስቆመው ያ በራሪ ቀን አስፈሪ ቢመስልም እግዚአብሔር ግን መንገድ አለው፣ መላ አለው፡፡ ይህ ቢደርስብኝ አልኖርም እንዳላልን፣ በሰው ሲደርስ ዓይተን እንዳልመነንን በራሳችን የደረሰ ቀን ግን እግዚአብሔር ጽንዓቱን ይሰጠናል፣ አፋችንን በደስታ ይሞላል፡፡ “በወንዞች ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥምህም” ብሏልና፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ዓባይን በጀልባ እየቀዘፈ ወደ ሱዳን ለመሄድ ለሚፈልጉ ተጓዞች ዋስትና አይሰጥም፡፡ በባድመ በኩል ወደ ኤርትራ ለማለፍ ለሚሹ ዋስትና አይሰጥም፡፡ እግዚአብሔር ግን በሕይወት ማዕበል ውስጥ ለሚያልፉ፣ በፈንጂ ወረዳ ለሚያቋርጡ ልጆቹ ዋስትናን ይሰጣል፡፡ የሚያሳልፈውን ቀን ያሳልፈዋል፡፡
“በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም ነበልባሉም አይፈጅህም” (ኢሳ. 43÷2) ይላል፡፡ አጥር ይዘለላል፣ እሾህም ይረገጣል፡፡ በእሳት ውስጥ ግን ማቋረጥ አንበሳ እንኳ የማይደፍረው ነው፡፡ ያለው ዕድል አቋርጦ መጨረስ ሳይሆን ተቃጥሎ ማለቅ ብቻ ነው፡፡ መንገዱ ሳይጋመስ መንገደኛው ማነስ ይጀምራል፡፡ ቢመለስም እንኳ ሕይወቱ እንጂ መልኩ እንደ ቀድሞው አይሆንም፡፡ ነበልባሉ ያበላሻል።
በእሳት ውስጥ ማለፍ በኃላፊነት ውስጥ ማለፍ ነው፡፡ የተሾመ ሰው ሁሉን ማስደሰት አይችልም፡፡ አልሰማም፣ አላይም ብሎም የመመነን መብት የለውም፡፡ ሁሉንም ይሰማል፣ ሁሉንም ያያል፡፡ ትዳሩ ላይቀር ይወቅሰዋል፣ የሚረካበት እያጣ ሁሉም ሲያጉረመርምበት ያያል፡፡ የትላንት በጎነቱ አይታሰብም፡፡ ትንሽ ስህተቱ ይጎላል፡፡ መልካምነቱን የእነ እገሌም ልፋት ነው ሲሉት ስህተቱን ግን የራሱ የግሉ ድክመት ነው ይሉበታል፡፡ ኃላፊነት ብንሸሸውም የሚይዘን ጊዜ አለ፡፡ እግዚአብሔር ግን ሰባት ቢለየን ሕዝብ የሚያስተዳድርበትን ችሎታውን እያሳየን ያጽናናናል፡፡
ኃላፊነት እሳት ብቻ ሳይሆን ነበልባልም አለው፡፡ እዚያ ጋ የተለኰሰው ነበልባሉ እዚህ ደርሶ ይፈጃል። እኔ የለሁበትም ማለት እስከማይቻል የሌሎችን ዕዳ መሸከም ይኖራል፡፡ እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቃዱ ስንኖር ከእሳቱ ቃጠሎ፣ ከነበልባሉ ፍጅት ያድናል፡፡ እንዴት አልፌ አወራው ይሆን? አትበሉ እግዚአብሔር መንገድ አለው! እርሱ እሳቱን አጥፍቶ ያድናል። እሳቱ እያለም እንዳያቃጥለን አድርጎ ያድናል። በብዙም ሆነ በጥቂት ማዳን ይቻለዋል። እርሱ ጥበበኛ የማይችለውን፣ ሐኪም ያቃተውንም ይፈታል። መርከብ እየሰመጠ በባሕር ላይ በእግር ያራምዳል። ወገኖቼ እግዚአብሔር መንገድ አለው። እርዳኝ እንጂ እንዴት ትረዳኛለህ? አይባልም። ደመና መሳፈሪያው፣ ውቅያኖስ መረማመጃው ነው። ምስጋና ለታላቅነቱ ከምድር እስከ አርያም አሜን።