እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሆይ ፣ አንተ የይለፍ ቃሌ ፣ የደኅንነት ነጭ ዓርማዬ ፣ የስኬት ምንጬ ነህ ። ያላንተ ማኅተም በሰማይ መንግሥት እውቅና የለኝም ። መንፈሰ ጽድቅ ሆይ ፣ እኔን እኔው ሳውከው የመዳን ቀንድ ሁነኝ ። እኔን ሰው ሲያውከኝ ጋሻህ ይዘርጋልኝ ። እኔን ኑሮ ሲያውከኝ በረከትህ አለሁ ይበለኝ ። እኔን ቀኑ ሲያውከኝ መጽናናትህ ይድረሰኝ ። አክአብን እንደ ገሠጸ ኤልያስ ፣ ዳዊትን እንደ ወቀሰ ናታን ፣ ሄሮድስን እንደ ዘለፈ ዮሐንስ መጥምቅ እውነተኛ ሰው አድርገኝ ። ጠዋት ለማታ ዓለም እያለፈ ነውና የጸናኸው አንተ ቡሩክ መንፈስ ሆይ አጽናኝ ። አሜን ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 4 ቀን 2014 ዓ.ም.