የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መንገድ አለው / ክፍል 4

ሐሙስ ሐምሌ ፲፮ / ፳፻፯ ዓ/ም
በስምህም ጠርቼሃለሁ (ኢሳ.43 ÷1)፡፡
በውጭ አገር የሚኖር አንድ ወንድም ከፍተኛ በሆነ ጭንቀት ውስጥ መሆኑን ሰማሁኝ፡፡ ቤተሰቦቹ በተጉት መሠረት ደወለልኝ፡፡ ይህ ወጣት ከአገር ሲወጣ አውቃለሁ፡፡ ወደ ፈረንጅ አገር ሲሄድ ወደ እናቱ ቤት እንደሚሄድ ከኢትዮጵያ ሲወጣም ከእስር ቤት እንደተፈታ ተሰምቶታል፡፡ በዚያ ወቅት ልቤ በጣም ተጨንቆ ነበር፡፡ ምክንያቱም የፈረንጅ አገር እዚህ እንደሚታሰበው አይደለምና፡፡ ሰው ከፍተኛ ተስፋ የጣለበትን አገር እንደጠበቀው ካላገኘው ጭንቀቱ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ከጭንቀት መንስኤዎች አንዱ የጠበቅነውን ነገር በጠበቅነው ልክ ባለማግኘታችን የሚመጣ ተስፋ መቊረጥ ነው፡፡ መቼም በዓለም ላይ ከጠበቅነው በላይ የምናገኘው ክርስቶስን ብቻ ነው፡፡ የዚህ ዓለም ነገር ግን ከጠበቅነው በታች መገኘቱ ባሕርይው ነው፡፡ ያ ወጣት እንዲህ ያለ ግራ መጋባት እንደሚገጥመው እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ የፈሩት መድረሱ፣ የጠሉት መውረሱ አይቀርምና ያ ልጅ በጭንቀት ተያዘ፡፡ እርሱ በደወለው ስልክ የጭንቀቱ ምክንያት ምን እንደሆነ ብዙ ተነጋገርን፡፡ የጭንቀቱ ምክንያት ትንሽ የሚመስል ግን ትልቅ ጉዳት ያስከተለ ነበር፡፡ ያ ወንድም፡- “የእጅ ስልኬን አያለሁ የሚደውልልኝ የለም፣ ምናልባት ተዘግቶ እንደሆነ ብዬ ስልኩን ወደሰጠኝ ተቋም እደውላለሁ እንዳልተዘጋ ይነግሩኛል፡፡ እንደገና ወደ ቤት ስልኬ እደውላለሁ፡፡ የቤቱ ስልክ ይጠራል፡፡ ታዲያ የሚፈልገኝ ሰው የለም ማለት ነው፡፡ የሚፈልገኝ ሰው ከሌለ መኖር ምን ይሠራልኛል?” አለኝ፡፡
የዚህ ወንድም ትልቅ ጭንቀቱ አለመፈለግ ነበር፡፡ በስሙ ጠርቶ ‹‹እንደምን አደርክ?› የሚለው ሰው ማግኘት ፈልጎ ያላገኘው ጥማቱ ነበር፡፡ የዚህ ወንድም ፍላጎቱ ትንሽ መልሱም ጥቂት ይመስለን ይሆናል፡፡ ለሌለው ሰው ግን ትንሹ ትልቅ፣ ሐኪም ላላገኘ ቀላሉ ከባድ መሆኑን የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ ከዚህ ወንድም በኋላ ባለኝ ትንሽ አቅም ሆደባሻ እንደሆኑ የምጠራጠራቸውን ሰዎች እየደወልኩ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነው ቀኑ በስሙ ይቀደስላችሁ ማለት ጀመርኩ፡፡ ለአንድ ሰው እንኳ መኖር ምክንያት መሆን መታደል ነው!  

በስማችን የሚጠራን ወደ እኛ የቀረበ፣ ሊያነጋግረን የሚፈልግ ነው፡፡ ስም መጥራት አውቅሃለሁ፣ እወድሃለሁ፣ ካንተ ጋር ጉዳይ አለኝ፣ በርህን ክፈትልኝ የሚል መልእክት አለው፡፡ “ስም ያለው ሞኝ ነው” እንደሚባለው ሞክሼአችን እንኳ ሲጠራ በየመንገዱ እንደነግጣለን፡፡ በመደንገጣችን እንናደዳለን፣ እንገረማለን፡፡ ምነው ለእኔ በሆነ ብለን ይመስላል፡፡ የሰው ልጆች ሁልጊዜ ሊሰሙት የሚፈልጉት ሙዚቃ ቢኖር የገዛ ስማቸው ነው ይባላል፡፡ ስማቸው ሲጠራ ደስ ይላቸዋል፣ ፈገግ ይላሉ፣ ልባቸው መከፈት ይጀምራል፣ የታወቅሁ የተፈለግሁ ነኝ የሚል ስሜት ያድርባቸዋል፡፡ የትኛውንም የምሥራች ከመስማታቸው በፊት ስማቸውን መስማት ይፈልጋሉ፡፡ ስማቸውን ካልሰሙ ከዚያ ሰው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ልበ ሙሉ አያደርጋቸውም፡፡ የሚዋደዱ ሰዎች ሲጣሉ የመጀመሪያው የጠባቸው መግለጫ፣ የጠባቸው የቅጣት በትር ስም መጥራት ማቆም ነው፡፡ ቀጥሎ በሠራተኛ ወይም በልጅ በኩል ወይም በጓደኛ ወይም በሦስተኛ ወገን ንግግር ማድረግ ነው፡፡ ስም መጥራት የፍቅር መግለጫ ነው፡፡ ለግንኙነትም የነጻነት ቁልፉ ነው፡፡ ስም መጥራት ስናቆም በቀጥታ መገናኘት እናቆማለን፡፡ 

 

ከሁሉ በላይ አንድ የአገር መሪ ወይም ትልቅ ባለሥልጣን በስማችን ሲጠራን ደስታችን ወደር የለውም፡፡ ከዚያ ሁሉ ሕዝብ መካከል የእኛን ስም ለይቶ መጥራቱ በልዩ የመታወቅ ደስታን ይጭርብናል፡፡ ከፍ ካሉት በላይ ከፍ ያለው እግዚአብሔር በስማችን ሲጠራን እጅግ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ እርሱ በጅምላ ሳይሆን በልዩ ያውቀናል፡፡ እንዲያውቀን ራሳችንን ማስረዳት አያስፈልገንም፡፡ ራሳችንን ሳናውቀው በፊት ያውቀናል፡፡ ራሳችንን ከምናውቀው በላይ ያውቀናል። ሰዎች እንደሚሉንም አይለንም።
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፡- “በስምህም ጠርቼሃለሁ& አንተ የእኔ ነህ” ብሎናል          (ኢሳ. 43÷1)፡፡ የአገራችን መሪ 80 ሚሊየን ሕዝብ እንደሚያስተዳድሩ ያውቃሉ፣ እያንዳንዳችንን ግን በስማችን አያውቁንም፡፡ እግዚአብሔር ግን በጅምላ ሳይሆን በግላችን ያውቀናል፡፡ በስማችንም ይጠራናል፡፡ እግዚአብሔር በስማችን ሲጠራን፡-
1.     ያውቀናል
2.    ቀርቦናል
3.    ተወዳጅቶናል
4.    ጉዳይ አለው ማለት ነው።
ያውቀናል
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ፍቅር በተናገረበት አንቀጹ ፡- “… ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ” ብሏል (1ቆሮ. 13÷12)፡፡ ዛሬ በእውቀት ደስ ይለናል፣ በእውቀት ደስ የሚለንም የማያውቁ ሰዎችን በመብለጣችን ነው፡፡ ወደ ሰማይ ስንሄድ ግን ካወቅነው እውቀት ይልቅ በእግዚአብሔር መታወቃችን ደስ ይለናል፡፡ የምናስበው፣ የምናልፍበት መንገድ፣ ስብራታችን፣ ሸክማችን … በእግዚአብሔር የታወቀ፣ ከዕይታውም ስውር እንዳልነበረ ስንረዳ ለዘላለም ደስ ይለናል፡፡
ወላጆቻችን የሚያውቁን ስንወለድ ነው፡፡ ባዩን ጊዜ ሳሱልን፡፡ እግዚአብሔር ግን በማኅፀን ያውቀን ነበር፡፡ ፈሳሽ ሳለን ፣ ደም ሳይረጋ፣ አጥንት ሳይሰካካ፣ ጅማት ሳይተሳሰር ያውቀን ነበር፡፡ ከማኅፀን ጀምሮ በልዩ እንክብካቤ እየተንከባከበ ለዚህ አድርሶናል፡፡ በሸለቆ በተራራው አልተለየንም፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ የለፋብን ሊጥለን ነውን? እኛ እንኳ ለምንጥለው ነገር አንደክምም፡፡ እኛ ዓላማ ባይኖረን እንኳ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ዓላማ አለው።
እግዚአብሔር በተደነቀች እውቀቱ ዓለም ሳይፈጠር ያውቀናል፡፡ ዓለም ሳይፈጠር በማዳን ዕቅዱ ውስጥ ከትቶናል፡፡ ፍቅሩ ታሪክ ያመጣው ዘመን የወለደው ሳይሆን  ከዘላለም ነው፡፡ ዛሬም የምናልፍበትን የሕይወት ገጽታ፣ የውስጣችንን ስሜት ልናስረዳው እንሞክራለን፡፡ እግዚአብሔር ግን ያውቀናል፡፡ ድካማችንንም ያውቀዋል፡፡ እንዳልሰማ ዝም ቢል፣ እንደማይሰጥ ቢዘገይም እግዚአብሔር ግን ለእኛ የመደበው ጊዜ አለው፡፡ ጽንስ ያለጊዜው ቢወለድ ልጅ አይሆንም። ዘር ያለጊዜው ቢታጨድ ፍሬ አይሆንም። የእግዚአብሔር በረከትም በእግዚአብሔር ጊዜ ሲሆን ውበት አለው።
ቀርቦናል
በስማችን የሚጠራን ወደ እኛ የቀረበ ወዳጃችን ነው፡፡ በስማችን የሚጠራን ዘወር ይሉልኛል ብሎ ተስፋ አድርጎ ነው፡፡ በስማችን የሚጠራን ፊታችንን ወደ እርሱ እንድናዞርለት፣ ከመንገዳችን ቆም እንድንልለት፣ ፍቅሩንና ዓላማውን፣ በጎ ምኞቱን እንድንሰማለት ነው፡፡
እግዚአብሔር ቀርቦ እየጠራን ነው፡፡ ቃሉ፡- “እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት ቀርቦም ሳለ ጥሩት”ይላል (ኢሳ. 55÷6)፡፡ እግዚአብሔር እጅግ የቀረበበት ዘመን ላይ ነን፡፡ እኛ ደግሞ እጅግ ርቀነዋል፡፡ እግዚአብሔር ቀርቦአልና፡-
                      ፊታችንን ወደ እርሱ እንመልስ፣ ጀርባችንን የሰጠንበት ዘመን ይብቃ፡፡
              እየነጎድን ካለንበት የገዛ መንገዳችን ቆም ብለን ጌታ ሆይ በዚህ ነገር ውስጥ አንተ አለህበት ወይ? አንተ የሌለህበት መንገድ ፍጻሜው ጥፋት ነው። እባክህን ፈቃድህን አሳየኝ ማለት አለብን፡፡
              ምን ያህል እንደወደደን፣ የቀራንዮ የፍቅሩን ተአምራት እናሰላስል፡፡ በእኛ ላይ ያለውን ዓላማውን እንለይ፡፡ በጎ ምኞቱን እንዲፈጽም ራሳችንን እንስጠው፡፡ እግዚአብሔር በጸጋው ቀርቦናል፡፡ ከራቀን ግን ጭንቁ ብዙ ነውና እንወቅበት፡፡
ተወዳጅቶናል
በስማችን የሚጠራን ቢያንስ ከዚህ በፊት ወይ በመልካችን ወይ በሥራችን የሚያውቀን ነው፡፡ ከዚህ በፊት የሚያውቀን ጌታ በስማችን ጠርቶናል፡፡ በማኅፀን የሚያውቀን፣ ስንወለድ የተቀበለን፣ በልዩ ጥበቃ ያሳደገን፣ ያበላን ያጠጣን. . .. አዎ ከዚህ በፊት የሚያውቀን ጌታ ይጠራናል፡፡ የሚጠራን የቀድሞ ወዳጅህ እኔ እሻልሃለሁ በማለት ነው፡፡
ትልቁ ጌታ ከእኛ ከወራዶቹ ጋር ኅብረት ሲያደርግ እንደ ማነስ አልቆጠረውም፡፡ ፍቅር ዝቅተኞችን አይንቅም፡፡ የራሱን ክብር ሰጥቶ ከፍ ያደርጋቸዋል፡፡
ጉዳይ አለው
እኛ ለእግዚአብሔር ከምናስፈልገው ይልቅ እግዚአብሔር ለእኛ ያስፈልገናል፡፡ እግዚአብሔር እኛን የሚፈልገን ለተራ ግንኙነት፣ ለጊዜ ማሳለፊያ ሳይሆን ለመንግሥት ጉዳይ፣ ለዘላለም ሕይወት ነው፡፡ ጌታ ሆይ ከእኔ ምን ትፈልጋለህ? ይኸው ማንነቴን ውረሰው ልንለው ይገባል፡፡ “በስምህም ጠርቼሃለሁ” (ኢሳ. 43÷1)
ስምን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ እግዚአብሔር፡-
1.             ስም ያወጣል።
2.            ስም ይቀይራል።
3.            በስም ይጠራል፡፡
መጥምቁ ዮሐንስ ገና ሳይወለድ ስም ወጥቶለታል (ሉቃ. 1÷13)፡፡ ስም የሚያወጣ አባት ልዩ ወዳጅ ነው፡፡ ለዮሐንስ ከዘካርያስ ይልቅ እግዚአብሔር አባቱ ነው፡፡ ስለዚህ ገና ሳይፀነስ ስም አወጣለት፡፡ እግዚአብሔር ከአባት ይልቅ አሳቢ፣ ከእናት ይልቅ ቅርብ፣ ከወንድም ይልቅ የሚጠጋጋ፣ ከእህት ይልቅ የሚሸፍን ነው፡፡
እግዚአብሔር ስምን ይቀይራል፡፡ አብራምን አብርሃም ያለው እርሱ ነው፡፡ ስሙ ራእዩን እንዳያሳንሰው አብርሃም አለው፡፡ የብዙዎች አባት እንዲሆን ፈልጓልና፡፡ አብርሃም ማለት የብዙዎች አባት ማለት ነው። ስም ያስራል፣ ስም እንቅፋት ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ስምን በመቀየር የታወቀ ነው፡፡ ስምዖንን ጴጥሮስ ያለ ይህ ጌታ ነው፡፡ ዛሬም ስማችንን ብቻ ሳይሆን ታሪካችንን ሊለውጥ ሌላ ሰው ሲያደርገን እያየን ነው፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ በስማችን ይጠራናል፡፡ ወዳጅነቱን ይገልጥልናል፡፡ ፍቅር የሚፈለግ አይደለም፡፡ ፍቅር የተገኘ ነው፡፡ ቀራንዮ የፍቅር ትምህርት ቤት ነው፡፡ የሚወዱንን ገና አንፈልግም የሚወደንን ጌታ እናምነዋለን፡፡
                           “በስምህም ጠርቼሃለሁ” (ኢሳ. 43÷1)
                                        ይቀጥላል
 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ