መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የዘመናት ናፍቆቴ

የትምህርቱ ርዕስ | የዘመናት ናፍቆቴ

አንተ ረዳኤ ምንዱባን የችግረኞች አጋዥ ፣ አንተ ተስፋ ቅቡፃን የጨለመባቸው መብራት ፣ አንተ አሰጣጥ የምታውቅበት ፣ የመስጠት ችሎታ ያለህ ፣ ከሞት በኋላም የምትጋብዝ ትልቅ ወዳጅ ፣ በባሕርይህ ድካም ፣ በአካላትህ ባዕድ የሌለብህ ፣ አድሮ ሁሉን ሳጣው አድሮ የማገኝህ ፣ ፣ ትሰጠኛለህ ብዬ ሳይሆን ሰጥተህ ያኖርከኝ ፣ ከእኔ ምንም ባይገኝም እንደሚያገኝ ሁነህ የፈለግኸኝ ፣ ቤተ ክርስቲያንን የበረሃ ምንጭ አድርገህ የሰጠኸኝ ፣ ጨለማዬ ላይ ይብራ ብለህ ያወጅኽልኝ ፣ የጸናው ማንነትህ ያልጸናውን እኔነቴን ያልናቀኝ ፣ እራመዳለሁ ስል ብወድቅም ተነሥ ብለህ ያበረታኸኝ ፣ እየሠራሁ ሳበላሽ በገርነት ጎበዝ ያልከኝ ፣ በቤትህ ጠፍቼ ሳለሁ በደጅ በጠፉት ስፈርድ የመከርኸኝ ፣ በሚያረክሰው ዓለም ያገኘሁህ ጸዓዳ ልብስ አንተ እግዚአብሔር ነህና ተመስገን ። የእኔ ሠራተኛ ፣ ጓዳዬን የምትሞላ ፣ በቤትህ ባድርም አንተ ግን በእኔ ውስጥ ያደርህ ፣ ለመማረክ ወጥቼ አንተ ግን የማረከኝ ፣ ቀኑን ሙሉ ስባዝን ቀኑን ሙሉ የፈለግኸኝ ፣ በምቾቴ ስክድህ በመንሣት ሳይሆን አሁንም በመስጠት ያስተማርከኝ ፣ አጢኜ የማልፈጽምህ እግዚአብሔር ተመስገን ።
የሰዎችና የሁኔታ ጥገኛ ብሆንም ፣ የቀኑ ወሬ ይዞኝ ብጠፋም ፣ ምድራዊ ጠባቂን እየፈራሁ ጠባቂ መልአኬን ባላከብር ፣ ፍርድ ቤትን እየሰጋሁ ትንሣኤ ዘጉባዔን ብረሳም ፣ በዋጋ ገዝተኸኝ በነጻ ብጠፋም ፣ ሥራዎቼን አተልቄ ውለታህን ባሳንስም ፣ የሚያገለግለኝን አገልጋይ ትቼ የሚገዛኝን ባፈቅርም ፣ ባልቀደምሁበት ሂዱ ብዬ ባውጅም ፣ የማትሞት አባት አንተ በይቅርታ ዓይንህ ታየኛለህ ። የዘመናት ናፍቆቴ ባንተ እንደሚፈጸም አምናለሁ ። አሜን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 22 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም