ቅዳሜ ሐምሌ ፬/ ፳፻፯ ዓ/ም
“አሁንም ያዕቆብ ሆይ÷ የፈጠረህ÷ እስራኤልም ሆይ÷ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል- ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ÷ አንተ የእኔ ነህ፡፡ በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ÷ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም ነበልባሉም አይፈጅህም” (ኢሳ. 43÷1-2)፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምናገኛቸው ብርቅዬ የተስፋ ቃላት አንዱ ይህ ክፍል ነው፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ለልጆቹ ቃል አለው፡፡ በዳኛ ፊት ቆመን ከባላጋራችን የሚገላግል ቃል ስንጠብቅ በወራት ቀጠሮ ይሸኘናል፡፡ በሐኪም ፊት የፈውስ ቃላት ስንጠብቅ ተስፋ በሚያስቆርጥ ድምፅ መሸኘት ብቻ ሳይሆን ያልበላን ጓደኛው እንዲበላን እገሌ ሐኪም ጋ ሂዱ ብሎ ይሸኘናል፡፡ ወዳጆቻችን አብረናቸው ለመኖር የቃል ኪዳን ቀኑን ቁረጡልን ስንላቸው የስንብት ቃል ያሰሙናል፡፡ አድገው ይደግፉናል ስንል ልጆቻችን ይረሱናል፡፡ ይተኩልናል ብለን ስንጠብቅ ደቀ መዛሙርቶቻችን የሚሰብር ቃል ይነግሩናል፡፡ በእውነት ይህችን ዓለም የገጠማት ከኢኮኖሚ ቀውስ ይልቅ የመልካም ቃል እጦት ነው፡፡ ቃልን ተርበናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ለእኛ የተስፋ ቃል አለው ራሳችንን አታለን የምንገባበት ሳይሆን በእርግጥም የሚሆን ቃል እግዚአብሔር አለው፡፡ ልጆቹ ስንሆን ተስፋውና ቃል ኪዳኑ ለእኛ ይሆናሉ፡፡
ቃል ያነሣል፣ ቃል ይጥላል በቃል ሰዎች ይኖራሉ፣ በቃል ይሞታሉ፡፡ ቃል ያጽናናል፣ ቃል ይሰብራል፡፡ ፈረቃ የሌለው መልካሙ የእግዚአብሔር ቃል ግን ትንሣኤና ሕይወት ይሰጣል (ዮሐ. 6፡63)፡፡ ወጌሻ የማይጠግነውን የሕይወት ስብራት ቃሉ ይጠግናል፡፡ የዚህች ዓለም ዕድሜ የረዘመው፣ ብዙዎች ለመኖር አቅም ያገኙት፣ በችግራቸው ላይ የዘመሩት፣ በእሳት ውስጥ የተቀኙት እግዚአብሔር የሰጣቸውን ቃል ተተግነው ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል፣ ቃል ኪዳን ነው፡፡ ከሰው ቃልም ይለያል፤ የመፍጠር፣ ለሞተው ነገር ሕይወት የመስጠት አቅም አለው፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ የተላለፈው የተስፋ ቃልም ዛሬም ሕያው ሆኖ ይሠራል፡፡
“ቀጥሎ ምን እሰማ ይሆን?” የሚል ጭንቀት ፍጥረትን እየናጠው ነው፡፡ በፍርድ ቤት ቀጠሮ፣ በሐኪም ቤት ቀጠሮ፣ ከወዳጅ ጋር ቀጠሮ፣ አለቃ ጋ ቀጠሮ፣ በኤምባሲ ቀጠሮ ያለባቸው ሲማቅቁ እናያለን፡፡ የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት ስላቆመ ከሰዎች ‹‹ምን እሰማ ይሆን?›› በሚል ፍርሃት እየተናጠ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል እንሰማለን የምንለውም ቃሉ በውስጣችን ተዋህዶ ፈውስና ሰላም እንዳይሆነን እምነት የለንም (ዕብ. 4÷2)፡፡ ቃሉን በጆሮአችን እንጂ በልባችን መስማት አልሆነልንም፡፡
አሜሪካ አገር ለመሄድ ሂደቶች ላይ የነበረች አንዲት እህት እዚያ ሄዳ ለምታገኘው በረከት እዚህ የጨበጠችውን ሁሉ ጣለች፡፡ እስከምትሄድ እንኳ መሥራት አቅቷት ንግዷን ሁሉ ዘጋች፡፡ ኅሊናዋን በሙሉ የተቆጣጠረው ይህ የመንገድ አሳብ ስለነበረ ዕለት ዕለት ፍርሃት እየከበባት መጣ፡፡ እዚህ ለመኖር የምትቸገር ወጣት አይደለችም፡፡ በእርሷ ዕድሜ የማይሰበሰብ ገንዘብ ሰብስባለች፤ እንዲሁም ከአንድ ዩኒቨርሲቲም በዲግሪ ተመርቃለች፡፡ ነገር ግን ዕድሏ ሁሉ ያለው አሜሪካ መስሎ ተሰማት፡፡ አሜሪካ ለእርሷ በረከት ሳይሆን ሕይወት መሰላት፡፡ መኖር በሰጪው እግዚአብሔር እንደሆነ ዘነጋች፡፡ ሩቅ አገር የሚሰጠው ጌታ በአገሯ ሊሰጣት እንደሚችል ጨለመባት፡ ይህ ፕሮሰስ ካልተሳካ ምን እሆናለሁ? ሰውስ ምን ይለኛል? አሜሪካ ካለውና ቃል ኪዳን ከፈጸመልኝ ነገር ግን ወለም ዘለም ከሚለው ማግባቱን ገና ካልተቀበለው ባሌ ተለይቼ ልኖር ነው? ይህንን ማሰብ እንኳ አልፈልግም እያለች መጨነቅ ጀመረች፡፡ ቤተሰቧ ደግሞ መጨነቋን እንዳያውቅባት መሸሽ ጀመረች፡፡ ራሷን ያሸከመችው መስቀል ከብዷት መንገዳገድ ጀምራለች፡፡ ወደ እኔ ጋ ሲያመጧት እንቅልፍ ከራቃት ብዙ ቀናቶች እንደሆኗት ነግራኛለች፤ ሰውነቷም መንምኗል፡፡
ንግግሯን ቀጠለች፡- “ ከመጨነቄ የተነሣ መጮህ አማረኝ እቤቴ እንዳልጮህ ያለሁት በኪራይ ቤት ውስጥ ነው ውጪ ቢሉኝስ፣ መንገድ ላይ እንዳልጮህ ሰው አበደች ቢለኝስ፣ የመጮህ መብት ያለበት የት ይሆን? ብዬ ሳስብ ሳስብ በስንት ፍለጋ አገኘሁት፤ እርሱም የጠበል ቦታ ነበር፡፡ ደስ ብሎኝ ሄድኩ፣ ገና ጠበል ውስጥ እንደገባሁኝ ጩኸቴን አቀለጥኩት፡፡ ቄሱም መስቀላቸውን ይዘው ማን ነህ? ተናገር ሲሉ፡- ‹‹አባ ፕሮሰስ ነው›› ስላቸው አዲስ ጋኔን የመጣ መስሏቸው፡- ‹‹ተናገር የት ነው የያዝካት›› ሲሉ ‹‹አባ እኔ ራሴ ነኝ ጨንቆኝ ነው›› ብዬ ነገርኳቸው . . . ” አለች፡፡
በሕይወት ውስጥ ከመሆንና ካለመሆን የበለጠ የሚያስደስት ነገር አለ፡፡ እርሱም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ የሆነ የተሳካ ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም፡፡ ስላልሆነም የሕይወት መጨረሻ አይደለም፡፡ የመሆን ደስታ ያለው እግዚአብሔር ሲኖርበት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሌለበት ከሆነ ስኬት ብቻውን አያረካም፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሆነበት አለመሳካት ይበልጥ ደስ ያሰኛል፡፡ ምክንያቱም “እግዚአብሔርንም ለሚወዱ እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን” ይላልና (ሮሜ. 8÷28)፡፡ ነገሮች ባይሳኩም “እንደ ፈቃዱ” ስንል የተሻለ ነገር እንዳለን እያወጅን ነው፡፡ በሰው ፈቃድ ከሆነ ነገር በእግዚአብሔር ፈቃድ ያልሆነ ነገር ዋስትና አለው፡፡
ይህች እህት እንቅልፍ የነሣት፣ ለኢንተርቪው ብላ ብዙ ጥያቄዎችን አውጥታ ራሷን እየጠየቀች መልሱን ለራሷ በመስጠት የተለማመደችበት ያ የቀጠሮ ቀን ደረሰ፡፡ አንዳች ጥያቄ ሳትጠየቅ ቪዛ ሰጧት፡፡ የከፈለችው ዋጋ ውድ ነው፡፡ ኢትዮጵያም አገር አሜሪካም አገር ነው፡፡ የፎቁ ዓይነት ካልሆነ በቀር አየርና ፀሐዩ ሁሉም ጋ ያው ነው፡፡ ሰዎች የተሻለ ለመኖር፣ የምግብ ዓይነት ለመለወጥ እየሞቱ ነው፡፡ ለመኖር መሞት በሥጋ ውስጥ በረከቱ ምንድነው?
ይህች ወጣት “አይሆንም” የሚል ድምፅ ላለመስማት ተጨነቀች፡፡ ሰዎች ተስፋ የሚያሳጣቸውን ድምፅ ላለመስማት እየተጨነቁ ነው፡፡ ዓለም የአይሆንምም ስፍራ መሆኗን መቀበል አልቻሉም፡፡ በተቃራኒው ግን ተስፋ የሞላበትን የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመስማት አይተጉም፡፡ ቢሰሙም ቀኑን ለመርሳት ቃሉን እንደ ሕመም ማስታገሻ ይጠቀሙበታል እንጂ አይፈወሱበትም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሚሠራው በእምነት ነው፡፡ ዘመናዊነቱ ጥግ ላይሆነን ከእግዚአብሔር ለየን፡፡ የጨበጥነው መስሎን ከቤተ እግዚአብሔር የወጣንበትን ነገር እንደገና እየፈለግነው ነው፡፡ ሲጠጉት ይርቃል የዓለም ነገር፡፡ ፍለጋው አያልቅም የምድር እሴት፡፡ እግዚአብሔር ግን የተገኘ፣ የተረጋገጠ ተስፋ ነው፡፡
መሐል መንገድ ላይ ከገባን በኋላ መንገዱ በየት ነው? የምንልበት ግራ መጋባት ገጥሞን ይሆን? ስለ ስህተታችን ከሚዘልፈን ልኩን የሚያሳየን ሽተን ይሆን? እግዚአብሔር ለዛሬው ግራ መጋባታችን መንገድ አለው? የሰማናቸውን የተስፋ መቊረጥ ድምፆች የሚሽር የተስፋ ቃል አለው፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ፡-
“አሁንም ያዕቆብ ሆይ÷ የፈጠረህ÷ እስራኤልም ሆይ÷ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል- ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ÷ አንተ የእኔ ነህ፡፡ በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ÷ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም ነበልባሉም አይፈጅህም” (ኢሳ. 43÷1-2) ብሎናል፡፡ ወገኖቼ! እግዚአብሔር እንዳለው ሰው ተጽናኑ፣ እግዚአብሔር እንዳበረታው ሰው ቁሙ!
-ይቀጥላል-