የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ባለ መታወክ አመሰግንሃለሁ

ሸክም የከበዳቸውን ሸክም ተቀብለህ ፣ እርሱም ሳያንስህ እነርሱን በትከሻህ ላይ አሳፍረህ ፣ በምሕረት ጣቶችህ ፀጉራቸውን እየደባበስህ ኮረብታውን የምታወጣ እግዚአብሔር እንዴት ድንቅ ነህ ! የመድረስ ምኞት ይዞት መንገድ የቀረውን ፣ ልቡ እንደ ናፈቀ የራበውን ያላገኘውን ፣ ሰፊ ቀን ሲጠብቅ ጠባብ ዘመን የገጠመውን ፣ ይሆናል እያለ እንዳይሆን የሆነበትን ፣ ጽድቁን ትቶ በቅጡ መኰነንን የሻተውን ፣ ተወርሶ ድሀ ፣ ተከድቶ ብቸኛ የሆነውን ፣ የእርሱስ ቍስል አይድንም የተባለውን ፣ በጓዳ መክረህ ፣ በቤተ ውበትህ አስውበህ ፣ ሌላ ሰው አድርገህ የምታቆም አማኑኤል እንዴት ዕፁብ ነህ ! የገዛ እናቱ ረሳችውን ፣ የገዛ መምህሩ ያስካደውን ፣ የገዛ አባቱ የካደውን ፣ የገዛ ሰውነቱ የከዳውን ፣ የገዛ ገንዘቡ ጠላት ያመረተበትን ፣ የገዛ ደግነቱ ያስደፈረውን ፣ የገዛ ጥንቃቄው ከአደጋ የጣለውን ያንን ሰው መራራውን የምታጣፍጥለት ኤሎሄ እንዴት ግሩም ነህ !

ኤልሻዳይ ሆይ የጽድቅ ተማሪ አድርገኝ ። እንደ ተመላላሽ ተማሪ ሳይሆን እንደ አዳሪ ደቀ መዝሙር በቀንም በሌሊትም ከፊትህ አትለየኝ ። የመጀመሪያው ቀን ትውስታ አይጠፋምና በመጀመሪያ ቀን ሰውን በፍቅር መቀበልን አድለኝ ። ሰውን እስካውቀው ብዬ ከመኮፈስ በክርስቶስ አውቀዋለሁ ብዬ ትሑት መሆንን ስጠኝ ። ተገቢያቸው ስለሆነ ሳይሆን ስላንተ ፍቅር ለሰዎች ሁሉ የቸርነት ልብ ስጠኝ ። ጉዞው አቀበት ሁኖ ቢታክት ፣ እንቅፋቱ በዝቶ እግሮች ቢቆስሉ ፣ ዓይኖች ቀኑን ማየት አቅቷቸው ዕንባ ቢያረግዙ ፣ ልብ በኀዘን ቢሞላ ፣ የፈሩት ቢደርስ ፣ የጠሉት ለመውረስ ቢቃረብ ፣ እጆች ዘርን ለመዝራት ተስፋ ቢቆርጡ ፣ ጎረቤቶች ፍርሃት ፣ ዘመዶች ጥቅም ተኮር ቢሆኑ ፣ ጓደኞች ተንሸራተው የማያበቁ የተልባ ስፍር ቢሆኑ ፣ ሰማይ ቢከዳ ፣ ምድር ቢናወጥ ፣ የዘሩት ባይበቅል ፣ የሄዱበት በሩ ዝግ ቢሆን ፣ ጉባዔው ቢበተን ፣ ሰልፉ ጀግንነት ቢያጣ ፣ መሪ መንገድ ቢጠፋው ፣ ጋባዥ ለማኝ ቢሆን ፣ ጸሎተኛ ወሬ ቢተነትን ፣ ሰላም ባዩ ቢያኮርፍ ፣ ምስኪኑ ቀን ወጣልኝ ብሎ ቢገፋ ፣ ገበሬው በሞፈር ካልጻፍሁ ብሎ ቢደነፋ ፣ ምሁር ጭቃ ቢያላቁጥ ፣ ጠቢብ ቢደነቁር ፣ ፍረጃ ቢበዛ ፣ ሰውን ሰው ከማለት እገሌ ለማለት አፍ ቢፈታ ፣ ቅዱሳን ቢረክሱ ፣ ካህን እያጠፋ ሌቦች ቢያፍሩ ፣ ትንሽ ነው ያሉት ትልቅ ቢሆን ፣ ትልቁ ቢያንስ ፣ … አንተ ግን አንተ ነህ ። ባለ መታወክ አመሰግንሃለሁ ። አሜን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 27 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ