ለመጠመቅህ ሰላም እላለሁ !
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ! ሁሉ በዮርዳኖስ ቢሰበሰብ በደል አስጨንቆት ነው ፣ አንተ ግን ወደ ዮርዳኖስ የሄድኸው ጽድቅን ልትፈጽም ነው ። ሁሉ ወደ ዮርዳኖስ ቢሄድ በሚበልጠው በዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ ነው ፣ አንተ ግን ወደሚያንስህ ወደ ዮሐንስ ሄድህ ። ሁሉ ወደ ዮርዳኖስ ቢሄድ በደል ተጭኖት ነው ፣ ሲመለስ በዕረፍት ነው ፤ አንተ ግን ዘላለማዊ ቅዱስ ነህ ። ሁሉ ወደ ዮርዳኖስ ቢሄድ ስለ ራሱ በደል ነው ፣ አንተ ግን ስለ ዓለሙ በደል ነው ። በዮርዳኖስ ነገሥታት አልተገኙም ፣ አንተ የነገሥታት ንጉሥ ግን ተገኝተሃል ። ሁሉ ወደ ዮርዳኖስ ቢገሰግስ ዮሐንስን መጥራት ስለማይችል ነው ፣ አንተ ግን ዮሐንስን “መጥተህ አጥምቀኝ” ልትል ሲገባህ የገሰገስህ ነህ ። ሁሉ ወደ ዮርዳኖስ ቢሄድ ጸጋን ሊቀበል ፣ ምሥጢረ ንስሐን ሊፈጽም ነው ፣ አንተ ግን ጸጋን ልትሰጥ ነው ።
ሰው ራሱን ተጸይፎ ከፊቱ ካለው ኃጢአተኛ ጀርባ ተሰልፏል ፣ አንተ ግን በኃጢአተኞች ሰልፍ ውስጥ ማንንም ሳትጸየፍ ቆመሃል ። እስራኤል ዮርዳኖስን መሻገራቸው የነጻነታቸው የመጨረሻ በር ነው ። ጥምቀትንም የጸጋና የቤተ ክርስቲያን በር አድርገህ ልትሰጠን በዮርዳኖስ ተጠምቀሃል ። በዮርዳኖስ ትይዩ ጌልጌላ ይታያል ፣ የግብፅ ነውር የተወገደበት የሸለፈት መቃብር ማዶ ቆሟል ። አንተም የሚጠመቁ ሁሉ ለዓለም ሞተው ፣ ላንተ ይኖሩ ዘንድ ጥምቀትን ባርከሃል ።
በተቀደሰው ጥምቀትህ የባሕርይ ልጅነትህ ተመሰከረ ፣ የእኛም ልጅነት በጥምቀት ይገኛል ። በጥምቀትህ ምሥጢረ ሥላሴ ተገለጠ ፣ እኛም በሥላሴ ስም እንጠመቃለን ። በጥምቀትህ ሰማይ ተከፈተ ፣ እኛም ስንጠመቅ መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን ። በጥምቀትህ ልጅነትህ ተመሰከረ ፣ እኛም በጥምቀት በተቀበልነው መንፈስ ቅዱስ የጸጋ ልጅነታችን ተመስክሮልናል ። ጠላት “እናንተ የተጣላችሁ ናችሁ” ሲለን መንፈስህ ለመንፈሳችን የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ ይለናል ። በጥምቀትህ ትሕትና ተገለጠ ፣ የተጠመቁ ሁሉ ትሑታን ይሆኑ ዘንድ አንተ አዘዝህ ። አንተ ያከበርከውን ጥምቀት እንዳናቃልል ፣ ምሥጢራትን እንዳናሳንስ እርዳን ።
ለተቀደሰው ጥምቀትህ ሰላም እላለሁ !!!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 11 ቀን 2014 ዓ.ም.