የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ድል ለነሣው / ክፍል 5

 የዲያቆን አሸናፊ መኮንን ገጽ ቅዳሜ ግንቦት 15/2007 ዓ.ም.
ባዕድ አምልኮን ድል መንሣት
ከሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን አራተኛዋ ናት። ለትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን ጌታ የተገለጸው፡- “እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች ያሉት በእቶንም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል” በማለት ነው /ራእ. 3፡18/። “እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች ያሉት” ማለት ሁሉን መርማሪ ነው ማለት ነው። በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚከናወነውን ክፉ ነገር ያያል፣ የሚቆጭ ቢጠፋ ይቆጫል፣ የሚታየው መሪ አይቶ እንዳላየ ቢያልፍም የማይታየው ጌታ ግን ምክሩን ይልካል። ጌታ የሚደረገውን መልካምም ሆነ ክፉ ያያል። ቤቱን ለማንም አይተውምና። እንዳየ መጠን ይመክራል እንጂ አይፈርድም። ቢፈርድ እንኳ እየተበቀለ ሳይሆን እንደገና ለንስሐ እየጋበዘ ነው። መዓትም ምሕረትም በእጁ ቢሆኑም እርሱ የሚሻው መማር ነው።
ሌላው መልኩ “በእቶንም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት” የሚል ነው። ይህ ጽኑነቱን የሚገልጥ ነው። ኃያላን የማያሸንፉት ኃያል፣ ጎበዞች የማይጥሉት ጎበዝ፣ አስፈሪዎች የማያስፈሩት ግርማዊ ነው። በዚህ መልኩ ለምን ተገለጠ? ስንል በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ውበትን፣ ሥልጣንን፣ ገንዘብን ታምና አማንያኑን የምታረክሰውን፣ በግብር ስሟ ኤልዛቤል የተባለችውን ሴት ዝም በማለቱ ነው። እኔ ባስፈራህ ኖሮ ማንንም አትፈራም እያለው ነው ለቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ። በመቀጠልም፡- “የእግዚአብሔር ልጅ” ይላል። የእግዚአብሔር ልጅ ማለት የባሕርይ አምላክነቱን የሚገልጥ ነው። ነገሥታት እያሉ ንጉሥ ቢባልም አማልክት ስላሉ ግን አምላክ አልተባለም። እርሱ ከማንም ጋር የማይወዳደር አምላክ ነው። ለማንም የአምላክነት እውቅና አይሰጥም። ስለዚህ የትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን መሪ ከበላዩ ያለው ትልቁ ጌታ መሆኑን ማወቅ አለበት።
የትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን ፈተና የሆነችባት አንዲት በግብር ስሟ ኤልዛቤል የተሰኘች ሴት ናት። የብሉይ ኪዳኗ ኤልዛቤል የእስራኤል ንጉሥ አክዓብን አግብታ ለጣዖት ያሰገደችው፣ ለእስራኤልም በጣዖት መውደቅ ምክንያት የሆነች ሴት ናት /1ነገሥ. 16፡31/። በትያጥሮን ቤተ ክርስቲያንም አማንያኑን ዝሙትን የምታደፋፍር ለጣኦት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምር ሴት ነበረች። ዝሙትና ጣኦት አምልኮ ሁለቱም ተመሳሳይ ናቸው። ቃል ኪዳንን መጣል የሚያመለክቱ ናቸው። በዝሙት ምክንያት በትዳሩ ላይ ሌላ ነገር ይደርባል፣ በጣኦት ምክንያትም በአምላኩ ላይ ሌላ ይደርባል። አመንዝራው ከቤቱ ላይወጣ ሚስቱን በአዋጅ ላይፈታ ይችላል። ልቡ ደጅ ሆኖ አካሉ ብቻ እቤት ተቀምጧል። ጣኦት አምላኪም በቤተ ክርስቲያን እየኖረ ልቡ ግን የሚገዛው ለሌላ ነገር ነው። በዚህች ሴት ድፍረት አስተማሪነት የትያጥሮን አማንያን ከቤታቸው እስከ አምልኮአቸው የተፈቱ ሆነዋል።

የትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን መሪ ሥራውን በትጋት የፈጸመ፣ ፍቅሩ ብዙዎችን የገዛ፣ እምነቱ የደከሙትን ያበረታ፣ አገልግሎቱ ብዙዎችን ያስመለጠ፣ ትዕግሥቱ ለብዙዎች መመለስ የረዳ ነው /ራእ. 3፡19/። ይህ ሁሉ ያለው መሪ ግን አንዲትን ሴት መገሰጽ የማይችል የይሉኝታ ሰው ሆኖ ነበር። በአንድ በጥባጭ ወይፈን በረት ሙሉ መንጋ እንደሚታመስ እንዲሁ በዚህች ሴት ብዙዎች በዝሙትና በጣኦት አምልኮ ወድቀው ነበር። ስለዚህ አገልግሎቱ በቀዳዳ ስልቻ እንደ መሙላት፣ በበር እያስቡ በጓሮ እንደ ማስወጣት ሆኖ ነበር።
ትልቁን ባለሥልጣን ኢየሱስ ክርስቶስን ተማምኖ መገሰጽ አለበት። በርግጥ የብሉይ ኪዳኗን ኤልዛቤል በመገሰጽ ምክንያት ኤልያስ ለስደት ተዳርጓል /1ኛ ነገሥ. 19፡1-3። ብዙ ነቢያትም ለረሀብ ተጋልጠዋል። የትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን መሪም ይህ ፈተና ቢገጥመውም ለዓላማው መጽናት ያስፈልገዋል። እርሱ ሥጋዊ መከራ በመፍራቱ ሌሎች በነፍስ መከራ ውስጥ እየወደቁ ነው። ለመምከርም ሥልጣን ያለው እርሱ ነው። ሳይናገር ባትሰማኝስ ማለት አይገባውም። በፍቅር ምክር ይህችን ሴትና ያሳተቻቸውን መመለስ አለበት።
ይህንን ድርሻ ቢወጣ የተዘጋጀለት በረከት፣ የድል ነሺነት ክብር አለ፡- “ድል ለነሣውና እስከ መጨረሻውም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደ ተቀበልሁ በአሕዛብም ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፣ በብረትም በትር ይገዛቸዋል፣ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቅጣሉ፤ የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ” /ራእ. 3፡26/። ይህ ሽልማት ጌታ ራሱ የተቀዳጀው ነው /መዝ. 2፡8-9/። ድል መንሣት ማለት እስከ መጨረሻው ጌታ የሚሠራውን መጠበቅ ነው። ደክሞ ከመንገድ አለመውጣት፣ ክፉ አሸነፈ ብሎ ለምርኮ እጅን አለመስጠት ነው። ለጊዜው እግዚአብሔር ዝም ሲል ጠላት ያሸነፈ ይመስላል። ለጠበቁት ግን የማታው ድል የጌታ ነው። ድል ለነሡ የተዘጋጀው ፍጹም የሆነ ገዢነት ነው። በአሕዛብ ላይ ማስፈራትን መጎናጸፍ ነው። ሌላው የንጋት ኮከብ እሰጠዋለሁ ይላል። የጨለማን መሸነፍ የሚያረጋግጥ፣ ጎልቶ የሚታይ ድምቀትና ምሳሌነት ነው።
 ራስና እግር ቦታ ከተለዋወጡ መራመድ የለም። ሁሉም ቦታውን ሲይዝ ብቻ ሕይወት ቀጣይነት አገልግሎትም ስምረት ይኖረዋል። በቤተ ክርስቲያን ስፍራን አለመያዝና ጸጋን ያለመለየት ችግር ይታያል። ይህ ብቻ አይደለም ሰዎች በዓለም ትልቅ የሆኑበትን ነገር ይዘው በመምጣት በቤተ ክርስቲያንም የበላይ መሆን ይፈልጋሉ። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የጸጋ የበላይነት የሌለባት በሥጋ ክንድ ያሸነፈና ደፋር የሚሆንባት ስፍራ ሆናለች። በትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን ራሷን የቀባች ይህች ሴት ለብዙዎች የድፍረት ኃጢአት ምክንያት እንደሆነች እንዲሁ ዛሬም ጳጳስ የሚያዋርዱ፣ የቤተ ክርስቲያንን ቁልፍ እየተቀበሉ ቄስ የሚያባርሩ ደፋሮችን እያመረትን ይሆን? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን።
ባዕድ አምልኮን ድል መንሣት አለብን። ባዕድ አምልኮ የምንለው ከእግዚአብሔር ውጭ ያለው ትምክሕታችን፣ የሚታየውና የማይታየው ጣኦት ነው። በዛሬው ዘመን ሰው የአንድ ትምክሕት ባለቤት መሆን ይፈልጋል። በእውቀቱ ወይም በሀብቱ ለመኩራት ይከጅላል። ትምክሕትን ድል መንሣት ወደ እግዚአብሔር ያስጠጋል። ይህን ድል የነሡ ከክርስቶስ ጋር ይከብራሉ።
ይቀጥላል 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ