የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቤቱስ ያምራል

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሰኞ ግንቦት 3/2007 ዓ.ም.

 
        ዲዮጋን የተባለ የግሪክ ፈላስፋ በመንገድ ሲሄድ አንድ ቆንጆ ሰው ነገር ግን ባለጌ የሆነ ሰው አየና፡- “ቤቱስ ያምራል ያደረበት ግን የማይረባ ነው” አለ ይባላል። የላኛው አካል ገላ ይባላል፣ ገል አፈር ማለት ነው። እኛ በተለምዶ ሰውነት እንለዋለን። “ነት” የሚለው ማሰሪያ መሆንን የሚያመለክት፣ በተጠቀሰው መገለጫ መገኘትን የሚያሳይ ነው። ሰውነት ሰው መሆን፣ በሰው ክብርና ጸጋ መገለጥ ማለት ነው። ገላን ሰውነት ስለምንል ሰውነት የሚያሟላውን ፍቅርን፣ ትሕትናን፣ ደግነትን፣ ታማኝነትን እንዘነጋለን። ገላችን የውስጥ ሰውነታችን ማደሪያ ነው። የላኛው አካላችን የውስጠኛው ማንነታችን አገልጋይ ነው። የራሱ ሆነ ጽድቅና ኩነኔ የለውም። የውስጣችን ጉዳይ አስፈጻሚ ነው። ጉዳይ ሲያስፈጽምም ለምን? ሳይል ነው።
 
      ዲዮጋን ውስጣዊ ሰውነትን የሚፈልግ ነው። የላኛው ቁመና የማይማርከው ሰው ነው። ነቢዩ ሳሙኤል ሳይቀር በመልክ ማማርና በቁመት ዘለግታ ተታሏል /1ሳሙ. 16./። የመልክ ማማር ለልብ ማማር ዋስትና አይሆንም። እንደ ላዩ ውስጥ ቢያምር ዓለማችን የጻድቃን መንደር በሆነች ነበር።
 
       አንድ  ቀይ፣ ቁመናው ያማረ፣ ነገር ግን ሌባ የሆነ ሰው ይሰርቅና ይሮጣል። ሴትዬዋ “ያዙልኝ” ስትል ፖሊስ አገኘች። ያ ሌባ ከጓደኞቹ መካከል ገብቶ ጨዋታ ቀጠለ። እርሷም መጣችና፡- “እዚህ ነው ያለው” በማለት ለፖሊስ ጠቆመች። ፖሊሱም፡- “የትኛው ነው?” ሲላት ደህነኛ የሆነውን ጥቁር ወጣት “እርሱ ራሱ ነው የሰረቀኝ” ብላ ይዛው መጮህ ጀመረች። ልጁ ስለለመደው በሳቅ ወደቀ። አዎ ቀይ ሌባ ተቀምጦ ጥቁር ደህነኛ ይያዛል። መልካቸውን ያሳመሩ ልብስና ሽቱአቸውን ያስተካከሉ ሁሉን በር የሚያስከፍቱ” ደረታም ሌቦችን እናያለን። ባለጠጋ ሲያገኙ የሚያረግዱ የሚያለቅሱ፣ ድሃ ሲያገኙ እንደ ቡል ዶዘር ጥሼ ልልፍ የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ዓለም የሚፈርደው በላይ ቁመና ነው። እግዚአብሔር ግን ውስጥን ያያል።
     
      ብዙ ያማሩ ሠርጎች ያማረ ኑሮ የላቸውም። ሠርግ ገንዘብን ማውጣት ነው፣ ትዳር ግን ራስን መስጠት ነው። ራሱን ለሰሰተ ትዳር ሕይወት መሆኑ ቀርቶ ትግል ነው።
      
      ብዙ ያማሩ ቤቶች ያማረ ሰላም የላቸውም። ለማኙ የባለጠጎቹን ቤት አልፎ ድሃዋ በር ላይ ቆሞ ይለምናል። ድሃዋ በንዴት ወጥታ፡- “ትልልቁን ቤት አልፈህ እኔ በር ላይ የምትለምነው ለምንድነው?” አለችው። ለማኙ ግን፡- “አይ እሜቴ ትልቁ ቤት ትልቅ ሰው የለበትም” አላት ይባላል። ቤቱ ያምራል፣ ያደረበት ግን…
 
    የዓለማችን የሰለጠኑ ከተሞች፣ ያደጉ አገሮች ትውልድ በውስጣቸው የሚፈርስባቸው ናቸው። ያማሩ ከተሞች ያማሩ ትውልዶች መገኛ አልሆኑም። የተለወጠን አገር ያልተለወጠ ትውልድ ያፈርሰዋል፣ የፈረሰን አገር ግን የተለወጠ ትውልድ ይገነባዋል። ከተሞቹ ያምራሉ፣ ያማረ ትውልድ ግን ያገኙ ይሆን?
 
     እኛስ ለልብሳችን እየተጨነቅን ለቅንነታችን ቸልተኛ ሆነን ይሆን? ልብሳችን የተተኮሰ ንግግራችን ግን የተበላሸ ይሆን? ቁመናችን ያማረ እምነታችን ያነሰ ይሆን? ሽቶአችን የሚያውድ ጥላቻችን የሚገፈትር ይሆን? እባክህ ጌታ ሆይ አንተ የመረጥከው ዓይነት ሰው አድርገህ ሥራን። አሜን። 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ