የትምህርቱ ርዕስ | ዳግም ልደት

“በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን ።” ኤፌ. 1 ፡ 5 ።

በበጎ ፈቃዱ ብሎ እግዚአብሔር አብን ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ብሎ እግዚአብሔር ወልድን ፣ ልጆቹ ልንሆን ብሎ ዳግም የሚወልደንን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን አነሣ ። መዳናችን ሥላሴያዊ መሆኑን መዘንጋት አይገባንም ። “ኢየሱስ ብቻ” የሚል ትምህርት የሰባልዮሳውያን ኑፋቄ እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ። በበጎ ፈቃዱ የሚለውን ለማየት እንሞክር ። እግዚአብሔር ፈቃድ ያለው አምላክ ነው ። ይህም አካላዊነቱን ያስረዳናል ። እርሱ ሰውን በመልኩ በመፍጠሩ የሰው ልጅም ፈቃድ ያለው ፍጡር ነው ። በዚህ ክፍል ላይ የተጠቀሰው ፈቃድ ነጻነት ተብሎ የሚተረጎመው ፈቃድ አይደለም ። የተግባር ዋዜማ የሆነው ፈቃድ ነው ። በሌላ አገላለጽ ቁርጥ አሳብ ማለት ነው ። በአሳቡና በተግባሩ መካከል የጊዜ ርዝመት እንጂ መለያየት የሌለበት ፣ የሆነ ያህል የሚቆጠር ነው ። እግዚአብሔር አሰበ ስንል አደረገ ማለታችን ነው ። በእግዚአብሔር ፈቃድና ተግባር መካከል የሚያሰጋ አዲስ አሳብ ሊመጣ አይችልም ። ፈቃደ ሥላሴን በሚመለከት ሦስት ነገሮች ጉልህ ሁነው ይታያሉ ። በፈቃዱ እኛን ለመፍጠር ፣ ለማዳንና ልጆቹ ለማድረግ ወሰነ ። እግዚአብሔር የወሰነው እኛን ለማራቅ ሳይሆን ልጆቹ ለማድረግ ነው ። እርሱ ደግሞ የወደደው ሰውን እንጂ እነ እገሌን አይደለም ።

ብዙ ወላጆች ልጃቸውን በሚመለከት ሲናገሩ በስህተት በወጣትነት ዝላይ የወለድሁት ነው ይላሉ ። እግዚአብሔር ግን በፈቃዱና በውሳኔው እንጂ በስህተት አልወለደንም ። እርሱ ልጆቹ ካደረገን እርሱ አባታችንም እናታችንም ነው ። እርሱ ልጆቹ ካደረገን እኛን ለመውለድ በመስቀል ምጥ አልፏል ማለት ነው ።

በሰው ነፍስ ውስጥ አሳብ ፣ እውቀት ፣ ስሜት / መነቃቃት ፣ ፈቃድ ወይም ውሳኔ የሚባሉ ነገሮች አሉ ። ነፍስ ብዙ ክፍልፋይ ያላትና እስካሁን ድረስ ተጠንታ ያልተደረሰባት ናት ። ሰውን ሙሉ አካሉን ብንጨብጠው አወቅነው ማለት አይደለም ። ሰው ከዓለም ይልቅ የሚሰፋ ፍጡር ነው ። ይህ ስፋት ያለው በነፍሱ ውስጥ ነው ። በሥጋው እዚህ ይታያል ፣ በአሳቡ ግን ዳርቻዎችን ያስሳል ። ሰው ሰፊ ፍጡር ነው ። አሳብ የነገሮች ሁሉ ፅንሰት ነው ። ይህ ዓለም እንኳ የተበጀው አስቀድሞ አሳብ መጥቶ ነው ። አሳብ ከቀደመ መንገደኛ ፍጡር የለም ። ግብ ያለው ፍጡር ግን አለ ። አሳብ የእውቀት መገኛ ነው ። ማሰብ ሰውን ከእንስሳ የሚለየው ነው ። ሰውን ሰው የሚያሰኘው ቅርጹ ሳይሆን አሳቡ ነው ። በቅርጽ ከሆነ እኛን በጥቂት የሚመስሉ እንስሳትም አሉ ። ማሰብ ነጻነት ይፈልጋል ። ነጻነት ከሌለ ማሰብ ፣ ማሰብ ከሌለ እውቀት ሊኖር አይችልም ። እውነተኛ ነጻነትም የመሳደብ ሳይሆን የማሰብ መብት ነው ። የአሳብ ነጻነት ከሌለ እውቀትና ምርምር ሊኖር አገርም ሊያድግ አይችልም ። የአፍሪካ መሪዎች እንኳን ተናግሮ አስበህ ነበር በማለት ሰውን ያንገላታሉ ። ራሳቸውን እንደ አማልክት ስለቆጠሩ ሰው የሚያስበውንም ያውቃሉ ። በአገራችንም እያንዳንዱ ሰው የአሳብ ጨቋኝ ይመስላል ። አሳብ እንደ ጠላት እንድንተያይ ፣ ጦር እንድንማዘዝ ያደርገናል ። አሳብ በአሳብ እንደሚሸነፍ ማመን ይቀረናል ። ሰው የወደደውን እንዲያምንና እንዲከተል እንፈቅዳለን ወይ  ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። የአሳብ ጨቋኝ ከሆንን በአገራችን ላይ ከመቶ ሚሊየን በላይ አምባገነን አለቆች አለን ማለት ነው ።

ከአሳብ ቀጥሎ እውቀት ይመጣል ። እውቀት ጫፉ የተጨበጠ እንጂ ያለቀ ማለት አይደለም ። እውቀትን የጀመራት እንጂ የጨረሳት የለም ። ከምናውቀው የማናውቀው ይበዛል ። የምንማረውም አለማወቃችንን አውቀን ትሑት እንድንሆን ነው ። አላዋቂ ደፋር ነውና ከዚያ ለመዳን መማር ያስፈልገናል ። እውቀት ሰው ነፍሱን ከዝገት የሚጠብቅበት ትልቅ እንቅስቃሴና ዘይት ነው ። ዝገትን ለመከላከል መንቀሳቀስና ዘይት አስፈላጊ ነው ። ዝገት አንድ ነገር ለተፈጠረበት ነገር ባለመዋሉ የሚመጣ ድርቀት ነው ። ለተፈጠሩበት ነገር መኖር ዕድሜን ያረዝማል ። መኪና ለመሄድ ስለተሠራ በተጓዘ ቍጥር ዕድሜው ይረዝማል ። እውቀት ጠል የሆነ ማንነት ውስጥ ያለ ሰው ስለሚዝግ ሰውን ይመርዛል ፣ ቀጥሎ ራሱ ይጠፋል ። እውቀት ጠል የሆኑ ሰዎች አጥፍቶ ጠፊዎች ናቸው ። ይሉኝታ ስለሌላቸው አውርተው አያባሩም ። ትምህርት ቤቶች እውቀትን የምናገኝባቸው መስኮች ናቸው እንጂ ብቸኛ መንገዶች አይደሉም ። ለሚማር ሰው ሁሉ ቦታ ፣ ሁልጊዜ ትምህርት አለ ። ከአሳብ ቀጥሎ እውቀት የነፍስ ጓዳ ነው ።

ስሜት ለአሳብና ለእውቀት ያለን መነቃቃት ፣ ጉዞ ለማስጀመር ሞተር ማስነሣት ፣ መቀጣጠል መንደድና መሞቅ ነው ። ስሜት ውስጥ ኃይል አለ ። በአሳብና በእውቀት ያልተደገፈ ስሜት ግን አደጋ አለው ። ያለ ሙቀትና ያለ እልህ ሥራ መሥራት አይቻልም ። መንፈሳዊ ቅንዓት አስፈላጊ ነው ። ቀዝቃዛነት ካልተወገደ ፣ ግለት ካልመጣ ራእይ ሊኖር አይችልም ። ስሜታዊ አንሁን እንጂ በስሜት የእግዚአብሔርን ሥራ መሥራት ይገባናል ። እግዚአብሔር ስሜታቸው ቶሎ በሚነካ ውስጣዊ ሙቀት ባላቸው ፣ ተነሣሽ ሰዎች ይደሰታል ። ቅዱስ ጴጥሮስን የመረጠው በብቃቱ ሳይሆን ቶሎ የሚነካ ውስጣዊ ሙቀት ያለው ስለነበረ ነው ። እግዚአብሔር መንፈሰ ቀዝቃዞችን አይወድም ። ውስጣዊ እሳት ከሌለ ከመሞታችን በፊት ሙተናል ማለት ነው ።

ከስሜት ቀጥሎ የምናገኘው ፈቃድን ነው ። ፈቃድ ቁርጥ አሳብ ፣ ወደ ተግባር ለመግባት አንድ እግርን ማንሣት ነው ። እግዚአብሔር በበጎ ፈቃዱ ሊፈጥረን ፣ ሊያድነንና ልጆቹ ሊያደርገን ፈቀደ ። ሰውን እንደገና የወለደ አባት እግዚአብሔር ብቻ ነው ።

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /10

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 11 ቀን 2014 ዓ.ም.

እባካችሁ ለሌሎች አካፍሉት

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም