የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ትንሣኤን በትንሣኤ


የዲያቆን አሸናፊ መንን ገጽ ——  ማክሰኞ ሚያዝያ ፮/፳፻፯ ዓ.ም
በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት አንድ እንግሊዛዊ ዜግነት ያለው ኡጋዴን ላይ ተገደለ፡፡ በዚህ ጊዜ የእንግሊዝ መንግሥት ቆንሲል ወደ ጃንሆይ ቀርቦ፡- “በግዛታችሁ ዜጋችን ተገድሏል፣ አንድ የእንግሊዝ ዜጋ የሞተበት ስፍራ በእንግሊዝ ሕግ መሠረት የእንግሊዝ ግዛት ነው…” አላቸው፡፡ እርሳቸውም ይህን ጉዳይ ፊታውራሪ  ሀብተ ጊዮርጊስ ይመልከተው አሉ፡፡ ጉዳዩም ለፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ በቀረበ ጊዜ ተንኲል ያለበት ነገር መሆኑን ስለ ተረዱ ከሦስት ቀን በኋላ ቀጠሩት፡፡ በሦስተኛው ቀን፡-  “በሕጋችሁ መሠረት አንድ እንግሊዛዊ የሞተበት ስፍራ የእንግሊዝ መሬት ነው?” አሉት፡፡ ቆንሲሉም፡- “ትክክል ነው”  አላቸው፡፡ እርሳቸውም፡- “በሕጋችሁ መሠረት እኛ ኡጋዴንን እንሰጣለን፤ እኛም ለንደን ላይ ሰው ሞቶብናል ያውም የንጉሥ ልጅ ስለዚህ ለንደን ይገባችኋል ብለህ ፈርምልን” አሉት፡፡ ቆንሲሉም ደንግጦ ሄደ፡፡ ለንደን ላይ የዐፄ ቴዎድሮስ ልጅ አለማየሁ ቴዎድሮስ ሞቷል፡፡
ይህንን ታሪክ ያነሣነው ቀራንዮ ላይ የንጉሥ ልጅ ኢየሱስ ሞቷልና መንግሥተ ሰማያት ይገባናል ለማለት ነው፡፡ ተሰዶ በባዕድ ምድር ገና በወጣትነት ዘመኑ የሞተው የንጉሥ ልጅ ሁልጊዜ ይቆጨናል፡፡ ከዙፋን ተሰዶ፣ በፈጠረው ተገፍቶ በመስቀል የሞተው የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትም ሊሰማን ይገባል፡፡ ሕይወት ሊያቀምሰን አፈር የቀመሰው አወይ የወልድ ፍቅር ምንኛ ድንቅ ነው! ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳሳሰበን የምትወዱት አልቅሱለት!  
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድምናው የአብ ልጅነቱን፣ በነቢያቱ ባናገረው ትንቢት የተስፋ አምላክነቱን፣ ከድንግል በመወለዱ ሰውን ምንኛ ማክበሩን፣ በበረት በመጣሉ ጽናት ያለው ፍለጋውን፣  በግብፅ ስደቱ የስደተኞች መጠጊያነቱን፣ በድህነት ኑሮው የምስኪኖች ሞገስነቱን፣ በመታዘዙ የወላጅ ክብርን፣ በመጠመቁ ከኃጢአተኞች ጋር መቆጠሩን፣ በመጾሙ ክፉ ፍትወትን ድል መንሣቱን፣ በመስበኩ ከሣቴ ብርሃንነቱን /ብርሃን ገላጭነቱን/፣ ደቀ መዛሙርትን በመላኩ ዓለሙን ሁሉ ሊያናግር መፈለጉን፣ በጌቴሴማኒ ጸሎቱ የኃጢአት አስከፊነትን፣ በጲላጦስ ፊት በመቆሙ ለተገፉት መጽናኛነቱን፣ በሊቀ ካህኑ ፊት በመቆሙ ከቤቱ መሰደዱን፣ መስቀል በመሸከሙ የቀንበራችን ሰባሪነቱን፣ በመሞቱ በእኛ ስፍራ መቆሙን፣ በመነሣቱ በእርሱ ስፍራ እኛን ማቆሙን፣ በማረጉ ልዕልናውን፣ በአብ ቀኝ በመቀመጡ የቤዛነቱ ስምረትን፣ ዳግመኛ በመምጣቱ ዋጋ ከፋይነቱን ያሳየናል፡፡ 


ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ያዳነው በከፍታው ሳይሆን በዝቅታው፣ በሕይወቱ ሳይሆን በሞቱ ነው፡፡ ይህ ሁለት ነገሮችን ያሳየናል፡፡ የመጀመሪያው ጠላትን መናቁን ነው፡፡ በዝቅታና በሞቱ በማሸነፍ የሰይጣንን ልኩን አሳየው፡፡ ላንተ ዙፋኔ ሳይሆን በረት፣ ሥልጣኔ ሳይሆን ሞቴ ይበቃሃል ያለው ይመስላል፡፡ በአምላካዊ ልዕልናው መዳንን ቢፈጽም ኖሮ፡- “አምላክ ነውና ይችላል፣ የገዛ ፍርዱን ነው ያነሣው” በማለት ሰይጣን በተዘባበተ ነበር፡፡ በማይመረመር ጥበብ ሰው በመሆን፣ በማይነገር ፍቅር በመሞት መዳንን ፈጸመ፡፡ የጌታችን ሞት በሁለተኛ ደረጃ እኛን በማይለካ ፍቅር መውደዱን ያሳያል፡፡ በልዕልናው ሆኖ ቢያድነን ሁሉን ቻይ እንለው ነበር፡፡ በማይነገር ፍቅር አዳነን የምንለው ግን ስለ እኛ በመዋረዱ ነው፡፡ አዎ በጌታችን ሞት ሰይጣን ሐፍረት ለበሰ፣ እኛ የክብር ካባን ተጐናጸፍን!
እግዚአብሔር የተአምራት አምላክ ነው፡፡ ያለ ተአምራቱ የዋለች ቀን የለችም፡፡ ይህች ቀንም የእርሱ ተአምር ናት፡፡ እግዚአብሔር ካደረገልን ነገሮች ሁሉ የበጎነቱ ጉልላት ብለን የምንጠራው አንድ ልጁን ስለ እኛ ኃጢአት መስጠቱ ነው፡፡ ስለ እኛ በመስቀል ላይ መዋሉ የአድራጎቶች ሁሉ አድራጎት፣ ተካካይ የሌለው መልካምነት ነው፡፡ እርሱም የሚለን ያወጣሁላችሁን ፀሐይ አያችሁን ሳይሆን ፍቅሬን አስተዋላችሁን? ነው፡፡ የፍቅሬ መለኪያ የዕለት እንጀራ ሳይሆን የቆረስኩት ሥጋዬ፣ ያፈሰስኩት ደሜ ነው ይለናል፡፡ ሚሊዮን ዓመት ብንኖር ሚሊዮን ጊዜ ቢደረግልን ከተደረገልን አይበልጥም፡፡ የተደረገልን መዳናችን ነው፡፡
የጌታችን ሞት እግዚአብሔር በእኛ ስፍራ የቆመበት ነው፡፡ ማለት ሞታችንን የሞተበት፣ ስለ እኛ ቤዛ፣ ዋስ፣ ምትክ የሆነበት ነው፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ግን እኛ በክርስቶስ ቦታ የቆምንበት ስለ እርሱ ቅዱሳን፣ ጻድቃን፣ ምእመናን /አማኞች/፣ ወልደ ትንሣኤ፣ ወለተ ትንሣኤ ተብለን የተጠራንበት ነው፡፡ የእኛ ቦታ የሚያምር አይደለም፡፡ የእኛ ቀራንዮ የስቃይ ቦታ፣ የኃጢአት ዋጋ የሚከፈልበት ነው፡፡ አንዳንድ ከእውነት የኰበለሉ፣ ከሥነ ምግባር የወደቁ ልጆችን ፍለጋ ወላጆች በማይመጥናቸው ስፍራ ይገኛሉ፡፡ እነርሱ እዚያ ድረስ ካልሄዱ ልጆቹ እንደማይመጡ ከልምድ ስላረጋገጡ ነው፡፡ ልጆቹ ያሉበት ስፍራ የተሻለ ይመስላቸዋል፣ ወይም ለመውጣት አቅም ያንሣቸዋል፡፡ ወላጆቻቸውን ባዩ ጊዜ ቢቆጡም ቢያፍሩም ስሜታቸው አንድ ነው “እኔ አልድንም ተዉኝ” የሚል ነው፡፡ እኔ አልድንም የምንለውን ካለንበት ድረስ መጥቶ አዳነን፡፡ የነበርንበት ሲኦል ነበር፡፡ እኛ ካለንበት ካልመጣ እርሱ ካለበት መውጣት አይቻለንም፡፡ ታዲያ እነዚያን አጥፊ ልጆች እያባበሉ ጫት የሚያስቅሙ፣ መጠጥ የሚያጠጡ የሚፈልጋቸው ወላጅ እንዳለ ሲያዩ፣ ከዚያ ስፍራ እጃቸውን ይዘው ሲያወጧቸው ሲያዩ በሐፍረት ዝም ብለው ይመለከታሉ፡፡ ጌታም እኛን ባዳነበት ቀን ሰይጣን አፍሯል፡፡
 
የእርሱ ቦታ ትንሣኤ፣ የማነ አብ /የአብ ቀኝ/ ነው፡፡ ካለበት ሊያወጣን ካለንበት መጣ፡፡ ወደ ላይ ከፍ ሊያደርገን ወደ መቃብር ወረደ፡፡ የማይገባንን ሕይወት ሊሰጠን የማይገባውን ሞት ተቀበለ፡፡ በዚህ ስፍራ ላይ መቆም በፍጹም አንችልም፡፡ የሚከብደው ግን እኛ ስለ ኢየሱስ ጻድቃን መሆናችን ሳይሆን ኢየሱስ ስለ እኛ ኃጥእ መባሉ ነው፡፡ የማይሞተው የሞተው የማንድነው እንድንድንና ሚዛኑ እንዲስተካከል ነው፡፡
የክርስቶስ ሞቱ ሰውነቱን፣ ትንሣኤው አምላክነቱን ያስረዳናል፡፡ መለኮት በሚሞት ሥጋ ስለእኛ ሞተ፡፡ ሥጋ በማይሞተው መለኮት ከሞት ተነሣ፡፡ ቃል ሥጋ በሆነ ጊዜ የወሰደው የሥጋን ድህነትና ሞት ነው፡፡ ሞቱ ሰውነቱን፣ ትንሣኤው አምላክነቱን ያስረዳል፡፡ የሞተው ሰው ብቻ ቢሆን ዓለም አይድንም ነበር፡፡ ምክንያቱም መዳን በፍጡር አይሆንምና፡፡ ደግሞም ፍጡር አዳነን ብለን ብናምን ርጉማን እንሆናለን፡፡ ጌታ መለኮት ብቻ ቢሆንም ስለ እኛ በመሞት ቤዛ ሊሆንልን አይችልም ነበር፡፡ ምክንያቱም መለኮት በባሕርይው አይሞትምና፡፡ አባቶቻችን እንዲህ ብለዋል፡-
“የሕይወታችን መገኛ የሚሆን የክርስቶስ ሞት የእኛን ሞት ወደ ትንሣኤ እንደለወጠ እናምናለን፤ ክርስቶስም ሞትን አጥፍቶ የማታልፍ ትንሣኤን ገለጠ እንደ ተጻፈ /ሐዋ . 3÷15፤4÷12 ፤ ዕብ. 2÷8-17/፡፡
ከሰውም ወገን ማንም ምን ሞትን ያጠፋ ዘንድ፤ ትንሣኤንም ይገልጣት ዘንድ አይችልምና፡፡ ዳዊት በሕያውነት የሚኖር ሞትንም የማያያት ሰው ማነው? ነፍሱን ከሲኦል፤ ሥጋውን ከመቃብር  የሚያድን ማነው? ብሎ እንደ ተናገረ /መዝ. 88÷ 48/፡፡
ራሱን ማዳን ያልተቻለው ሌላውን ማዳን እንደምን ይችላል? አንድ ራሱን ሊያድን ያልቻለስ ዓለምን ሁሉ ሊያድን እንደምን ይችላል …” /ሃይማኖተ አበው ዘአቡሊዲስ ቁ. 6-9 /፡፡
ጌታችን ስለ ኃጢአት ሞቶ ነገር ግን ባይነሣ ኖሮ ስላለፈው ኃጢአት ዋጋ እንደከፈለ ብቻ እናስብ ነበር፡፡ በመነሣቱ ግን ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ ሕያዋን አደረገን… ለኃጢአት መሞት ብቻውን በቂ አይደለም፣ ለጽድቅም መነሣት ያስፈልጋል፡፡ የጌታችን ትንሣኤ የጽድቅ ኃይል፣ የቅድስና ሞተር፣ የመታዘዝ ጉልበት ነው፡፡
ጌታችን የሞተው በዓሉን እንድናከብር አይደለም፣ እርሱን እንድናከብረው ነው፡፡ ሕይወቱን ሰጥቶናል፡፡ ከሕይወታችን ያነሰውን ልንሰጠው አይገባም፡፡ ትንሣኤን በኃጢአት፣ በመጠጥና በዘፈን ማክበር በውድቀት ማክበር ነው፡፡ ይልቁንም በጌታ ስም ኃጢአት መሥራት የበደል በደል ነው፡፡ ትንሣኤን በትንሣኤ ማክበር ይገባል፡፡ ትንሣኤው የደፈረሰውን ፍቅር የምናድስበት፣ ንስሐ ያለበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ትንሣኤን በትንሣኤ!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ