መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ለማዳን የሚለምን አገልጋይ

የትምህርቱ ርዕስ | ለማዳን የሚለምን አገልጋይ

  

 

 

“በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤” ኤፌ. 4፡1 ።

 

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እለምናችኋለሁ” በሚለው ንግግሩ የሚገልጣቸው አራት ነገሮች አሉ ። የራሱን ትሑት ሰብእና ፣ የሰዎችን ነጻ ፈቃድ ፣ የንግግር ጥበብን ፣ የወንጌል ጠባይን ይገልጣል  ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እጅግ ትሑት ነበረ ። ትሕትናውን በማየት በዚህ ዘመን ያለነው ክርስቲያኖች ራሳችንን መመዘን እንችላለን ። ቅዱስ ጳውሎስ የክርስቶስ ባሪያ ነኝ ይላል ፣ እኛ ደግሞ የንጉሥ ልጆች ነን እንላለን ። እርሱ ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል ? ይላል ፣ እኛ ደግሞ እምቅ ኃይል አለኝ እንላለን ። እርሱ ድንኳን እየሰፋ ለድሆች ይሰጥ ነበር ፣ እኛ ድንኳን ከሚሰፉት እንዘርፋለን ። እርሱ ደመወዙን ትቷል ፣ እኛ ስለ ቦነስ እንጣላለን ። እርሱ በድንግልና ሕይወት ኖሯል ፣ እኛ በአንድ መርጋት አቅቶናል ። እርሱ ስለ ምእመናን መጽናት ምጥ ይዞታል ፣ እኛ ስለምናገኘው ጥቅም አሳብ ይዞናል ። እርሱ ጸልዩልኝ ይላል ፣ እኛ ሁሉን ጨብጫለሁ ብለን እናስባለን ። እርሱ በሰንሰለቱ ይኮራል ፣ እኛ በወርቅ ቀለበት እንደሰታለን ። እርሱ እለምናችኋለሁ ይላል ፣ እኛ ደግሞ “እነግርሃለሁ ስማ” እንላለን ። ጸጋ እንዳለን ምልክቱ ፣ ጸጋ ካነሰንም እንዲበዛልን መስፈርቱ ትሕትና ነው ። ሐዋርያው እስረኛ ነውና ብስጩ ቢሆን ያምርበታል ፣ እርሱ ግን በትሕትና “እለምናችኋለሁ” ይላል ። 

 

“እለምናችኋለሁ” የሚለው ንግግሩ የሰዎችን ነጻ ፈቃድ ያከብራል ። ሰው እንደ ኮምፒዩተር ፕሮግራም የሚጫንበት ፍጡር አይደለም ። ነጻ ፈቃድን ስናከብር ለሰው ነጻ ፈቃድ የሰጠውን እግዚአብሔር እየሰበክን ነው ። ነጻ ፈቃድን ማወቅ የሰዎችን ክብር እንድንጠብቅ ያደርገናል ። በእልህና በቍጣ ፣ ሌሎች የሚያምኑትን በመንቀፍ ሳይሆን በማዳን ስሜት እንድንናገር ያደርገናል ። በሰው ሃይማኖትና አስተሳሰብ ዘው እያልን መግባት ፣ የእኔ ትክክል ነው ለማለት እገሌ ተሳስቷል ብሎ መጀመር ነጻ ፈቃድን አለማወቅ ነው ። የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ እንደማይሠራ ዘንግተን በእልህ እየተንጨረጨሩ መስበክ አላዋቂነት ነው ። ሰውን እስከ ዛሬ ያመንከው ዋጋ የለውም በማለት እናስቆጣው ይሆናል እንጂ አናለዝበውም ። የምታምነው ምንድነው ? ብሎ እስኪጠይቀን ሕይወታችን ካልገዛው ቃላችን አይገዛውም ። “እለምናችኋለሁ” የሚለው የሐዋርያው የተለመደ ንግግሩ ነው ። ምን ያህል ከሐዋርያት የስብከት ዘዴ እንደ ወጣን ይህ ክፍል ይነግረናል ። 

 

“እለምናችኋለሁ” በማለቱ የንግግር ጥበብን እያሳየን ነው ። ንግግር ሰዎችን ባለ ድርሻና ተሳታፊ ሲያደርግ ተቀባይነት ያገኛል ፣ ተቃውሞን ያርቃል ። የሚለምንን ሰው የሚሳደብ ማንም የለም ። መለመን መለማመጥ አይደለም ፣ በእግዚአብሔር ስም የሰውን ልብ ማራራት ነው ። ሰው ካልታመመ በቀር ምግብ እንቢ አይለውም ፣ ምግብ እንቢ ያለውን ሰው በጉርሻ ሳይሆን በማንኪያ ፣ በቍጣ ሳይሆን በመለመን ይመግቡታል ። አሊያ ወደ ሞት ይሄዳል ። ክርስቶስ መድኃኒት ነው የምትል ወንጌልም በማዘን መንፈስ መሰበክ አለባት ። የለዘበች ምላስ ቍጣን ማብረድ ትችላለች ፣ አለቃንም ትማርካለች  ። “ካነጋገር ይፈረዳል ፣ ካያያዝ ይቀደዳል” እንዲሉ ። ንግግር በተፈጥሮ የምንካነው ብቻ ሳይሆን ልምምድና ትምህርት የሚፈልግ ነው ። ያልቦካ ጭቃ እየለጠፉ ለጽድቅ ቀንቼ ነው ብሎ መቀባባት ተገቢ አይደለም ። በኃይል ንግግርም አሳምናለሁ ብሎ ማሰብ መጠላትን እንጂ መወደድን አያተርፍም ። ሁሉም ሰው የራሱን ጥቅም ሊለቅ ይችላል ፣ የራሱን ክብር የሚለቅ ግን በጥቂት እንኳ ላይገኝ ይችላል ። ደረቅ ንግግር ይሰብራል ፣ የሚልመጠመጥም መልእክቱን የግሉ ያደርገዋል ። በጥበብ የለዘበ ንግግር ለአንድ ልከኛ አገልጋይ አስፈላጊው ነው ። 

 

“እለምናችኋለሁ” የሚለው ንግግር የወንጌልን ጠባይ ይገልጣል ። ወንጌል የምሥራች ናት ። የምሥራች አያሸብርም ። የምሥራች ብለን ስንናገር ሰዎች የሚሰጡት መልስ “ምስር ብላ” የሚል ነው ። ዝም ስንል “ምንድነው ንገረኝ?” ይሉናል ። ወንጌልን እስከዚህ ድረስ የደስታ መልእክት ማድረግ ይገባናል ። ወንጌሉና ወንጌላችን ይለያያል ። ወንጌል ከጌታችን ጽንሰት እስከ ዕርገቱ ያለው ዜና ክርስቶስ ነው ። ከዚህ የወጣ ስድብ ፣ ዘራፍና ፉከራ ወንጌል አይደለም ። ወንጌል የማንንም ክብር ነክቶ አያውቅም ። እንደውም ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ ይላል ። ሽቅብ ተንጠራርቶም ከቅዱሳን ጋር እኩል ነኝ ፣ እኔ ከመልአክ እበልጣለሁ አይልም ። ከሁሉ የማንስ ነኝ የሚል ነው ። 

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እለምናችኋለሁ” በማለቱ ታላቅ አባት መሆኑን ገለጠ ። ሸለቆ ውስጥ የወደቀ ሰው ልታደግህ ተብሎ አይለመንም ። እርሱ ራሱ አውጡኝ እያለ ይለምናል ። ሐዋርያው ግን “እለምናችኋለሁ” በማለት ሳያበሩ እንዳይሞቱ ይማጸናል ። “ብርሃን ናችሁ” ተብለዋልና ። ብርሃን የማዕረግ ስም ሳይሆን የተግባር ስም ነው ። ወንበሩን ይዘው ሥራ ሳይሠሩበት እንዳያልፉ እየተማጸናቸው ነው ። ዕድልና ጊዜ እኩል ገጥመው አይገኙምና እባካችሁ ተጠቀሙበት  እያለ ነው ። ምንም ከሌለው ሰው ይልቅ እያለው የማይጠቀምና የማይጠቅም ያሳዝናል ። 

 

ንግግራችን እልህ ያለበት ከሆነ የበለጠ እልኸኛ እናመርታለንና ዝም እንበል ።

 

ንግግራችን ጥበብ የሌለው ከሆነ ሰውን እናስከፋለንና ዝም እንበል ።

 

ንግግራችን የሰውን ነጻ ፈቃድ የማያከብር ከሆነ ሰውን እንደ ዕቃ ቆጥረነዋልና ዝም እንበል ።

 

ንግግራችን ወንጌሉን ሳይሆን ወንጌላችንን የሚያወራ ከሆነ ከእኛ የበለጠ ዓመፀኛ ያፈራልና ዝም እንበል ። 

 

 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም