የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መጽሐፍ ቅዱስ / ክፍል አምስት

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ

                                                       እሑድ ሐምሌ 6/2006 ዓ.ም.
በክፍል አራት ትምህርታችን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ሲል ሦስት ነገሮችን እንደሚገልጽ በመጠቆም ብቻ የፈጸምን ሲሆን እነዚህን ሦስት ነገሮች ቀጥሎ እንዘረዝራለን፡፡
1.      አካላዊ ቃል
ይህ በግሪኩ ሎጎስ /Logos/ የሚለው ሲሆን እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዮሐንስ በወንጌሉ፡- “በመጀመሪያ ቃል ነበረ÷ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ÷ ቃልም እግዚአብሔር ነበር” (ዮሐ. 1፥1) የሚለው “በመጀመሪያ ሎጎስ ነበረ” ማለቱ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አካላዊ ቃል (ሎጎስ) ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ሎጎስ የሚለው ቃል አይገኝም፡፡ ለምን? ስንል ኢየሱስ ክርስቶስ ገና በሥጋ አልተገለጠምና ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ግን “ቃልም ሥጋ ሆነ” ስለሚል ሎጎስ ተግባራዊ ሆኗል (ዮሐ. 1፥14)፡፡ ሌሎች ቃሎች ረቂቅ፣ ዝርው (ብትን) ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን መለኮታዊ አካል ያለው ስለሆነ አካላዊ ቃል ተብሏል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፣ ቃል የልብ መልእክተኛ ነው፣ ሥልጣንና አዛዥነትም ይገልጣል፡፡ እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ መልእክተኛ ሆኖ ወደ ዓለም መጥቷል፡፡ ሥልጣንና አዛዥነትም አለውና የእግዚአብሔር ቃል ተብሏል፡፡

ታላቁ የዜማ አዋቂ መሪጌታ ፀሐይ ብርሃኑ፡- “ሎጎስ በጥንት የአረማውያንና የአይሁዳውያን ሥነ ጽሑፍ  የታወቀ ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ500 ዓመት የነበረው ሒራክሊቱስ የተባለው ፈላስፋ “ሎጎስ እግዚአብሔርን በመግለጥ ዓለምን የሚገዛና የሚያሳውቅ የበላይ ምክንያት በማለት ጽፎ ነበር፡፡ ከእርሱም በኋላ በይበልጥ ለሌሎች ያስተዋወቁት ስቶይክስ የተባሉ ከ335-263 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበሩ ፈላስፎች ናቸው፡፡ እነዚህ ፈላስፎች በአቴንስ ትምህርት ቤት አቋቁመው ስለ ሎጎስ ያስተምሩ ነበር፡፡ የዚህ ጽንሰ ሐሳብ ትርጉም ግሪክኛ በሚናገሩ አይሁዳውያን ዘንድ ይበልጥ እየተስፋፋ መሄዱ ጥበብ (Wisdom) ከሚለው ጋር የትርጉም ዝምድናን አገኘ፡፡ በእስክንድሪያ ከ30 ዓመተ ዓለም እስከ 50 ዓ.ም የነበረው ፋይሎ የተባለ አይሁዳዊ ፈላስፋ ግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስን በማዛመድ ሎጎስ የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም አንድ ያደረገ መለኮታዊ ኃይል ነው በማለት ይገልጻል፡፡ የፋይሎን መጻሕፍት ያነበቡ ግሪክኛ ተናጋሪ አይሁድም እግዚአብሔር ራሱን ለዓለም ይገልጥ የነበረው በቃል አማካይነት ነው፡፡ ያህዌ ለአብርሃም፣ ለአጋር፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ፣ ለሙሴ በቊጥቋጦ ራሱን የገለጠላቸው በቃል አማካይነት ነው… በማለት ይተርካሉ፡፡ ስለዚህ ወንጌላዊው ዮሐንስ በግሪክኛ ወንጌሉን ሲጽፍ አይሁዳውያንና አረማውያን በለመዱት “ሎጎስ” የሚለውን ቃል በመጥቀስ፡- “ለአባቶችና ለነቢያት ሥጋን ከመልበሱ በፊት የተገለጠው የያህዌ ቃል ዛሬ በሥጋ የተገለጠው ክርስቶስ እንጂ ሌላ አይደለም በማለት በመጀመሪያው ምዕራፍና ቊጥር ይገልጻል፡፡” ብለዋል /ቃለ ምዕዳን 1 ፡ 1993 ዓ.ም  ቦስተን/፡፡ አዎ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሲል በመጀመሪያ የሚገልጸው አካላዊ ቃል የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፡፡


2.     የተጻፈው ቃል (መጽሐፍ ቅዱስ)
በግሪኩ ግራፌ /Graphe/ የሚለው ነው (ዮሐ. 5፥39-40)፡፡ በጥንት ዘመን እግዚአብሔር ቃሉን በሕልም፣ በራእይ፣ በሜዳ ይሰጥ ነበር፡፡ አሁን ግን በተጻፈው ቃሉ በኩል ይናገረናል፡፡ ብዙዎች በክርስትናቸው ለማደግ ተአምር ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን በክርስትና ለማደግ ከቃሉ የበለጠ ተአምር የለም (1ጴጥ. 2፥1)፡፡ ነቢዩ፡- “በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጽኑ” (መዝ. 32(33፥6) ይላል፡፡ ታዲያ ሰማይን ያፀና ቃል የእኛን ሕይወት ማቆም እንዴት ይሳነዋል?
3.    መገለጥ
በግሪኩ ሪህማ (Rhema) የሚለው ነው፡፡ ለአንድ ሰው ለተለየ ጉዳይ የሚነገር የእግዚአብሔር ድምፅ ወይም የመንፈስ ቅዱስ መልእክት ነው፡፡ ይህ ወቅታዊ መገለጥ በዕብራይስጥ ዳቫር /Davar/ ይሉታል፡፡ በግሪኩ ግን ሪማ-ሬማ ይለዋል፡፡ ይህ ድምፅ ተአምራዊ ስለሆነ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አጋንንትም ተአምራት ያደርጋሉና፡፡ ይህ ወቅታዊ መገለጥ እግዚአብሔር ሲሰጠን የምንቀበለው እንጂ አንቴናችንን ገትረን የምንጠባበቀው አይደለም፡፡ ይህን ወቅታዊ መገለጥ እንደ ዶክትሪን ይዘው ቤተ ክርስቲያን የሚመሠርቱ፣ በሐሰተኛ ተስፋ ሕዝብን የሚያስቱ ወገኖች ብዙ ናቸው፡፡
መቼም እግዚአብሔር ሲናገር አትናገር አንልም፡፡ ነገር ግን ድምፁን መለየት ግድ ይላል (ዮሐ. 10፥4)፡፡ ይህንን ወቅታዊ መገለጥ ለመቀበል፡- አንደኛ፡- የመጣው መገለጥ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ይስማማል ወይ? ማለት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም መገለጡ የመንፈስ ቅዱስ ከሆነ መንፈስ ቅዱስ የሚናገረው በቃሉ ነው (ዮሐ. 14፥26)፡፡ እግዚአብሔር፣ ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ አይናገርምና መገለጡ የቃሉ ድጋፍ አለው ወይ? ብሎ መመርመር ይገባል፡፡
ሁለተኛ፡- ተቀባዩ ወገን መገለጡን ከተጻፈው ቃል በላይ ያከብራል ወይ? ማለት ያስፈልጋል፡፡ እንድናውቀው የተፈቀደልን የመጨረሻው ነጥብ በቅዱስ ቃሉ ሠፍሯል፡፡ የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ፡- “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና ጐዳና ለአባቶቻችን ለነቢያት ተናግሮ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” (ዕብ. 1፥1-2) ብሏል፡፡ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው መልእክተኛ በመሆኑ በእርሱ ከተነገረው የሚበልጥ የሚመስል መልእክት ማንም ይዞ ቢመጣ ከእግዚአብሔር የተላከ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ሲል
የቃሉ ምሳሌዎች
“መጽሐፍ ቅዱስ የሚተረጎመው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው” ይባላል፡፡ የእግዚአብሔር ቃልም ስለ እግዚአብሔር ቃል ይናገራል፡፡ ከዚህም ውስጥ ለቃሉ የተሰጡ ምሳሌዎችን እናያለን፡-
– የወንዝ ዳር፡- ያለመልማልና (መዝ. 1፥2-3)፤
– የማር ወለላ፡- ያጣፍጣልና    (መዝ.118(119) ፥103፤ሕዝ. 3፥2-3)፤
– ጥሩ ውኃ፡-   ያረካልና        (መዝ.22(23)፥2)
– መዶሻ፡-      ያደቃልና       (ኤር.23፥29)
– እሳት፡                ያጠራልና       (ኤር.23፥29)
– ብርሃን፡-     ያሳውቃልና     (መዝ.118(119፥105)፤
– እንጀራ፡-     ያኖራልና    (ማቴ. 4፥4፤ ዘዳ. 8፥3)፤
– ራጅ፡-                ውስጥን ያሳያልና (ዕብ. 4፥12)
– ዘር፡-         ያፈራልና       (ሉቃ. 8፥4-15)፤
– ወተት፡-      ያሳድጋልና      (1ኛ ጴጥ. 2፥1) ፤
– ሰይፍ፡-      ትጥቅ ነውና    (ኤፌ. 6፥17) …፡፡
የእግዚአብሔር ቃል በብዙ ምሳሌዎች የተገለጠ መሆኑን አይተናል፡፡ ከምሳሌዎቹ ውስጥ አንዱን እንደገና ብናይ፡-
የእግር መብራት፡- “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው” (መዝ. 118(119)፥105)፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ከቀኑ ሐሩር የተነሣ በሌሊት መጓዝ የተለመደ ነው፡፡ ከጨለማውም ጋር ሽፍቶችና ዘራፊዎች አሳሳቢዎች ስለሆኑ በኅብረት መጓዝ የተለመደ ነው፡፡ ጨለማው ጥልቅ መልክአ ምድሩም ገደላማ በመሆኑ የሚረግጡትን በትክክል ለማየት ይቸገራሉ፡፡ ሜዳ የረገጡ መስሎአቸው ገደል ሊገቡ ይችላሉ፡፡ የሚረግጡትን እርምጃ በትክክል ለማየት እግራቸው ላይ መብራት  አስረው ይሄዱ ነበር፡፡ ይህ የሚረግጡትን በትክክል ያሳያል፡፡ ነቢዩ በዚህ ምሳሌ፡- “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው” አለ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ምሪት ይሰጣል፡፡ ውሳኔን ያጠራል፡፡ የምንኖርበት ሕይወት ውሳኔን የሚጠይቅ ነው፡፡ አስተማማኝ ውሳኔ እንደወሰንን ለማወቅ በጉዳዩ መጸለይና የልባችንን ሰላም ማዳመጥ የእግዚአብሔር ሰዎችን (አገልጋዮችን) ምክር መጠየቅ አስፈላጊ ሲሆን የመጀመሪያው ግን ቃሉ ይደግፈኛል ወይ ማለት ነው፡፡ 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ