የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሞተን ነበር

“በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ ፤” ኤፌ. 2፡1-2 ።

በደልና ኃጢአት ሙት ያደርጋሉ ። ተደጋጋሚ ስህተቶች በደል ሲባሉ ድንገተኛ ውድቀት ኃጢአት ሊባል ይችላል ። በአዳም ኃጢአት ላይ ቃየን መግደልን ጨምሮበታል ። ራሱ አዳምም በሕግ መተላለፍ ላይ ምክንያተኝነትን አክሏል ። በተላላፊነቱ ዓመፀ ፣ በምክንያተኝነቱ ከንስሐ ቀረ ። በደል የሰው ልጆች የተያዙበት ወጥመድ ነው ። ወዳስለቀሳቸው ታሪክ እንደገና የሚመለሱት በበደል ምክንያት ነው ። እሳት አንድ ጊዜ ፈጅቷቸው ዕድሜ ልካቸውን ይጠነቀቃሉ ፣ በደል ፈጅቷቸው ግን እያለቀሱ ይሰማራሉ ። በደል በአንድ ዓይን ቢስቁበትም በአንድ ዓይን የሚያለቅሱበት ፣ ዛሬ ልክ ነኝ ቢሉበት ነገ የጸጸት ወለድ ያለበት ነው ። ሰዎች ስህተት ብቻ ሳይሆን የተደጋገመ በደልም አላቸው ። ለበደልና ለኃጢአት ሌሎችን ተጠያቂ በሚደረግበት ዓለም “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ” ይላል ። ሁላችንም በደለኞችና ኃጢአተኞች ነን ። የምንለያየው በዓይነቱ እንጂ በንጹሕነት አይደለም ። ኃጢአት የአንድ ቀን ክስተት ሲሆን ከፊቱ የንጽሕና ዘመን አለውና ስህተቱ ጥርት ብሎ ይታያል ፣ ሰውዬውም በጸጸት ወደ ንስሐ ይቀርባል ። በደል ግን ከኋላው ኃጢአት አለና ጥርት ብሎ አይታይም ። ስለዚህም ልብን ያደነድናል ። አንድ ሰው የገደሉ ሰዎች የሚሰማቸው ጸጸት ከፍ ያለ ነው ። ሲደጋግሙት ግን የሕዝብ ቍጥር ያስተካከሉ መስሎ ሊሰማቸው ይችላል ። ሰው ኃጢአተኛ ብቻ ሳይሆን በደለኛም ነው ። ስህተት ብቻ ሳይሆን ድፍረትም ያለበት ነው ።

በደልና ኃጢአት ሙት ያደርጋል ። ሞት ወደ ዓለም የገባበት በር ኃጢአት ነው ። ሞት የተገነዘበት ፣ ገዳዩ የሞተበት ምሥጢርም የክርስቶስ ቤዛነት ነው ። ክርስቶስ ሰውን ሲያገኘው ሙት ሁኖ አገኝቶታል ። ታሞ ቢያድነው ኖሮ “በሽታው እየለቀቀኝ ነበር ፣ እርሱ ሰበብ ሆነልኝ እንጂ” ይል ነበር ። ጣር ይዞት ቢያገኘውም “ፍርሃት እንጂ ለሞት የሚያበቃ ገጠመኝ አልነበረም” ይላል ። ዕለቱን ሞቶ ቢያገኘው ገና አካሉ አልቀዘቀዘም ነበር ፣ ከመቶ አንድ እንዲህ ይገጥማል ይባላል ። ሠልስት ላይ ቢያገኘው አልዓዛርም በአራተኛው ቀን ተነሥቷል ይባል ነበር ። ክርስቶስ ሰውን ያገኘው ግን 5500 ዘመን የሞት ዕዳ ወድቆበት ሳለ ነው ። በዚህ ሞት ያልሞተ አልነበረምና አልቃሽና ልቅሶ ደራሽ አልነበረም ። ለሕመሙ የሚያለቅሰው የሰው ልጅ ለበለጠው ሞቱ ግን ዝም ይላል ፤ ሞት ለራስ ጉዳትም ማልቀስ አለመቻል ነው ። ኃጥእም እርሱ ደንዝዞ ቤተሰቡ ስለ እርሱ እንቅልፍ ያጣል ። አልዓዛር የተነሣው በተአምራት ሲሆን የአልዓዛር ሞት የተፈጥሮ ግዴታ የሚባል እንጂ በደልና ኃጢአት አልነበረም ። ክርስቶስ ግን ሰውን ያዳነው በተአምራት ሳይሆን በመሥዋዕትነት ነው ። የዳነውም ከዘላለም ሞት ነው ።

ሙት መንቀሳቀስ አይችልም ፣ ኃጥእም ከገቢረ ጽድቅ የራቀ ነው ። ሙት ቢራሩለት አይድንም ፣ ኃጥእም ያለ ቤዛ ትንሣኤ አያገኝም ። ሙት አሁን የሕሊና ሸክም ነው ፣ ካልቀበሩት እህል አይቀምሱም ፤ ኃጥእም የእግዚአብሔርና የአገልጋዮች ሸክም ነው ። ሙት ከቆየ አካባቢውን ይበክላል ፣ ኃጥእም ባልንጀራ ይፈልጋል ። ሙት ብዙ ልቅሶ ቢለቀስለትም ፣ ብዙ እንባ ቢፈስለትም ልመለስ አይልም ። ኃጥእም እናቱ ጡትዋን አውጥታ ብትማጸነው ያለ እግዚአብሔር ቃልና ያለ መንፈሱ ረዳትነት አይመለስም ። ሙት ክፉውን አይፈራም ፣ አማኝ ስለሆነ ሳይሆን ስለሌለ ነው ፤ ኃጥእም ሲኦልና ገሀነም ቀልድ ይመስለዋል ። ሙት ስላልበላ ጾመኛ አይደለም ፣ ኃጥእም በስስት ራሱን ስለ ጎዳ ዓለምን እየናቀ አይደለም ። ሙት ለሸክም ይከብዳል ፣ ዓመፀኛም አብረውት የሚኖሩትን ያደክማል ። ሙት በስሙ የተዘጋጀውን እህል ውኃ አይቀምስም ፣ ኃጥእም ለእርሱ የተዘጋጀውን የክርስቶስን ሥጋና ደም ይሸሻል ። ሕፃንም አዋቂም ይሞታል ፣ ኃጢአትም ሁሉን ይገዛል ። በቁሙ ቤት የሌለው ሲሞት ርስት ያገኛል ፤ ርስት ጉልት ያለውም ቢሆን በጽድቅ ካልኖረ ሙት ይባላል ።

ሞት የሚለው ቃል በጥሬው ሲተረጉሙት መለየት ማለት ነው ። ሞት ያለ ሕይወት መሆን ነው ። ሕይወት ከሆነው እግዚአብሔር መለየትም ትልቁ ሞት ነው ። ሞት አዳም በወደቀ ጊዜ የመጣ የኋላ ዕዳ እንጂ ከተፈጥሮው ጋር የነበረ ግዴታ አይደለም ። እንኳን የነፍስ ሞት የሥጋ ሞትም አልነበረበትም ። ክርስቶስ በመሞቱ ግን የሥጋ ሞት ተቀደሰ ። መለኮት በሥጋ ሙቷልና ሞት የአማኝ የሰርጉ ቀን ሆነ ። የሞት ትርጉም መለየት ነበረ ፣ አሁን ግን ከክርስቶስ ጋር መገናኛ ሆነ ። መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን በተለያየ መንገድ ይፈታዋል ። ሞት ለደግም ለክፉም ማብራሪያ ቀርቧል ። የአዳም ሞት የሞትንበት ሲሆን የክርስቶስ ሞት ግን የዳንበት ነው ። እሾህ በእሾህ እንዲነቀል ሞት በሞት ተሸነፈ ። ሰዎች ይህን ዓለም መናቃቸው ፣ መናኔ ንብረት ሁነው በመጠን መኖራቸው ሞቱ ያሰኛቸዋል ። አማኝም የምናኔ ኑሮ መኖር ግዴታው ነውና ከክርስቶስ ሞት ጋር ይተባበራል ። ማለትም ለዚህ ዓለም ፍላጎት በሞት ሕግ ፣ በሞት ጭካኔ ይለያል ። የሞት ሕግ በሁሉ ይሠራል ፣ አማኝ በሙሉም መቀደስ ይገባዋል ፤ ሞት እናትና ልጅን የሚለይ ስለት ነው ። ዘመዶቹ እያባቡትም አማኝ አዲሱን ዓለም የሚመርጥ ነው ። ሞት ለክርስቶስ ሲነገር ዓለም የዳነበት ነው ። ለአማኝ ሲነገርም ዓለምን የተወበት ነው ።

የሞት ክፉ ትርጉም ግን ከአዳም ይጀምራል ። ሞት ወደ ዓለም የገባው በኃጢአት በር ነው ። ሞትም የኃጢአት ክፍያ ነው ። ሁሉም ነገር ራሱን የሚመስል ደመወዝ አለው ። ኃጢአትም ሞት የሚባል ደመወዝ ይከፍላል ። ሞት መለየት ነውና ኃጥእም ከሕሊናው በመለየት ቅጣቱን ይጀምራል ። የአዳም ሞት ሰውን ሁሉ መዋቲ እንዳደረገ የክርስቶስ ሞት ግን ሰውን ሁሉ አድኗል ። አዳም ሊገድለን ሞተ ፣ ክርስቶስ ሊያድነን ሞተ ። በሞትንበት ሥጋ መዳናችን ይገርማል ። አዳም በበደሉ ፣ ክርስቶስ በጽድቁ ሞቷል ።

በደልና ኃጢአት የሰውን ሁለንተና ይገድላል ። ሞት ሰው ሲፈጠር የታቀደ አልነበረም ። በደል ግን ሰውን የሞት ልጅ አደረገው ። ሞት አስቀድሞ በፍርሃቱ ፣ ቀጥሎ በሁነቱ ሰውን ሁሉ የሚያሰጥም ሆነ ። ሞት ድርብርብ ሁኖ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ የሚነባበር ሆነ ። በተነባበረ በረከት የተፈጠረው ሰው ፣ ምድርና ሰማይን እንዲወርስ የተበጀው የሁለት ዓለም ባለቤት ፤ የሁለት ዓለም ሟች ሆነ ። ሰው የሚወድቀው የከፍታውን ያህል ነውና ። ይህን የሥጋ ሞት ተወጣሁት ቢል እንኳ የነፍስ ሞት የሚጠብቀው ሆነ ። ክርስቶስ ጌታችን ዛሬ ላመኑበት ሞተ ነፍስን ፣ በምጽአት ደግሞ ሞተ ሥጋን ድል ነሥቶ በትንሣኤ አካል በዘላለም አገር ያኖረናል ።

በደል ሙት ያደርጋል ። የኤፌሶን ሰዎች ሙታን ነበራችሁ ሲባሉ መቃብር ገብታችሁ ነበር እያላቸው አልነበረም ። ጌታችን “ሞቼ ነበር” አለ ። እርሱ ግን የሞተው በሥጋ ነው ። የኤፌሶን ሰዎች ግን በነፍስ ሞተው ነበር ። የእርሱ ሞት ጽድቅ ፣ የእነርሱ ሞት ክሽፈት ነበር ። ሞትን በነበር ለመናገር መብቃት የሚቻለው “ሞቼ ነበርሁ” ያለውን ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው ። ይህ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ረቂቅ ቅኔ ፣ ጣዕም ያለው ዜማ ነው ። ኦርቶዶክሳዊነት ክርስቶስን ይናኛል እንጂ ለክርስቶስ እንግዳ አይደለም ። የክርስቶስ ስም ሲነሣ የሚደነግጥ ክፉ መንፈስ እንጂ አማኝ አይደለም ።

ሞትን በነበር ያስተረከን አምላክ ምስጋና ይድረሰው !

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /28

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ