የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የጴጥሮስ አማት



የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ…….ሕዳር 27 2006 ዓ/ም 
እግዚአብሔር ከባርነት እሳት ነጥቆ፣ ከቀንበር ኑሮ በክንዱ አላቆ፣ በኃይል ሳይሆን በፍቅር ማርኮ፣ ለምድር ሳይሆን ለሰማያዊው ክብር ሕዝቡን ከቀደሰ በኋላ በጸጋው በኩል የሚያገለግሉትን ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን አገልግሎት አስደሳችና የአርያምን አክሊል የሚያቀዳጅ የመሆኑን ያህል ብርቱ ኃላፊነትም አለው፡፡ መንጋው ሲተኛ ስለ ሕዝቡ እግዚአብሔር ፊት መንቃት፣ በቃልና በኑሮ በፍቅርና በእምነት እንዲሁም በንጽሕና ለሚያምኑት ምሳሌ መሆን፣ የእኛና የሕዝቡን ፍላጐት ሳይሆን እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ያለውን የዘላለም አሳብ መግለጥ፣ በደከሙትና በዛሉት መካከል ከእምነት በሆነ ድፍረት እና ብርታት መገለጥን ይጠይቃል፡፡ ዛሬ አገልግሎት ሙያ አልያም ከፈትነት መዋያ ተደርጐ ቢቆጠርም እግዚአብሔር በዚህ ላይ ያለው አሳብ ግን የታመነ ነው፡፡ እውነተኛ አገልጋይ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረው ዘንድ እየተጋ በእውነትና በመንፈስ ሰማያዊውን አሳብ በሰዎች ልብ ውስጥ ለማስፈፀም ሕይወቱን የሰጠ ነው፡፡
ነገር ግን እግዚአብሔርን ሳይሰሙ መናገር፣ በእውነት ሳይነኩ መምከር፣ በአደባባይ ፎክሮ በጓዳ እጅ መንሻ ተቀብሎ በንጉሡ ፊት መሸማቀቅ፣ የባልንጀራን ኃጢአት በፍቅር ከመሸፈን ይልቅ በጥላቻ መግለጥ፣ እኔን ካላመኑ ሁሉን ይጠራጠሩ ማለት የዘመነው አገልግሎት ጠባይ እየሆነ መጥቷል፡፡ እግዚአብሔር ግን ከሁሉ በፊት በፈቃዱ እንድንገለገል ይፈልጋል፡፡ በማቴ. 8÷14 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ጴጥሮስ ቤት በገባ ጊዜ አማቱ (የጴጥሮስ) በንዳድ ታማ በመኝታ ላይ ሳለች እንዳገኛት ይናገራል፡፡ የጴጥሮስ አማት በዛ በታመመ ሰውነት፣ ደዌ ባቀለጠው ልብ ወደ ቤቷ የመጣውን ጌታ ለማገልገል ደፋ ቀና ወጣ ገባ ለማለት አልሞከረችም፡፡ ምክንያቱም በዛ ሙሉ ባልሆነ አቋም ልክነት በማይታይበት ሁኔታዋ ከምታስደስተው ይልቅ የምታስከፋው፣ ከምታቀናው ይልቅ የምታጠመው እንደሚልቅ አገልግሎቷም በወንፊት የመስፈርን ያህል ልብ የማያደርስ እንደሚሆን የተኛችው እርሷ የቆመውም ጌታ ያውቃሉ፡፡
ስለዚህ  በረሃው ከምንጩ፣ በሽታው ከፈውሱ፣ ጉድለቷ ከሙላቱ፣ ሸክሟም ከአሳራፊው አስቀድሞ መገናኘት ነበረበት፡፡ ይህ ሲሆን አገልግሎቱ ሕይወት የሚነካ፣ የንጉሡን ልብ የሚያሳርፍ፣ የአርያምን ደጆች የሚያስከፍት፣ እልፍኝ አልፎ መንደርን የሚወርስ ይሆናል፡፡ ጌታም እጃDን ዳሰሰ የጴጥሮስም አማት ንዳዱ ለቀቃት ከዚህም በኋላ ተነሥታ አገለገለቻቸው፡፡ ልብ ልንል የሚገባው ነገር ከነንዳዷ አለማገልገሏን ነው፡፡ ስለ ንዳድ ስናነሣ ብርቱ ራስ ምታትን እናስባለን፡፡ የሰውነታችንን ሙሉ ስርዓት የሚመራውን የሕይወታችንም ዋነኛ ክፍል የሆነውን አእምሮ የሚቆጣጠር እንደሆነም መረዳት ይቻላል፡፡ ራሴን ታመምኩ ማለት እግሬን እንደማለት ቀላል አይደለም፡፡ በእግር የማይሠሩ ሥራዎች በአእምሮ ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ አእምሮ የማይሠራውን ግን እጅም እግርም ሊሠሩት አይችሉም፡፡  ስለዚህ ከተራ ራስምታትነት ያለፈና አንዳች የሚያቃጥል /የሚቀጣጠል/ ነገር እንዳለ የሚጠቁም ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔርን ማገልገል ምንኛ ከባድ ነው፡፡ ዛሬ ለብዙዎች ከነንዳድ ማገልገል፣ ማስተዳደር፣ መምራት፣ መመገብ፣ ማሳደግ፣ መዘመር … ቀላል አልፎም ተርፎ ጥቅም ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ነዶ ሕዝቡን ማንደድ፣ ባዝኖ መንጋውን ማባዘን፣ ስቶ ከእውነት ማሳት፣ ሠግቶ ሰውን ማሥጋት የመልከኛው ክርስትና የኃይል አልባው አምልኮና አገልግሎት መገለጫ ነው፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ንዳድ ከእውነተኛው መፍትሔ ጋር እስካልተገናኘ ድረስ በሞት አገልግሎት ውስጥ ማምሸት ማንጋት፣ መሮጥ መትጋት፣ መውጣት መግባት፤ ላስተካክል ብሎ ማበላሸት፣ ላቅና ብሎ ማጥመም፣ ልሰብስብ ብሎ መበተን፣ ላፋቅር ብሎ ማናከስ የእድሜ ይፍታ መፍትሔ መሆኑ ቋሚ ነው፡፡

      በመጽሐፍ ቅዱሳችን የመጀመሪያ ክፍል በሆነው በዘፍጥረት (ኦሪት ዘልደት) አራተኛው ምዕራፍ ውስጥ የአዳም አብራክ ክፋይ በምሳሌውም እንደ መልኩ ልጆቹ የሆኑትን ቃየልና ወንድሙ አቤልን በሁለት የተለያየ መንገድ ላይ እናገኛቸዋለን፡፡ የሥጋ መዛመድ ለዓላማ አንድነት፣ ለአመለካከት ሕብረት፣ በጋራ መንገድም ለመዝለቅ ዋስትና እንደማይሆንም እናይባቸዋለን፡፡ የቃየልና አቤል ጠባይ እንደሙያቸው ሁሉ የተለያየ ነበር፡፡ ከብዙ ቀን በኋላ ቃየል ከምድር ፍሬ አቤል ደግሞ ከበጎቹ በኲራትና ከስቡ ለእግዚአብሔር መስዋዕትን አቀረቡ፡፡ እግዚአብሔርም የቃየልን ትቶ ወደ አቤልና መስዋዕቱ ተመለከተ (ተቀበለ)፡፡ እግዚአብሔር በፈለግነው አቅጣጫ ሳይሆን በወደደው መንገድ እንድናመልከው ይፈልጋል፡፡ በራስ መንገድ እግዚአብሔርን የማምለክ ልምምድ በወደዱትም አይነት ጐዳና የእግዚአብሔርን ይሁንታ የማግኘት ጥማት የቃየልን ውጤት ያስከትላል፡፡
      አገልግሎት የአምልኮ ክፍል እንደመሆኑ ቃሉን መሠረት ባላደረገና ሥጋና ደምን ባማከረ መንገድ ሲሆን ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ቃየል እግዚአብሔር ወደ መስዋዕቱ አለመመልከቱ ሳይሆን የወንድሙ ተቀባይነት ማግኘት ፊቱን አጠቆረው እጅግም ተናደደ፡፡ የእኛ ዓላማ ግቡን አለመምታቱ ሳይሆን የባልንጀራችን ስኬት፣ የእኛ ጸሎት አለመሰማቱ ሳይሆን የወንድማችን ስእለት መስመር፣ የእኛ አገልግሎት የሰውን ልብ አለመንካቱ የእግዚአብሔርን በጐ ስጦታ አለማምጣቱ ሳይሆን የጓደኛችን ምርኮ መሰብሰብ ፊታችንን የሚያከስለው ልባችንን የሚያቆስለው ስንቶቻችን ነን፡፡ እግዚአብሔርን ማባበልም ሆነ ማስገደድ አይቻልም፡፡ በራስ ምክርና ስሌትም ወደ ፍጹም በረከት መድረስ አይሆንም፡፡ እግዚአብሔር የሰማይ የምድር ገዥ (መንግሥት) ነው፡፡ ስለዚህ የሚያመልኩትና የሚያገለግሉት ሁሉ የእውነትን ቃል በቅንነት በመናገር የማያሳፍር ሠራተኛ በመሆን የተፈተነ ማንነታቸውን ለእርሱ ለማቅረብ መለኮታዊውን መርህ (መመሪያ) እንዲከተሉ ይሻል፡፡
       ቃየል ስህተቱን ማረም፣ ያበላሸውን ማስተካከል፣ ያሳዘነውን እግዚአብሔርን በንስሐ ይቅርታ መጠየቅ እንደሚችል የሚያስብበት ጊዜ አልነበረውም፡፡ ምክንያቱም ልብና አእምሮውን ቅናት ሥጋዊ ሞልቶታል፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ጠላት ዲያብሎስ የደለለው፣ የክፋትን ጉሽ የተጐነጨ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን፣ የምድሩን እንጂ የሰማዩን የማሰብ ፋታ የለውም፡፡ ይህ ደግሞ የአገልግሎታችንን ትርፍ አለማወቅ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ፡- መቼም ቢሆን እንክርዳድ ስንዴ ሆኖ ላናጭደው የቃየልን መንገድ አንውደደው፡፡ ቃየል በእግዚአብሔር ፊት ከእምነት የሆነ መልካም ነገር ባያደርግም መልካሙ እግዚአብሔር ግን ሊያናግረው መጣ፡፡ እግዚአብሔር ቀጣዩን ቢያውቅም ነፃ ፈቃድን ያከብራልና በፈጠረው ላይ ተስፋ አይቆርጥም፡፡ ቃየልን የተበዳዩ እግዚአብሔር የፍቅር ንግግር ብቻ  ሊያሸንፈው በተገባ ነበር፡፡ ክፋት የላከው ጌታውን አያፍርም ነውና በአሳቡ ደነደነ፡፡ እግዚአብሔር ግን አለው፡- ለምን ተናደድህ ለምንስ ፊትህ ጠቆረ መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅህ ታደባለች ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት፡፡” (ዘፍ.4፥ 6) ፡፡
ቃየል ራሱን ሊጠይቅ የሚገባውን ጥያቄ እግዚአብሔር ጠየቀው፡፡ ለምን እንዲህ ሆነ ? ለምንስ እንዲህ አልሆነም? ችግሩ ከእኔ ነው ወይስ ከሌላ? መፍትሔውስ ማን ጋር ነው? ልወስደው የሚገባኝ እርምጃ ምን ሊሆን ይችላል? ውጤቱ ባሰብኩት መንገድ ባይሆንስ? የሚሉት ጥያቄዎች ለመፍትሔው መንደርደሪያ ናቸው፡፡ ፊትን የሚያበራው መልካም ማድረግ ነው፡፡ ሰዎች ኮስሞቲክስ (መዋቢያ) ባለፈበት ገጽ ይማረካሉ እግዚአብሔር ደግሞ የበጐነት ሸማ በተነጠፈበት ሕይወት ያርፋል፡፡ ሰው ለፈጠረው እግዚአብሔር ያለውን ፍቅርና አክብሮት የሚገልጽበት መንገድ መታዘዝ ነው፡፡ ˝ለመታዘዝ ምላሹ መታዘዝ ነው፡፡ አንድ ሰው እግዚብሔርን ከታዘዘ እግዚአብሔርም ጥያቄውን (ጸሎቱን) ይታዘዘዋል” / አባ እንጦንስ/፡፡ መታዘዝ አደርጋለሁ ሳይሆን ማድረግ፣ እመለሳለሁ ሳይሆን መመለስ፣ እለወጣለሁ ሳይሆን መለወጥ ነው፡፡ ቃየል መታዘዝ ከመስዋዕት ማዳመጥም የአውራ በግ ስብን ከማቅረብ እንደሚበልጥ በማያገናዝብ አቋም ስለነበረ ወንድሙን አቤልን፡- ና ወደ ሜዳ እንሂድ በማለት በገዛ ወንድሙ ላይ ተነሣበት ገደለውም፡፡
ቃየል ወንድሙን ለመግደል አይደለም ለመውቀስ እንኳን የሚያበቃ ምክንያት አልነበረውም፡፡ ግን የቅንዓት ንዳድ ሲሠራ ምክንያት፣ ሲያጠፋም የሚወቅስ ሕሊና የለውም፡፡ ተፈጥሮንም ፈጣሪንም አያስተውልም፡፡ ይጀምር እንጂ ስለጀመረው፣ ይናገር እንጂ ስለሚናገረው፣ ይትጋ እንጂ ስለሚያተጋው ግድ የለውም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ለመጥላት ምክንያት ቢኖረን እንኳን ምክንያታችንን ለመውደድ እንድንለውጠው ይጠይቀናል፡፡ የሚጠሉንን መውደድ፣ የሚረግሙንን መመረቅ፣ ለከፉብን መልካም ማድረግ፣ ስለሚያሳድዱንም መጸለይ ክርስቲያናዊ ኑሮ እንዲሁም የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን ምስጢር ነው፡፡ የአንድ አባት እግዚአብሔር ልጆች፣ የአንድ አፈር ስሪቶች፣ በአንድ ዓለም ክርስትና ነዋሪዎች፣ ለአንድ ዓላማ ወንጌል ዘማቾች ሳለን የግል ፍላጐትና አሳብን እያገለገሉ፣ ባልንጀራን እየበደሉ፣ ወንድምን በቅናት እየገደሉ መኖር አሳፋሪ ነው፡፡ ካህሊል ጂብራን የተባለ ፀሐፊ “የፈላስፋው ድምጽ” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሑፍ አራተኛ ክፍል ላይ “ወንድምን መግደል ክርስትና ከሆነ ለቃየል መቅደስ ሥሩና አምልኩት” ያለው ዛሬ በክርስቲያኖች መሐል ያለው ሰጥአገባና መገፋፋት ታይቶት ሳይሆን አይቀርም፡፡
  
በእርግጥም ወንድምን ማሳደድ፣ ባልንጀራን ማጥመድ፣ ከእምነት ሳይሆኑ የእግዚአብሔርን እሽታ መናፈቅ በቃየል መንገድ አምልኮ ማረፍ ነው፡፡ ከአጋንንት ጽዋ እየጠጡ፣ ለእኔነት ጣዖት እያጠኑ፣ የእግዚአብሔርን ክብር እየጋረዱ የእግዚአብሔር ነኝ ማለትም የተለመደ ሆኗል፡፡  የፈላስፋው ድምጽ እንዲህ ይላል፡- “ለመኖር ስል ወንድሜን የምገድል ከሆነ ሞትን አስበልጫለሁ ማለት ነው፡፡” ከሕያው እግዚአብሔር ካልሆነ የሞት አገልግሎት ትርፉ የሥጋ ብቻ ነው፡፡ ቃየል የራሱ ድካም አይታየውም፣ ለምሰሶውም ግድ የለውም፣ ለውድቀቱ ሁሌም ተጠያቂ ሌሎች ናቸው፣ ለምህረት ዋጋ አይሰጥም፣ እግዚአብሔርን አይፈራም ሰውንም አያፍራም፡፡ ቃየል እገላለሁ ካለ ይገላል፣ አጠፋለሁ ካለ ያሳካል እንጂ ለምን የለም፡፡ ቃየል ይዘራል እንጂ ስለሚያጭደው ደንታ ቢስ ነው፣ ቃየል ይናደዳል እንጂ ስላናደደው፣ ፊቱ ይጠቁራል እንጂ ስላጠቆረው ሀቅ አይመረምርም፡፡ ቃየል ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅነት አያውቅም፡፡ ቃየል ደም አፍስሶ የማያውቅ ነፍሰ ገዳይ፣ ሰርቆ የማያውቅ ሌባ፣ ሀሰት የሚጠላ ቀጣፊ ነው፡፡ ቃየል አታጭሱ ይላል ግን ሰው ያጨሳል፣ አትቃሙ ይላል ግን ሥጋ ሰብእን ይበላል፣ ስካርን ይኮንናል ግን ባልንጀራውን በደም ያሰክራል፡፡ ተወዳጆች ሆይ እናንተስ?
በቃየል መንገድ እየሄዱ፣ ከማይጠፋውም ዘር ሳይወለዱ ሕዝቡን በዚህ አልያም በዚያ ተጓዙ ማለት፣ በእውነት በመንፈስ ሳያመልኩ ማስመለክ፣ ከቃሉ እንጀራ ሳይቆርሱ መንጋውን ማጉረስ እንዴት ይቻላል?  እትዉ በፍቅር!!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ