የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤት ልጅ ሁነናል

“አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል ።” ኤፌ. 2 ፡ 13 ።

መራራቅ በተለያየ ምክንያት የሚከሰት የሕይወት ሐቅ ነው ። ሰዎች በይሉኝታ ይርቃሉ ። ይሉኝታ አስፈላጊ የሚሆንባቸው ቦታዎች አሉ ። በይሉኝታ ሰዎች የተወሰኑ በጎ ነገሮችን ማድረግ ይችላሉ ። ይሉኝታ ሁሉ ግን እውነት አይደለም ። ይሉኝታ ከተፈጥሮ ፣ ከአስተዳደግ ፣ ከማኅበረሰብ ሊወረስ የሚችል ነው ። ይሉኝታ ሰዎቹ ገና ለገና እንዲህ ይሉኛል ብሎ በሕሊና ማፈርና የነፍስ ስደት መጀመር ነው ። ተጠባብቆ በሚኖር ማኅበረሰብ ዘንድ ይሉኝታ ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ክብር አለው ። በይሉኝታ ውስጥ የሚያልፈው ሰው ብዙ የልቡና እንግልት ቢደርስበትም ማንም አያውቅለትም ። ይህች ዓለም በግዴለሾችና ከመጠን በላይ በሚጨነቁ ሰዎች የተሞላች በሁለት ገመድ የምትጓተት አሮጊት ናት ። በይሉኝታ ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች የሌሎችንም ግዳጅ የራሳቸው አድርገው ይጨነቃሉ ። ይሉኝታ የማያሠራ ቢሆንም ቢያደርጉት እንኳ በፍርሃት ስለሆነ ጉልበትን ይበላል ። በይሉኝታ ውስጥ የታሰሩ ሰዎች በመራቅ የታወቁ ናቸው ። እንዲህ በመጥፋቴ ምን ብለውኝ ይሆን ? እያለ በማፈር ይሰቃያል ። አንድ ስልክ መደወል ሲችል ብዙ ቀኖቹን ይረብሻል ። መሄድ ሲችል በግምት ራሱን ይጨርሳል ። ፍቅር ግን የጋራ ነውና እርሱ ሲጠፋም እነዚያ ሰዎች መፈለግ አለባቸው ። አንዳንድ ሰዎችን የምናባልጋቸው እኛው ነን ። ስልክ ይዘው አይደውሉም ፣ እግር እያላቸው አይፈልጉንም ። እኛ የእነርሱን ሥራ ደርበን እንሠራለን ። እነርሱም የይገባኛል ስሜት ስለሚያዳብሩ ፍቅራችን ከመጥቀም ይልቅ እየጎዳቸውና ከሰው ቍጥር እያጎደላቸው ይመጣል ። እንስሳት እንኳ ጓደኝነትን በሚያከብሩበትና በሚፈላለጉበት ዓለም ላይ የግንኙነት ምዕራፉን የዘጋ ሰው በቁም የሞተ ነው ። ይሉኝታ ለመራራቅ ትልቅ በር ይከፍታል ። በይሉኝታ ያለ ሰው የሌሎችን ድርሻ ደርቦ የሚሠራና ሌሎችን የሚያሰንፍ ነው ። ራሱ በራሱ ያላመነውን ችግሩን ሰዎች እንዲያውቁለት የሚፈልግ ሞኝ ነው ። በቻለ ጊዜ ሁሉ ሰዎችን መፈለግ አለበት ። ባልቻለ ጊዜ አሳውቆ እስኪመቸው ድረስ መጠበቅ አለበት ።

መራራቅ የሚከሰተው በመቀያየምም ነው ። ፍቅር መቀራረብን ሲጨምር ቂምና በቀል ደግሞ መራራቅን ይከስታል ። የእኛ አገር ፍቅራችን እፍ የሚል አገር ጠበበኝ የሚያሰኝ ነው ። ጠቡም ልክ የሌለው ይሆናል ። በእርግጥ ሰውን ወደው ከማያውቁ ደንዳና ሰዎች ይልቅ ተዋደው የሚጣሉ ሰዎች የተሻሉ ናቸው ። ጥላቻ ግንብ ነው ። ይቅርታ ግን ድልድይ ነው ። ሌላው መራራቅ የሚከሰተው በእንጀራ ምክንያት ነው ። ሰው የሚኖረው ወዳጁ ካለበት ሳይሆን እንጀራው ካለበት ነው ። የሰው ልጆች ኑሮን ለማሸነፍ ከአገር ርቀው ፣ ሕይወታቸውን ከነጣቂዎች ለመታደግ ከዘመዶቻቸው እልፍ ብለው ይኖራሉ ። እየተዋደደ የሚለያይ ፣ እየተጠላላ አብሮ የሚኖር ብዙ ነው ። ዓለም ዥንጉርጉር ነውና ለፍርድ አይመችም ። መራራቅ በእስር ምክንያት ሊከሰት ይችላል ። እስር ቤት እኔ ልገባበት አልችልም የምንለው ሳይሆን ማንኛውም ሰው ሊገባበት የሚችል የኑሮ ገጽታ ነው ። ይህ ዓለም የምፈቅደው ብቻ ሳይሆን የተወሰነልንን የምንኖርበት ዓለም ነው ። እስር ቤትና ሞት ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ይነካል ። የመጨረሻው ንጉሥም የመጨረሻው ድሀም በእስር ቤት ይገናኛሉ ። ደረጃው ያራራቃቸውን ወለሉ አንድ ያደርጋቸዋል ።

መራራቅ ሲከሰት ይሉኝታን ሰብሮ መገናኘት መልካም ነው ። ምነው ባልመጣብኝ የሚሉን ሰዎች ባሉበት ዓለም ላይ ምነው ጠፋህብኝ ብለው የሚቀየሙን ካሉ ዕድለኞች ነን ። እነዚህ ሰዎች ያልተረዱን መስሎ ይሰማን ይሆናል ። ዕድል ናቸውና አንድ ቀን በራቸው ሲዘጋ ይቆጨናል ። ካለፈ በኋላ ማልቀስ ጠባያችን ከሆነ ሰንብቷል ። ይህ ግን የፈሰሰ ውኃ አይታፈስም የሚያሰኝ ነው ። ሰዎች ሰብአዊ ኩራት ይዞአቸው ፣ ባደጉበት ማኅበረሰብ ይቅርታ መጠየቅ ዳገት ሁኖባቸው እንጂ መበደላቸውን ሕሊናና መንፈስ ቅዱስ ይነግራቸዋል ። ስለዚህ እኛው ገፍተን ወይም ሽማግሌ ጠርተን ልንታረቅ ይገባናል ። አዲስ ሰው መቀየር ይቻላል ። ፍጹም ሰው ማግኘት ግን አይቻልም ። ኑሮ ከምንወዳቸው ሲያርቀንም በዓመት ሁለት ጊዜ ወይም አንድ ጊዜ መገናኘት ያስፈልገናል ። እግዚአብሔር ለእስራኤል በዓላትን ሲሰጥ ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ ወደ አገራቸው እንዲገቡ በማሰብም ነው ። ማሰብ ስንጀምር ኃይላችንን መሰብሰብ እንችላለንና እንደ ወጣን መቅረት የለብንም ።

ከእግዚአብሔር የራቅነው ግን በይሉኝታ አይደለም ። ሥራና ኑሮ ገጥሞንም ሳይሆን በኃጢአት ምክንያት ነው ። በኑሮአቸው ላይ የሚያመነዝሩ ሰዎች አንድ ቤት ቢኖሩም ልባቸው ግን ተራርቋል ። እንዲሁም ከእግዚአብሔር ፀሐይና ፣ ከጌታ አየር ብንጠቀምም አምልኮቱን ከሰረቅን ተራርቀናል ። አዳም አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ከገነት ርቆ ፣ ከገነት ጌታም ተቆራርጦ ይኖር ነበር ። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን በደሙ መፍሰስ ወደ አባቱ ቤት ተመለሰ ። አማኑኤል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ተብሏልና መለያየት ላይገጥመን በተዋሕዶ አንድ ሁነናል ። የቀደመ ታሪካችን ከእግዚአብሔር መራቅ ነበር ። የአሁን ማንነታችን ግን በጌታችን ሰው መሆን ተዛምደን ፣ በደሙ ታርቀን የእግዚአብሔር ወገኖች ሁነናል ። ከብዙ ዘመን በኋላ ተራርቀው የተገናኙ እንደ ገና የመወለድ ያህል ይሰማቸዋል ። አንዳንድ መራራቆች አለመተዋወቅና ስሜታችንን መለዋወጥ አለመቻል ነው ። እግዚአብሔርን በክፉ ሥዕል በሚስለው ጠላት አማካይነት ብዙዎች ርቀው ይኖራሉ ። እግዚአብሔር ግን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የተዛመደን ፣ በደሙ ፈሳሽነትም ያዳነን ነው ። እስራኤል የቤት ልጅ ፣ አሕዛብ የደጅ ልጅ ሁነው ኑረው ነበረ ፤ አሁን ግን ሁላችንም የቤተ ክርስቲያን አባላት ሁነናል ።

ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ