የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው /9

ወዳጄ ሆይ !

ሰውን ከጭንቀቱ የምታድነው ተስፋ በመስጠት ፣ ችግሩን አሳንሰህ በማሳየት ፣ አጠገብህ ነኝ በማለት ነው ። ተስፋውን ገድለህ ቍስሉን ብትጠርግ አይድንም ። እግዚአብሔርን ሳይሆን የችግርን የበላይነት ማሳየት ችግርን ማምለክ ነው ። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የተባለበት ዘመን ሐዲስ ኪዳን ተብሏልና አጠገብህ ነኝ ብሎ ችግረኛን ማጽናናት ብሩህ ዘመንን ያድለዋል ። ትላንት ክፉ መስለው ይታዩህ የነበሩ ዛሬ ደግ መሆናቸውን ፣ ትላንት ደግ መስለው ይታዩህ የነበሩ ዛሬ ላይ ልበ ጠንካራ መሆናቸውን ካየህ ፤ ዛሬም ክፉ የመሰሉህ አንድ ቀን ደግ መሆናቸውን ፣ ደግ የመሰሉህም እንደ ሸነገሉህ ትረዳለህ ። በችግርህ ቀን የቆመልህን ሰው ላትቀየም ውደደው ።

ወዳጄ ሆይ !

ሊሰጥህ ሲችል የከለከለህን ሰው አትቀየመው ፣ ሊሰጥህ ፈልጎ አቅም ያጣውንም አትናቀው ። ሰው ክፉ ነው ስትል አንተም ሰው መሆንህን አትዘንጋ ። በጥረቱ ያደገን ሰው ብታወርደውም ከፍ ይላል ። ቅን ሰው ስትሆን ሰላምህ የረጋ ይሆናል ። የሞላልህ ቀን የጎደለባቸውን አስብ ፤ የጎደለብህ ቀን የሞላላቸውን በማሰብ ላንተም ቀን እንዳለህ ተስፋ አድርግ ። ማበረታታት የሰውን ጸጋ የምታወጣበት መቅጃ ነው ። ሰው ጸጋውን ቢያወጣ ጥቅሙ ለራሱ ሳይሆን በዙሪያው ላሉት ነው ። በጨነቀህ ቀን የምትፈልገውና እንዲያወራህ የምትሻው ሰው ፣ በዚህ ምድር ላይ እግዚአብሔር የሰጠህ ፣ የሚሸከምህ ወዳጅህ ነው !

ወዳጄ ሆይ !

ከቤተ ክርስቲያንና ከእውነት ርቀህ ለመመለስ ትዕቢት ፣ ለመቅረት የሕሊና ወቀሳ ይዞህ የምትንገላታ ከሆነ ዛሬውኑ ወስን ። ብዙዎች ቢጠሏት እንኳ አንተ ብቻህን አገርህን ውደዳት ። ሚስትህን የምታጣት ትኩረት ካልሰጠሃት ነው ። ልጆችህን በባለ አደራነት መንፈስ እንጂ ለጥቅምህ ብለህ አታሳድግ ። ሕይወታቸውን ለሰጡህ ምንም ለመስጠት አትቆጥብ ። የሚተገበር ነገር ሲወራ ውስብስብ ይሆናል ። ለቃለ እግዚአብሔር ከሚገዛ ለልማዱ የሚገዛ ብዙ ነው ። ወደ ቤተ እግዚአብሔር በጥያቄ መጥቶ በጥያቄ የሚመለስ ምእመን ካለ ፣ ችግሩ ከምእመኑ ወይም ከአገልጋዮች ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ብትታመም በአገርህ ትታመማለህ ። አገርህ የታመመች ከሆነች ግን ዓለም ዝግ ይሆንብሃል ። ተሰደህም ለመከበር አገር ያስፈልግሃል ። ከሰላም የበለጠ ሀብት ፣ ከማስተዋል የበለጠ ሥልጣኔ ፣ ከፍቅር የበለጠ ደስታ የለም ። ያለ እግዚአብሔር እየተስፋፉ ያሉ ሰዎች እየጠበቡ ነው ። ልብስ ጸድቶ ልብ ከቆሸሸ የመንፈስ ነጻነት ገና አልመጣም ። የድሮ ሰው ልቡ ንጹሕ ፣ ልብሱ አዳፋ ነበር ። የዛሬ ልጅ ልብሱ ንጹሕ ፣ ልቡ ሸርታታ ነው ። መጠጥና ነገር የተሞላ ሰው ለመናገር እንጂ ለመስማት ቦታ የለውም ። ብዙ ሴት የሚያበዛ መጨረሻው ስብራትና የተጣለ መሆን ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

መጠጥና ዝሙት እንዳያሸንፍህ ራስህን ተቆጣጠር ። መጠጥ በጓደኛ ፣ ዝሙት በዓይንና በጆሮ ይጀመራሉ ። መጠጥ ዕብድ ፣ ዝሙትም የዕድሜ ልክ ባለ ዕዳ ያደርግሃል ። መጠጥና ዝሙት ተናባቢ ናቸው ። እጅግ ዘማውያን ግን መጠጥ አንጠጣም ባዮቹ ናቸው ። ያለ ስጦታህና ያለ አቅምህ የተሸከምከው ያንገዳግድሃል ። ስጦታህ ከሆነ አቅሙ አብሮ ይሰጥሃል ፣ አዝምቶ መሣሪያ የሚነሣ ንጉሥ የለምና ። ራስህን የሾምህበት ነገር ፍጻሜው ባዶ/መና ነው ። ለአገርህ አንተ ብቻ ያለሃት ፣ ለቤተሰብህ ካንተ ውጭ ማንም እንደሌለ ማሰብ ራስን መሾም ነው ። ሁለት ብርቱ ሰባኪዎች በአንድ መድረክ ቢያገለግሉ ይገፋፋሉ ። በሁለት አቅጣጫ ቢጓዙ ግን ስብከተ ወንጌልን ያሰፋሉ ። ይህንንም ከበርናባስና ከጳውሎስ ተማረው ። መጨረሻ ላይ ለመገናኘት ለጊዜው ተለያዩ ። /የሐዋ. 15፡36-41/

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ