የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የተንበረከክነው ለማን ነው ?

“ስለዚህም አሕዛብ ስለ ሆናችሁ ስለ እናንተ የክርስቶስ ኢየሱስ እስር የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ለእግዚአብሔር እንበረከካለሁ ።” ኤፌ. 3፡1 ።

“ተንበርክከን ከምንኖር ፣ ቆመን ብንሞት ይሻላል” የሚለው ንግግር ዝነኛ ነው ። ተንበርክኮ መኖር ፈርቶ ሐሰትን እውነት እያሉ መኖር ፣ ነጻነትን ተገፍፎ የበዪ ተመልካች መሆን ፣ ትውልድ የማይቀጥልባትን አገር ይዞ መዝፈን ፣ የአድር-ባይነት ኪዳን ውስጥ ገብቶ ለመጣ ሁሉ ማሸብሸብ … ነው ። በዚህ ትርጉሙ መንበርከክ ዘላለም ለማይኖሩባት ዓለም ሞትን ፈርቶ ፣ ሕሊናን ሸጦ መንቀዋለል ነው ። በዚህ ትርጉሙ ከራስ ጋር ተጣልቶ ከጊዜው ጋር ታርቆ ለመኖር መሞከር ነው ። ያሸነፈ ለመሰለ እየሳቁ ፣ የቀሚሱን አቧራ እያራገፉ ፣ በልብ እየረገሙ በአፍ እያወደሱ መኖር ነው ። ከዚህ ሞት የተሻለ መሆኑን የሚገልጥ ንግግር ነው ። ያ ሞትም የተፈጥሮ ሞት ሳይሆን ቆሞ መሞት ነው ። እውነቱ ይህ ነው ብሎ ፣ ጨለማን ጨለማ ብሎ ፣ የዘመን ድሪቶን ፣ ጊዜ የወለደውን ተረት አሽቀንጥሮ ጥሎ ሰማዕት መሆን ነው ። ከአንዳንድ ኑሮ አንዳንድ ሞት ትርጉምና ክብር አለው ማለት ነው ። ቆሞ መሞት እንቢ ለአገሬ ፣ እንቢ ለነጻነቴ ብሎ የማይቀረውን ሞት የክብር መሥዋዕትነት ማድረግ ነው ። ስለዚህ መንበርከክ ለዓለም ትርጉሙ አሉታዊ ነው ።

በእግዚአብሔር ዘንድ ግን በትዕቢት ቆመን ከምንኖር ፣ በትሕትና ተንበርክከን ብንሞት ይሻላል ። በእግዚአብሔር ዘንድ መንበርከክ ንስሐ መግባትና ሸክምን ማውረድ ነው ። ከወንድም ጋር ታርቆ የተሰበረውን ድልድይ መጠገን ነው ። መንበርከክ በእግዚአብሔር ዘንድ በጸሎት ፣ በምስጋና ፣ ቃለ እግዚአብሔርን በማሰላሰል ፣ መንፈሳዊ ኅብረትን በማፍቀር መኖር ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካደረጋቸው ተግባራት ሁሉ ተንበርክኮ እግር ማጠቡ አስደናቂ ብቻ ሳይሆን ልናደርገው የሚገባ ግዳጅም ነው ። ገዳማውያን አባቶች ዝቅ ብለው እግራችንን ሲያጥቡ የሚሰማን የማፈር ንዝረት መግለጫ የለውም ። መንበርከክ የሚያንሱንን ሰዎች እግር ለማጠብ ነው ። በዓለም ዘንድ ትልቅ ነውር ሲሆን በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ክብረት የሚያሰጥ ነው ። ለማስታረቅ ተንበርክከው እንቢ የተባሉ ሰዎች እንቢ ባዮቹን ተቀይመው ይኖራሉ ። መንበርከክ ለማስታረቅ ዝቅ ማለት ነው ። ቆሞ ማስታረቅ አይቻልም ፣ ቆሞ መታረቅም አይቻልም ። ዝቅ ማለት ያስፈልጋል ። ተንበርክኮ ያለውን ሰው ረግጦ መሄድ በምድር በሰማይ የሚያስወግዝ ክፉ ድርጊት ነው ። የተንበረከከው ለጥቅሙ ሳይሆን ለፍቅርና ለሰላም ነውና ሊከበር ይገባዋል ። መንበርከክ በቅርጻቸው ሳይሆን በልባቸው ሰው በሆኑ ዘንድ ክብር አለው ።

በትምህርት ቤት የሄድን እንደሆነ መንበርከክ ለቅጣት ነው ። ተማሪው በተማሪዎች ፊት ተንበርክኮ በማፈር እንዲቀጣ ይደረጋል ። መንበርከክ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ለበረከት እንጂ ለቅጣት አይደለም ። ለወትሮ ከማናከናውነው ፣ የትምም ከማናከናውነው ተግባር አንዱ መንበርከክ ነው ። ሃይማኖት ካለን ግን እንበረከካለን ፤ እንሰግዳለን ። “ሴት ልጅ ከተንበረከከች ፣ ወንድ ልጅ ካለቀሰ እግዚአብሔር ይለመናል ይላሉ ። አባቶች ለሴት ልጅ መንበርከክ ፣ ለወንድ ማልቀስ ተጨማሪ ፈተና ነው ማለታቸው ነው ። መንበርከክ እግዚአብሔር እኛን የሚለመንበት ነው ። መንበርከክ ኃይል ያንተ ነው ብሎ ለእግዚአብሔር እጅ መስጠት ነው ። መንበርከክ መማረክ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ያለው ችግር የሚወድቀው በመንበርከክ ነው ። አንዳንድ ሰዎች ባለጠጋ ፊት ይሰግዳሉ ፣ ሌሎችም ሹም ፊት ይንበረከካሉ ። በሰማይና በምድር ሥልጣን ላለው ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም መንበርከክ ግን ድል አለው ። ያንበረከከንን ነገር የምናበረክከው በመንበርከክ ነው ። የችግሮቻችን መልሱ ያለው ከጉልበታችን እስከ መሬት ነው ።

ሐዋርያው፡- “እኔ ጳውሎስ ለእግዚአብሔር እንበረከካለሁ” ይላል ። እኔ በማለቱ በጉልበት ብቻ ሳይሆን በልብም መንበርከኩን ያሳያል ። ብዙ አማኝ በልቡ ቆሞ በጉልበቱ ሽብርክ ብሏል ። መንበርከክን ልክ የሚያደርገው ውጫዊ ትእይንቱ ሳይሆን ልባዊ እውነቱ ነው ። መንበርከክ ልማድ የሆነባቸው ሰዎች አሉ ። አንዳንድ የትዳር ጓዶች የሁልጊዜ አጥፊ የሆነው ሰው ተንበርክኮ “የዛሬን ይቅር በዪኝ ፣ የዛሬን ይቅር በለኝ” ሲባባሉ የምንሰማው ምላሽ አለ ። “ልማዷ ነው ፣ ልማዱ ነው” የሚል ነው ። መንበርከክ ልማድ ሳይሆን አምልኮ ሊሆን ይገባዋል ። ሌሎች ሲያደርጉት አይቶ ፣ ወይም ሃይማኖተኛ ለመባል ሳይሆን በእውነት መንበርከክ ይገባል ። እግዚአብሔር የሚሸነፈው ሲሸነፉለት ነው ። መንበርከክ ለእግዚአብሔር መሸነፍ ነው ። ሐዋርያው ለማን እንደሚንበረከክ ያውቀዋል ። እርሱ አሁን በሮም የቄሣር እስረኛ ነው ። ለቄሣር ቢንበረከክ ኖሮ ይሾም ፣ ይሸለም ወይም ነጻ ኑሮ ያገኝ ነበር ። አልንበረከክም በማለቱ ግን ታሰረ ። በአንድ አካል ለሁለት ጌታ አላድርም ያለ ቆራጥ ነበር ።

ከሁሉ የሚገርመው የሚንበረከከው ከእስር ለመውጣት ሳይሆን ስለ ኤፌሶን ሰዎች መመለስ ለማመስገን ፣ መጽናታቸው ለመጸለይ ነው ። በሌሎች ሰዎች ደስታ ማመስገን የተፈታ አእምሮ ይፈልጋል ። ሐዋርያው በሥጋ ታስሮ በመንፈስ አርነት የወጣ ነበር ። እኛ ግን በሥጋ ነጻ ሁነን በመንፈስ የታሰርን ነንና ወዮልን ። በይሉኝታ ፣ በቅናት ፣ በሐሜት ፣ ገንዘብ በመውደድ ፣ በዝሙት ታስረናል ። የሥጋ እስረኛው ሐዋርያው ጳውሎስ ለመንፈስ እስረኞች ያስብ ነበር ። የእውነት ጉዞ ካልጀመሩ እንዲጀምሩ ፣ ከጀመሩ እንዲጸኑ ይንበረከክ ነበር ። መንበርከክ የዘሩት የቃለ እግዚአብሔር ዘር እንዲያድግ ውኃ ማጠጣት ነው ። የዘራ ብቻ አያጭድም ፣ የተንከባከበ እንጂ ። ሐዋርያው ስለ ክርስቶስ የተቀበለውን እስር ሰንሰለቱን እንደ እጅ አምባር ፣ እግረ ሙቁን እንደ ወርቅ ጫማ ይቆጥረው ነበር ። ጥቁር ከሚመስለው ነገር ጀርባ ያለውን ብርሃን ለማየት መፈታት ያስፈልጋል ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ