የታመቀ ስሜት መነሻዎች
1- የአስተዳደግ ሁኔታ
እናትን ወይም አባትን አሊያም ሙሉ ወላጅን በማጣት ያደጉ ልጆች የታመቀ ስሜት አላቸው ። ዕለት ዕለት ይህን ይመስሉ ይሆን ? እያሉ የወላጆቻቸውን ሥዕል ሲስሉ ያለማቋረጥ በውስጣቸው ያወራሉ ። ያንን ስሜት ገልጦ መናገር አሳዳጊዎቻቸውን የሚያስቀይም ስለሚመስላቸው ዝም ይላሉ ። በአገራችን ያለ አስተዳደግ መናገርን እንደ ብልግና የሚቆጥር በመሆኑ እንደ ፍግ እሳት ውስጥ ውስጡን እየነደድን እንድናልቅ አድርጎናል ። የአገራችን አስተዳደርም መናገርን የሚፈቅደው ሲሰክሩና ሲያብዱ ብቻ በመሆኑ የታመቀ ስሜት የእኛ መገለጫ ሁኗል ። ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲመጡ ነገራችን ዕርቃኑን የወጣው ተደብቀን ማውራት ስለቻልን ነው ። ይህ ሁሉ ገመና ለምን አደባባይ ተሰጣ ? ስንል የታመቀ ስሜት በተገቢው መንገድ ካልተነፈሰ የሚያጥለቀልቅ ጎርፍ ስላለው ነው ።
2- ያልወጣ ኀዘን
ወዳጆችን በሞት በማጣት የሚመጡ ኀዘኖች አሉ ። አንዳንድ ሰዎች አታልቅሱ ተብለው በመከልከላቸው ፣ ሌሎች ሃይማኖተኛ ሰው አያለቅስም ብለው በማሰባቸው ፣ የቀሩት ዘመናዊነት መስሏው በጥቁር ቲሸርትና ኮፊያ ልቅሶውን እንደ በዓል በማሳለፋቸው ውስጣቸው ኀዘን ይሰነቀራል ። ከሰው ጋር ማልቀስ ኀዘንን ያወጣል ። ከሰው ጋር ጠንካራ መስለው ሰው ሲሄድ ብቻቸውን የታመቀ ስሜት ውስጥ የሚገቡ ብዙዎች ናቸው ። በአገራችን ያለው የተለያየ የልቅሶ ባሕል ኀዘንን የሚያወጣ ነው ። ኀዘን ካልወጣ ጭንቀት እየሆነ ይመጣል ።
3- ጉዳት
ሰው ሁኖ በሰው ያልተጎዳ ሰው ማግኘት ከባድ ነው ። ከቅርብ ዘመናት ወዲህ በአገራችን መጎዳዳት የዕለት ሥራ ሁኗል ። የእኔ ህልውና ያለው በእገሌ መጥፋት ውስጥ ነው በሚል ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ውስጥ የገባን ይመስላል ። በሰዎች የተጎዱ ሁሉን ሰው በመሸሻቸው የታመቀ ስሜት ውስጥ ይገባሉ ።
4- ብቻዬን ነኝ ብሎ ማሰብ
የሚሰማኝ ስሜት ፣ የሚሰማኝ እኔን ብቻ ነው ብሎ ማሰብ የታመቀ ስሜት ይወልዳል ። እንደ እኔ የሚሰማው ግን እልፍ ነው ። እንኳን አንድ ዓይነት መከራና መረጃ ባለበት ዘመን የሚኖሩ ይቅርና የዛሬ ሦስት ሺህ ዓመት በፊት የነበረው ሰው ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ስሜት አለው ። ያ ባይሆን አንድ እውነት የዘመናት ፈዋሽ አይሆንም ነበር ።
5- ምሥጢር ሲባክን
አምነን የነገርነውን ምሥጢራችንን ሸቀጥ አድርጎ በአደባባይ ሲቸረችረው ፣ ይቅርታችን እንደ ውርደት ሲቆጠርብን የታመቀ ስሜት ውስጥ እንገባለን ። የታመቀ ስሜት ጨካኝ ፣ መራራ ፣ ኀዘነተኛ ፣ ብስጩ ፣ ተበቃይ ፣ ተጠራጣሪ ያደርጋል ። ከታመቀ ስሜት ለመዳን የሚሆነው ነገር ሲሆን የነበረ መሆኑን ማሰብ ይገባል ። አዲስ ሰው እንጂ አዲስ መከራ የለም ። በይቅርታ ያለፈውን ዘመን ፋይል መዝጋት ፣ ለሚመጣው መጠንቀቅ መፍትሔ ነው ። ከሁሉ በላይ ቀጥሎ ያሉት ሁለት ነገሮች አስፈላጊ ናቸው ። የመጀመሪያው እንደ እኛ የሚሰማውን ሰው ማግኘት ሲሆን ሁለተኛው በሕይወት ትግላችን ውስጥ አልፎ ድልን ያስቀመጠልንን ክርስቶስ ጌታችንን ማሰብ ነው ።
አቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፍጽምትና ጽንዕት በምትሆን ባንተ ሰላም አስበን !
ወስብሐት ለእግዚአብሔር