የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአሳብ ውጊያ/11

8- ሥራ ፈትነት

ዕረፍት የማጣትን ያህል ሥራ ፈትነት ለአሳብ ውጊያ ይዳርጋል ። የሰው ልጅ አእምሮ በትላንት ፣ በዛሬና በነገ አሳቦች የተሞላ ፣ ልጅነትን ከሽምግልና ፣ ፍቅርን ከበቀል ጋር ለማስታረቅ የሚታገል ነው ። ጽድቅና ኃጢአት ሰልፍ የሚያደርጉበት ትልቁ የትግል ሜዳ ልቡና ነው ። ወቀሳ ፣ ፍርድ ፣ ክስ ፣ ፍቅር ፣ ጠብ ፣ ቸርነት ፣ ስስት በይገባኛል ስሜት ሊቆጣጠሩት የሚፈልጉት ልቡናን ነው ። አሳብ ሰውን ትልቅ ፍጡር የሚያደርገው ቢሆንም በዚህ ዓለም ላይ ባካና ያደረገውም እርሱ ነው ። የሰው ልጅ በአሳቡ ሁሉን ቻይና ምሉዕ በኵለሄ ለመሆን የሚጥር ፣ በወቅታዊነትና በዘላለማዊነት መካከል አሳቡ የሚዋዥቅበት ፍጡር ነው ። ዕረፍት በማጣት ራሱንና ቤተሰቡን ይከስራል ። ብዙ ትዳሮች የሚፈቱበት አንደኛው ምክንያት ዕረፍት በማጣት ሲባክኑ ነው ። ለጓዳው ሲጨነቅ ቤቱ በሙሉ ይፈርሳል ። ቤት የሚቆመው በገቢ ብቻ ሳይሆን በፍቅርም ነው ። ልጆችም በወላጅ ተስፋ ቆርጠው መረን የሆነ ሕይወት ውስጥ የሚገቡት ከወላጆች ጊዜ ሲያጡ ነው ። ዕረፍት ያጡ ሰዎች ጤናቸውንም ይከስራሉ ። ማኅበራዊ በረከትንም ያጣሉ ። ቁሳውያን እንጂ መንፈሳውያን መሆን ይሳናቸዋል ። በዚያው ተቃራኒ ሥራ ፈትነት ለሰይጣን ውጊያ የሚያጋልጥ ነው ። የአሳብ ውጊያዎችን ድል ከምንነሣበት ቀዳሚው ጸሎት ሲሆን ተከታዩ ሥራ ነው ።

ሥራ የሰው ልጅ የተፈጠረበት ዓላማ ነው ። ሥራ ርግማን ሳይሆን በረከት ነው ። ሥራ እንጀራችንን በጣዕም እንድንበላው የሚያደርገን ፣ ከትግል በኋላ የሚገኝ ድልና ምርኮ ነው ። ይህ ዓለም በስድስት ቀን ቢፈጠርም በየቀኑ አዲስ ነገርን እንዲያገኝ እግዚአብሔር ሥራን ለሰው ልጅ መድቧል ። ለመሥራት አስገዳጁ ሆድ ብቻ መሆን የለበትም ። ሁሉም ነገር ቢሟላም የሰው ልጅ የሚሠራው ነገር በግድ ያስፈልገዋል ። የተሰጠን አካል ካልሠራንበት የባከነ ተፈጥሮ ይሆናል ። ሥራ ከሌለ አጥንታችን መሳሳት ፣ ጡንቻችን መርገብ ይጀምራል ። ደማችን በቅጡ አይዘዋወርም ። ከመኝታችን ለመነሣትና ለመልበስ ድፍረት አይኖረንም ። ሁሉም ሰው በደጅ የሚገናኘው ሥራ ስላለ ነው ። ሥራ ማኅበራዊ ኑሮን ፣ የሰው ለሰው ግንኙነትን የሚያፋጥን ነው ። እስከ ሽምግልና ጠንካራ ሁነው ፣ በሽታን ተዋግተው የሚኖሩ ሰዎች የሚሠሩ ሰዎች ናቸው ። ተግባረ ዕድ እንኳን ለሰብአ ዓለም ለመናንያንም እጅግ አስፈላጊ ነው ። ጭንቀት የሚበረታው ሥራ ስንፈታ ነው ።
የሚሠራ ሰው ለችግር ከመጨነቅ ይልቅ መፍትሔ ይፈልጋል ። የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ለመስጠትም ሥራ አስፈላጊ ነው ።

ሥራ ደመወዙ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ ጥቅሞች አሉት ። አእምሮን የሚያሳርፍ በመሆኑ ሥራ ሊወደድ ይገባዋል ። ማሰቢያ አእምሮ ፣ መሥሪያ እጅ ተቀብለናልና አለመሥራት ኃጢአት መሆኑን ማወቅ ይገባናል ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አርአያ ለመሆን ድንኳን እየሰፋ አገልግሎቱን ያግዝ ነበር ። ጌታችን ሥጋ ለብሶ በመጣ ጊዜ የአናጢነት ሥራን ይሠራ ነበር ። ሰይጣን የወደቀው ፣ ሌሎችንም የሚጥለው በሥራ ፈትነቱ ነው ። አለማመስገን አለመሥራት ነውና አላመሰግንም ብሎ ወደቀ ። አሁንም ምንም ሥራ ስለሌለው ሲያስት ይኖራል ። እንደ ሥጋ ለባሽ ሆድ የሚባል ጣጣ ቢኖርበት ኖሮ ሰይጣን ክፋቱን ይቀንስ ነበር ። “የሰይጣን ሌላ ስሙ ስንፍና ነው ።”

“ሥራ ከምፈታ ፣ ልጄን ላፋታ” ይባላል ። ሰው ሥራ ሲፈታ ለሌሎች ሰላም አይሰጥም ማለት ነው ። ሔዋን የኃጢአትና የሞት በር ሁናለች ። ሰይጣን የጣላት ሥራ ፈትታ ፣ ከኅብረት ተነጥላ አግኝቷት ነው ። ለሰይጣን ማታለልና ለከንቱ ምኞት ተላልፈው የሚሰጡ ሰዎች ሥራ ፈቶች ናቸው ። ሽብርንና ሌብነትን ሲያቅዱ የሚውሉ እጆቻቸው በሥራ እንዲሻክሩ የማይፈልጉ ናቸው ። እጆች ሲለሰልሱ ልብ ሸካራ ይሆናል ፣ የሻከሩ እጆች ያሏቸው ለስላሳ ልብ አላቸው ። ሌሎች የሠሩትን እየፈለግን ሥራን መጥላት አይገባንም ። ይልቁንም መብል ወድዶ ሥራ ጠልቶ የሚሆን ነገር አይደለም ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” በማለት ቍርጥ ያለ ትእዛዝ ሰጥቷል ። 2ተሰ. 3፡10 ።

ምንም ሥራ ባይኖረን ንጹሕ ልብሳችንን ደግመን ማጠብ መልካም ነው ። ደግሞም እኛ ለእኛ ሥራ ነን ። ከራስ ፀጉራችን እስከ እግር ጥፍራችን ድረስ ሥራ ነን ። ፀጉርን ማበጠር ፣ ፊትን መታጠብ … ይህ ሁሉ ሥራ ነው ። አካባቢያችንን ማጽዳት ፣ ያለንን ንጹሕ አድርጎ መልበስ ለሥራ ተፈላጊ ያደርገናል ። ሥራ የማይሠራ ሰው ወይም ሥራ ፈት አእምሮ ያለው ሰው የሌሎችን ደመወዝ ሲቆጥር ይውላል ። በማይመለከተው በሰው ነገር ውስጥ ይገባል ። አፉና ልቡ ከመፍረድ አያርፉም ። ስለማይሠራ አይሳሳትምና የተሳሳቱ ሰዎችን ሲያገኝ ምሕረት የለውም ። ምናልባት ጡረታ ወጥተን ከሆነ ፣ አሁንም ሥራ አለንና ሥራችንን መፈለግ አለብን ። ተምረን ተመርቀን ሥራ አጥተን ከሆነ በማንበብ ፣ በጎ አድራጎቶችን በጉልበት በማገዝ ፣ በመጸለይ መትጋት ይገባናል ። ነግቶ መተኛት ፣ ወፎች ሲዘምሩ ማንኮራፋት ለክርስቲያን ተገቢ አይደለም ። ከገንዘብ በፊት ግንዛቤን ማዳበር ገንዘቡ የመጣ ቀን የምናውልበትን ያሳየናል ። እውቀት የሌለው ሀብት አጥፊ ነው ። አንዲት መንፈሳዊ እኅት፡- “እውቀት የሌለበት ሀብት ወይ በታኝ አሊያም ስስታም ያደርጋልና ተማሩ” ብላለች ። “ጀብድ የማትሠራ ነፍስ እንቅልፋም ናት ።”

ወጣቶች ዛሬ እውቀትን ፣ ነገ በረከትን እንደምታገኙ አስቡ ። እግዚአብሔር የእጆቻችሁን ሥራ ያቅና ። የማይሰፈር በረከቱ ከእናንተ ጋር ትሁን ። መሥራት ለነገ ትውልድ ማሰብም ነው። የማይሠሩ የትላንቱን ያፈርሳሉ ፣ የነገን ያበላሻሉ ። “በአባቶቻቸው የማይኮሩና ለልጆቻቸው የማይጨነቁ በቅሎዎች ናቸው ።”

አዎ የአሳብ ውጊያ ከሚያመጡ ነገሮች አንዱና ዋነኛው ሥራ ፈትነት ነው ። “ሥራ የፈታ አእምሮ የሰይጣን ወርክሾፕ ነው” ይባላል ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ