የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዓላማ

 

ዓላማ ባለፈው ቀን ላይ የተቀመጠ ትዝታ ሳይሆን በሚመጣው ቀን ላይ ያለ ተስፋ ነው ። ዓላማን ከተስፋ ልዩ የሚያደርገው የተስፋ ፈጻሚው ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔር ነው ፤ ዓላማ ግን ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራው ነው ። ዓላማ እግዚአብሔር ያውቃል ብሎ መቀመጥ ሳይሆን በጨለማ ጉዞውን ጀምሮ ቀትር ላይ መድረስ ነው ። ዓላማ ወዳጅንና ጠላትን ፣ ክፉና ደግ በመለየት ይጀምራል ። ዓላማ ከክፋት ጋር ዘላለማዊ ጦርነት እንዳለው ያውቃል ። ዓላማ ኳስ ሜዳ ሳይሆን ጦር ሜዳ ነው ። ጠላት ምኞትን ፣ ወሬን ፣ ፉከራን ፣ እቅድን ሳይሆን ዓላማንና ባለ ዓላማን ይፈራል ። ቆንጆነት ዓላማ አይደለም ፣ የተቀበልነው ነው ። ዓላማ ግን የምንቀበለው መዳረሻችን ነው ። ልጆችን መውደድ ዓላማ አይደለም ፣ ልጆችን ለአገርንና ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ አድርጎ ማሳደግ ግን ዓላማ ነው ። 

ዓላማ ከስኬት በላይ ነው ። ሰዎች ስኬት ላይ ደርሰው ቤትና ንብረት ሊኖራቸው ይችላል ። ቤትና ንብረት የሌለው ባለ ዓላማ ግን ከሁሉም ይበልጣል ። ዓላማ ሰውን ታሳቢ የሚያደርግ ነው ። እኔና የእኔ ከሚለው ጥበት የወጣ ነው ። ሰውን ጠልቶ ተራራና ወንዝን መውደድ ዓላማ አይደለም ። ዓላማ ባሻገር ያለውን ማየት በመሆኑ ለሌላ ሰው መኖር ለሌላ ዘመን ማቀድ ነው ። ዓላማ ዘር ነው ። ዘር ካልተዘራ አይበቅልም ፣ ዓላማም ካልተጀመረ ትውልድን አይዋጅም ። ዘር በዚህ ዓመት ተዘርቶ በሌላ ዓመት ይታጨዳል ። ዓላማም እኛ ጀምረነው ሌላው ትውልድ ፍሬውን ሊበላው ይችላል ። ዛሬ ያልተጀመረ ነገ አይፈጸምም ። የዓላማ ቀን ዛሬ ነው ። የትዳር አሳብ ፣ የልጆች ቍጥር እርሱ ዓላማ አይደለም ። ዓላማ የእኔ ለማንለው አገርና ወገን መኖር ነው ። ሀብታምነትና አባወራነት ስኬት እንጂ ዓላማ አይደለም ። ዓላማ ማሰብ ይጠይቃል ፣ ሀብት ግን ሳያስቡ ከቤተሰብ ይወረሳል ። 

ዓላማ ዓይንና ጆሮን ለእግዚአብሔር ማዋስ ነው ። እግዚአብሔር በእኛ ዓይን ምስኪኖችን ያያል ፣ በእኛ ጆሮ የተከፉትን ይሰማል ። ዓላማ ሲጀምሩት ጨለማ ፣ ሲዘሩት ማጥ ያለበት ነው ። የሚታይና የሚረገጥ ነገር የለውም ። ዘር ከቤት ወጥቶ ከተዘራ በኋላ ፈተናው ይበዛል ፣ የዝናብ እጥረት ፣ ውርጭ ፣ አረም ፣ ተምች ፣ አንበጣ ይመጣበታል ። ዓላማም ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ ፈተና ይገጥመዋል ። “የእሳትና የጠላት ትንሽ የለውም” የሚለውን አባባል በትክክል የሚተገብረው ሰይጣን ነው ። ስለዚህ ባለ ዓላማ ስንሆን ገና በጠዋቱ ይፋለመናል ። ዓላማ ፈተና ከሌለው ዓላማ አይደለም ። 

ለዓላማ ሕይወትን መስጠት ፣ ዓላማን በትክክል ማወቅ ፣ የጊዜ አጠቃቀምን መልመድ ፣ ተስፋ ማድረግ ፣ ባሻገር ማየት ፣ ፈተናዎችን እንደ መሰላል መቍጠር አስፈላጊ ነው ። ዓላማ ዒላማ ነው ። ዓላማ ሰንደቅ ዓላማ ነው ። “ሂትለር በጨካኝነቱ ፣ እማሆይ ትሬሣ በደግነታቸው ይታወሳሉ ። እኔ ግን በምን እታወሳለሁ ?” ብለን ራሳችንን እንጠይቅ ፤ ቀኑ ዛሬ ነው ። 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን 

ሐምሌ 23 ቀን 2013 ዓ.ም.

እውነት 3

ለልባችሁ የቀረላችሁን አሳብ እስቲ ግለጡ ። እግዚአብሔር ፊቱን ያብራላችሁ !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ