ቤተ ጳውሎስ፤ ሚያዚያ 9 2004 ዓ.ም.
በዳቦ አላስቆረስኩም
ገድሎ ማዳን ሳይሆን ፣ ሞቶ ማዳን ማለት
ምን ዓይነት ስሌት ነው ፣ ምን ዓይነት ጀግንነት?
ተወልዶ ያደገው ፣ በመስቀል የሞተው ፣ ደግሞም የተነሳው
የማዳን ክዋኔው ፣ ጥበቡ ስውር ነው ምሥጢሩም ጥልቅ ነው
ስለፈሩት አይደል ፣ ወይ ስለተወደደ
ስለ ፍቅር ብሎ ፣ ከሰማይ ወረደ
ነጻነት ለማወጅ ፣ በራሱም ፈረደ
ሰው ሆነና ሞተ ፣ ለጥቆም ተነሳ የሚለው ቃላችን
መሠረቱ ይኸ ነው ፣ ድኅነተ እምነት ፣ በክርስትናችን
አምላክ የወደደን እኛ ስንከዳው
ይህን ያስፈጸመው ፣ ምክንያቱ ምንድነው?
ከተከታተልነው ፣ ነገሩ እንዲህ ነው
ሁሉን አስተካክሎ ፣ ሁሉን አሟልቶለት
በአምሳሉ ፈጥሮ ፣ ሲያኖረው በገነት
ህያው እንዲሆንም ፣ እስትንፋሱን ሰጥቶት
እባብ አሳመጸው ፣ መስሎ ያዘነለት
ተንኰልን አስቦ ፣ በጸጋው ቀንቶበት ፤
እንዲያው ለመሆኑ ፣ ፈጣሪ ምናለ?
ምንን ፈቀደልክ ፣ ምንን ከለከለ ?
እያለ ጠየቀ ፣ ያዘነ መሰለ ፣
በዓይኑ አባብሎ ፣ እየሸነገለ
ሴት በየዋህነቷ አስረዳች በዝርዝር
እንዳልተከለከሉ ካንዲቷ ዛፍ በቀር
ይህችን ዛፍ እኮ አትብሉ ያላችሁ
እንዳታውቁበት ሁሉን ለይታችሁ
ክፉና ደግ ይህ ነው ማለት ከቻላችሁ
እንግዲያውስ ከርሱ በምን ታንሣላችሁ?
አምላክ እንዲሆኑ ፣ ፍሬን የበሉ ዕለት
ማለ ተገዘተ ፣ ሞልቶት ምቀኝነት ፣
አዳምም እንዳሉት ፣ የበለስን ፍሬ ፣ በላ እያጣጣመ
በነዚህ ምክንያቶች ፣ ትእዛዝ አፈረሰ ፣ በደልን ፈጸመ።
አዘነ ፣ አለቀሰ ፣ ጸጋው ተገፈፈ
ራቁት መሆኑን ለሔዋን ለፈፈ
ቅጠልን ለበሱ ሱባዔ ቆጠሩ
ይቅር እንዲላቸው ፣ ጾም ጸሎት ጀመሩ /ስለ ቁም ነገር የታከለ/
እግዜርም ያዳምን መሸሸጉን አውቆ
ሃዘን ከቁጣው ጋር በአንድነት ደባልቆ
አዳም በማጥፋቱ ፣ በጣሙን አዝኖበት
ጠባቂ አቆመ ከገነት አባሮት ፣
የሞት አዋጅ ወጣ ፣ በይፋ ታወጀ
የሞት አዋጅ ወጣ ፣ በይፋ ታወጀ
ለሰው ዕድሜ ሁሉ ፣ ገደቡ ተበጀ
ስለ ጸሎታቸው ፣ ስለጸጸታቸው ፣ ቃሉንም ሰጣቸው
ከልጅ ልጅ ተወልዶ ፣ እንደሚያድናቸው
ወድቀው ስለቀሩ በእባብ ተታለው
የዘር ቅራኔውም ፣ ተዘራ መሃላቸው
ወደ ዓለም ተጥሎ ፣ መከራው በዛበት
ሃሩሩና ቁሩ ፣ ረሃብ ከድካም ጋር ፣ ተፈራረቁበት
ሁሉንም አሰበ ፣ ለማግኘት መድኀኒት
ወደ ጥንት ክብሩ ፣ የሚመለስበት
ከፈጠረው አምላክ ፣ የሚታረቅበት
ጀግናው እስከሚገኝ ፣ ንጉሡ እስኪመጣ ፣ ዘመን ሰነበተ
የአዳም ዘር በሙሉ ፣ መላን በመፈለግ ፣ በእጅጉ ታከተ
ተስፋውን ቆረጠ ፣ ራሱን አወቀ ፣ አቅም እንደሌለው ፣
ተማጸነ አምላኩን ፣ አንዴ እንዲያድነው ፣
ማለ ተገዘተ ሌላም እንዳይለምደው
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ፣ አንድ ሁነው መከሩ ፣ አንድ ሁነው አሰቡ
ፍርድ ሳይቀለበስ ፣ ይቅርታን ለማምጣት ፣ እጅግ ተጠበቡ
ገብርኤልን ተልኮ፣ ብሥራት አቀረበ
ቃለ እግዚአብሔር ፣ በድንግል አደረ
ወልድ አምላካችንም ከድንግል ተወልዶ ፣ እንደኛው ሰው ሆነ
ዓለም የማትበቃው ፣ የፍጥረት ፈጣሪ ፣ በእቅፍ ተመጠነ
መድኅን እንደሚሆን ፣ ቀድመው ስላወቁት
የፊተኛውን ቃል ፣ ኢየሱስ ነህ አሉት
ሥጋን በመዋሃድ ፣ ፍጹም ሰውን ሆነ
ጥምቀትን ተጠምቆ ፣ ጽድቅንም ከወነ
ከቆሮንቶስ ሄደ ፣ መከራን ቀመሰ ፣ ስለዓለም መነነ
በሥጋ ባህርዩ ፣ ደከመ ተጠማ ፣ በራብ ተፈተነ
ሥራውን ባረከ ፣ መንገዱን ቀደሰ
ህዝብን ለማስተማር ፣ ሥርዓትን ቀየሰ
ድውይን ፈወሰ ፣ በመንፈስ አከመ
ትንግርትን አሳየ ፣ ታምራት ፈጸመ
የጠፋ ወገኑን ፣ እንደገና ሊያድስ
የወደቀ አዳምን ፣ ዳግመኛ ለማንገስ
በመስቀል ላይ ዋለ ፣ ሞትንም ሞተልን
በተስፋው ቃልና በወደደን መጠን
በመስቀል ላይ ሞተ ፣ ደሙን አፈሰሰ ፣ ድልን ተቀዳጀ
ካሳው ተከፈለ ፣ ዳናችሁ ተባልን ፣ አዋጁም ታወጀ
ሞት በሞት ተሻረ ፣ ኃጢአት ተቀበረ
ገነት ተከፈተች ፣ የአዳም ዘር ከበረ
ለልጅ ልጁ ሁላ ፣ ብሥራት ተነገረ
ሲዖል ተከፈተ ፣ ስሙ ተሰበከ ፣ ነፍሳት ተለቀቁ
ሰይጣን ድል ሆኖ ፣ ሲታሰር ሲመታ ፣ እነሱ ቦረቁ
ከእንግዲህ በኋላ በኢየሱስ ስም አምነን
ትንሣዔ ስላለን እስከ ዘለዓለም እኛም እንድናለን።
ከጥፋቴ በልጦ ፣ የታደልኩት ምህረት በብዙው ረድቶኝ ፣
ልብ እንድገዛና አምኜ እንድድን የዛሬን ቀን ሰጥቶኝ
ከገባሁበትም ፣ ከድካም አረንቋ ፣ በድሉ አወጣኝ፡፡
ስለዚህ ወገኖች ፣ አበርቱኝ አጽናኑኝ ፣ ፈቃዱን ልፈጽም
ኃጢአቴን ቀብሬ ፣ የኔዋም ትንሣዔ ፣ ከሱው ጋር ትፈጸም ፡፡
በሞተልኝ ጌታ ፣ እምነቴ ይጠንክር ፣ ይሄ ቀን ሳይጨልም ፡፡