የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 20/

 

እባካችሁ አንብቡ

ቀኑ ሐምሌ 5/67 ዓ.ም. ነው ። የቄሣር አደባባይ በብዙ ሕዝብ ተጨናንቋል ። ሮማ እርድ እንዳገኘ አውሬ ደስታና ዝላይ ላይ ናት ። የጴጥሮስና የጳውሎስ የሞት ፍርዳቸው ሊሰጥ ስለሆነ ከቤቱ የቀረ ሰው ያለ አይመስልም ። በክርስቲያኖች እንደ ዋና የሚታዩትን ፣ የእናት ቤተ ክርስቲያን የኢየሩሳሌም ሐዋርያ የሆነው ቅዱስ ጴጥሮስ ፣ ለአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ሐዋርያ የሆነው ቅዱስ ጳውሎስ በሞት ፍርድ ሊቀጡ ነው ። ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ በሰማዕትነት በቃልና በደም ምስክርነታቸውን ሊያጸኑ ነው ። ገዳይ ልከኛ ሟች ጥፋተኛ ይመስሉ ይሆናል ። የእውነት ሀገሯ ግን በሰማይ ነው ። በምድር እንጀራ የሚሰጡ በሰማይ ግን እንደሚለምኑ ከባለጠጋው ከነዌ ፣ በምድር የሚለምኑ በሰማይ ግን እንደሚያርፉ ከድሀው ከአልዓዛር አይተናል ። የምድር ፈራጆች በሰማይ ተፈራጆች ፣ የምድር ከርታቶች በሰማይ ግን ጌቶች ናቸው ። የዕለት እውነትና የዘላለም እውነትን የሚጠሉ ሰዎች ለመግደል ጠብ እርግፍ ይላሉ ። የአንዳንድ ሰው ትጋት የእግዚአብሔርን ሰው ለመግደል ነው ። መቅረዝ ለራሱ እንደማያበራ የእግዚአብሔር ሰውም ለሌላው የሚያበራ ነው ። የእግዚአብሔርን ሰው የሚገድል በራሱ ላይ መብራት የሚያጠፋ ነው ። ቢሆንም አውራ ዶሮ ለራሱ ሳይነቃ ሌላውን አይቀሰቅስም ። 

አማልክቶቻችን በክርስቲያኖች ምክንያት ተቆጥተው መዓት አመጡብን ብለው የሚያምኑ እግረ ደረቅ እያሉ የሚጠሉአቸው ክርስቲያኖች ሲሞቱ ለማየት ፈልገዋል ። በ64 ዓ.ም በበጋው ወራት ሮምን ያቃጠለውና ብዙ ሕዝብም እንዲሞት ምክንያት የሆነው ኔሮን ፣ የሕዝቡን ቍጣ ለማብረድ ክርስቲያኖች አቃጠሉት ብሎ አስወርቶ ነበር ። ንብረታቸውንና ወገኖቻቸውን ያጡ ሮማውያን የጴጥሮስንና የጳውሎስን ሞት ለማየት በደስታ ተከማችተዋል ። ክርስትና ግን በጴጥሮስና በጳውሎስ ተሰበከ እንጂ አልተመሠረተም ። በልቤም አንድ ግጥም መጣና ፎክር ፣ ፎክር አለኝ፡-

ዛፍ ቢቆረጥ ያበቅላል ቍጥቋጦ ፣

አምሳሉን ይተካል አይቀርም ተቆርጦ ።

ክርስትና በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሠረተች በመሆኗ አናቅጸ ሲኦል አይችሉአትም ። ኔሮን ግማሽ እብድ እየተባለ ይጠራ ነበር ። ቤተ መንግሥቱን ለማስፋፋት ሮምን በግማሽ ያቃጠለ ፣ ከተማይቱ ስትነድድ አፋፍ ላይ ሁኖ ይመለከት ነበር ። ሙሉ እብድ እንዳይሉት በዙፋን ያለው እርሱ ነው ። ጤነኛ እንዳይሉት መናገሻ ከተማውን አቃጥሎ የሚስቅ ፣ ከተማውን ሁሉ የግሉ ቤተ መንግሥት ለማድረግ የማይሰቀቅ ነበር ። 

የወጣውን ብዙ ሺህ ሕዝብ ባየሁ ጊዜ በጳውሎስ ቤት የተማርነውን ጥቂት ምእመናን አሰብኩና ተገረምኩ ። ስናስተምር አምስት ሰው ይመጣል ፣ ስንሞት ግን አምስት ሺህ ሰው ይመጣል ብዬ አዘንሁ ። 

በድንገት ታላቅ ሁካታ ሆነ ። ጴጥሮስና ጳውሎስን እያዳፉ ወደ ፍርድ አደባባይ አመጧቸው ። ጴጥሮስ አርጅቷል ። ጳውሎስም በዕድሜና በበሽታ ተደቁሷል ። የመገናኛው ድንኳን ላይዋ መልክ የለሽ ነበር ፣ በውስጥዋ ግን ውድ ወርቅ የያዙ ብዙ ንብረቶች ነበሩ ። ክርስቲያንም ላዩ አያምርም ፣ ውስጡ ግን ወርቅ ነው ። ላያቸው የሚያምሩ እንደ ኤልያብ እግዚአብሔር የናቃቸው ናቸው ። /1ሳሙ. 16/ እግዚአብሔር የቁመት ዘለግታ አይማርከውም ። እምነት እንጂ ቁመት እግዚአብሔርን አያይም ። ኤልያብ ያላየውን ጌታ አጭሩ ዘኬዎስ አይቶታል ። በዚህ ጊዜ አሻግሬ ማሰብ ጀመርሁ ። ሐምሌ አምስትን በየዓመቱ የጴጥሮስና የጳውሎስ መታሰቢያ ብለን ልንሰይማት ነው ብዬ ተደሰትኩ ። በሮማ ግዛት የጣዖታት ፣ የቄሣሮች ፣ የበሽታ ቀን ተብሎ ይከበራል ። የቅዱሳን በዓል ቢከበር ሰማዕት መመልመያ ፣ ድሀ መመገቢያ እንጂ ምን ክፋት አለው  ግኖስቲካዊ ኑፋቄ ያጠቃቸው ፣ እምነትና ፍልስፍናን ያጋቡ ሰዎች ግን ሁሉን አምርረውብን ምልምል ዛፍ ያደርጉናል ። ስለሚገፍፉን ሥርዓት እንጂ ስለሚያለብሱን ካባ አያስቡም ። 

የሞት ቅጣት በሚፈጸምበት አደባባይ ከታወቁ ጨካኝ ወታደሮች በቀር ማንም እንዲቆም አይፈቀድም ። ከሟቾቹ ጀርባ የንጉሡ ሰገነት አለ ። ሕዝቡም ሟቾቹን ፣ ከጀርባ ደግሞ ፈራጅ የሆኑትን ባለሥልጣናት ይመለከታል ። የኔሮን መምጣት እየተጠበቀ በመሆኑ ዕርቃናቸውን በአደባባይ እንዲቆሙ ተደረገ ። በየዋሻ ተደብቀው ነበሩ ክርስቲያኖች ይህን ፍርድ ሊያዩ አደባባይ ወጥተዋል ። ክርስትና በክርስቶስ ደም የተዘራች በሰማዕታት ደም ያፈራች የእውነት ዘር ናት ። ይህ ቀን ዓለም እንደምታስበው እሳቱ የሚጠፋበት ሳይሆን የሚቀጣጠልበት ቀን ነው ። በምድር ላይ ሞቱ የሚባሉት እነዚህ አባቶች በሰማይ ግን የሰርግ ቀናቸው ነው ። በሰማይ ዕድሜ ያለው ረጅም ሞት ተብሎ የሚጠራው የእኛ የምድር ኑሮ ነው ። አንድ ነገርን ከምድርና ከሰማይ ሲያዩት ይለያያል ። በሰማያዊ ስፍራ መቀመጥ ማለት ከዚያ ሁኖ ዓለምን ማየት ነው ። ሁሉም ነገር ትንሽ ነው ። 

ኔሮን የክብር ቦታውን ያዘ ። ታላቅ ሁከትና ጭብጨባ ተሰማ ። አምባገነኖች ሕዝቡ ፈርቶ ሲያፏጭላቸው የሚወዳቸው ይመስላቸዋል ። ትላንት የገዛ ወዳጆቻቸውን ሳይቀር በልተው የመጡ ናቸውና ፣ ለእኔ አይመለሱም እያለ በፍርሃት ሕዝብ ሲያጨበጭብላቸው እውነተኛ ክብርና ፍቅር አድርገው ያስቡታል ። አምባገነኖች ትንሽ ጠብን አይንቁም ፣ ለሕዝቡ ግን ተራራ የሚያህል መከራ አሸክመውት እንደሚወድዳቸው ማሰባቸው ይገርማል ። አምባገነኖች “እኔነት” ለሚባል ጣዖት ወደ ራሳቸው የሚያጥኑ ናቸው ። ወደ ራሱ የሚያጥን አሁን ዕጣኑን ፣ ቀጥሎ እሳቱን ይቀበላል ። ሮማ የሞት ፍርድ የፈረደችበትን አንድ ቸርነት ታደርግለታለች ። የመጨረሻ መልእክቱን እንዲያስተላልፍ ዕድል ትሰጠዋለች ። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም እንዲናገር ዕድል ተሰጠው፡- 

“ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል ። ከኖርኩበት ኑሮ ይልቅ ለምወደው አምላክ መሥዋዕት በመሆኔ ክብር ይሰማኛል ። ምሴተ ሐሙስን የምበቀልበት ቀን ስለሆነ ደስታዬ ወደር የለውም ። ሞትን ፈርቼ የሸሸሁ ስሆን አሁን ግን ሰማዕትነት እንዳያመልጠኝ ወደ ሮም መጥቻለሁ ። የትላንት ፈሪ የዛሬ አማኝ ነኝ ። ሮምን ከዚህ በፊት አይቻት አላውቅም ። ባያት በሰማዕትነት ተቀበለችኝ ። ከዚህ በፊት አይቻት የማላውቃት ሰማይ ግን በአክሊል ትቀበለኛለች ። እኔ አርፋለሁ ክፉ ፈራጆች ግን ትሰቃያላችሁ ። ገዳዮች ያኔም ነበሩ ዛሬም አሉ ። ወደፊትም ይኖራሉ ። ፍጻሜአቸው ግን አያምርም ። የሚታይ ኃጢአት የሚሠሩትን የማይታይ ቅጣት የሚሰጠው አምላክ አለ ። እርሱ ልብና ኩላሊታቸውን እየወጋጋ ይቀጣቸዋል ። የሚያያቸው ሰው ግን አልተቀጡም ብሎ ያስባል ። እግዚአብሔር ግን ጅራፉ ልዩ ልዩ ነው ። አንዱን በወኅኒ አስሮ ሌላውንም በሕሊናው ቸንክሮ ይቀጣዋል ። እናንተ በጨከናችሁ ቍጥር እኛም ለማመን እንጨክናለን ። ሮማ በከፋች ቍጥር ሰማዕታት አያቆሙም ። ሰማዕትነት የሚበርደው ሮማ በራራች ጊዜ ነው ። አንተ ሕዝብ ሆይ ይሾም ሲሉህ ይደልዎ ፣ ይገደል ሲሉህ ይደልዎ የምትለው እስከ መቼ ይሆን ?”

የጴጥሮስን ንግግር መቋቋም ያቃተው ሕዝብ ጮኸ ። የመናገሪያው መድረክም ለጳውሎስ ተሰጠው ። ጳውሎስ ግን በድካም ውስጥ ቢሆንም ታላቅ ደስታ ይታይበት ነበር ። እንዲህም አለ፡-

“እኔ እሞታለሁ ፣ መጻሕፍቶቼ ግን ይቀጥላሉ ። በቁም የቀበራችሁትን በሞቱ ማክበር ልማዳችሁ ነውና በዚህ አደባባይ ላይ ትልቅ መቅደስ ሠርተው ልጆቻችሁ ሲያስቡን ይኖራሉ ። የገዳዮች ሐውልት ይፈርሳል ፣ የሰማዕታት ክብር ግን ይኖራል ። እስከ ዛሬ ካልሰማችሁኝ ዛሬ አትሰሙኝምና ከዚህ በላይ አልናገርም ።”

ወታደሩ ይበቃሃል ብሎ ገፋው ። በዚህ ጊዜ የወታደሮቹ አዛዥ፡- “ጳውሎስ ሮማዊ ዜግነት ስላለው የውርደት ሞት በሆነው በመስቀል አይቀጣም ። ጴጥሮስ ግን በመስቀል ይቀጣል” አለ ። በዚህ ጊዚ ጴጥሮስ ተንበርክኮ እግሩን ይዞ መለመን ጀመረ ። ሁሉም ይሙት ሊሉት ቢመጡም የክርስቲያንን መፍረክረክ ግን ማየት አይፈልጉምና ደነገጡ ። በዚህ ጊዜ ወታደሩ ሳቀና ወደ ቄሣሩ ዞሮ፡- “ክቡር ሆይ፣ እንደ ጌታዬ እንደ ክርስቶስ አትስቀሉኝ ፣ የቁልቁሊት ስቀሉኝ ብሎ እየለመነን ነው” አለ ። ኔሮን ቄሣርም የወደደውን አትንሱት ብሎ ፈገግ አለ ። ወዲያው ወታደሩ ሰይፉን መዝዞ የጳውሎስን አንገት ቀላ ። ጴጥሮስንም የቁልቁሊት ሰቀሉት ። ሕዝቡ በደስታ አጨበጨበ ። ኔሮንና ሕዝቡ በክርስቲያኖች ሞት ቢፋቀሩም ፍቅራቸው ግን ሐሰተኛ ፣ ነፋስ የሚበትነው ገለባ ነበረ ። 

ፍጹም መሞታቸውን ሲያረጋግጡ እንጠጋ ዘንድ ፈቀዱልን ። ተደብቀው የነበሩ ክርስቲያኖችም ዛሬ ትኩረት ውስጥ አይገቡምና ሊያግዙን መጡ ። ጴጥሮስን ወስደን በቫቲካን ኮረብታ ላይ ቀበርነው ። ጳውሎስንም በኦስቲያ መንገድ ላይ ቀበርነው ። ጴጥሮስና ጳውሎስ ሐምሌ አምስት 67 ዓ.ም ዐረፉ ። በረከታቸው ይደርብን ! 

ተፈጸመ

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሐምሌ 5 ቀን 2013 ዓ.ም.

ወድ ወገኖቻችን ለልባችሁ የቀረላችሁን እስቲ ለመጻፍ ሞክሩ ። እግዚአብሔር ከቅዱሳን በረከት ያሳትፋችሁ ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ