‹‹ጎልያድም ዳዊትን፡- በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን አለው? …. ዳዊትም እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ አለው››
፩ ሳሙ ፲፯፣፵፫-፵፭፡፡
የአድዋው ጦርነት ለብዙ አውሮፓውያን የጦርነቱ ታዛቢዎችና ለጦርነቱ ተሳታፊዎች ለኢጣሊያውያንም ጦርነቱ ‹‹የጎልያድንና የዳዊትን ጦርነት›› ታሪክን ከቅዱስ መጽሐፍ ዞር ብለው እንዲያስታውሱ የተገደዱበትን ሁኔታ የፈጠረ ነበር፡፡ እጅግ ዘመናዊ በሆነ ጦር ተደራጅቶ የመጣውን የኢጣሊያን ጦር ለመመከት ከመላው ሀገሪቱ የተሰባበሰበው የኢትዮጵያ ጦር ምንም ዓይነት ዘመናዊ የጦርነት ሥልጠና ያልወሰደና በእጁ የነበረውም መሣሪያ ጦርና ጎራዴ ቢሆንም፣ ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያውያን በልባቸውና በደማቸው ውስጥ ግን ለዳዊት ድልን ያጎናጸፈውና ያን ግዙፍና በጦረኝነቱ መላው ፍልስጤም የሚርድለትን፣ የእስራኤልን ሠራዊት ለ40 ቀናት የተገዳደረውን ጎልያድን በአንዲት ጠጠር ድል ያደረገው የዳዊት አምላክ ኃያሉ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነበር፡፡ የድሉ ምንጭም የእግዚአብሔር ኃይል፣ ኢትዮጵያውን ለሃይማኖታቸውና ለነጻነታቸው የነበራቸው ቀናዒነት እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
አድዋ ላይ በተካሄደው ጦርነት የተገኘው ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው በባርነትና በቅኝ ግዛት የሚማቅቁ አፍሪካውያንና የመላው ጥቁር ሕዝብ ድል ነው፡፡ ይህ ድል በኢትዮጵያ ላይ የተሞከረውን የቅኝ አገዛዝ ሩጫ ከንቱ ያስቀረ፣ በዘመናዊ ትጥቅ፣ በጉልበትና በሠራዊቱ ብዛት ተመክቶ የመጣውን ወራሪውን የኢጣሊያን ጦር ያሳፈረ፣ በአፍሪካ አህጉርና ለነጻነቱ ለሚታገለው ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የእብሪተኞችን የግፍ አገዛዝ ጨለማ ያስወገደ የነጻነት ጎህ ነው፡፡ ባለፉት የሀገራችን ረጅም የታሪክ ዘመናት የተገኙ ድሎች፣ የተፈጸሙና የተመዘገቡ ገድሎች፣ የሰው ልጅ አስደናቂ የፈጠራና የጥበብ ውጤቶች የሆኑ ታሪካዊ ቅርሶችና ሀብቶች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን ጋር የጠበቀ ቁርኝነት አላቸው፡፡
ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን በአካል ተገኝተው የጎበኙ አያሌ የውጭ ሀገራት ዜጎች ስለ ሀገራችንና ስለ ሕዝቦቿ በጋራ የሚመሰክሩት አንድ እውነት አለ፤ ይኸውም፡- ‹‹ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸውና ለነጻነታቸው ቀናዒዎች ናቸው፡፡›› የሚል ነው፡፡ በአንድ ወቅት ታዋቂው የፈረንሳይ ጋዜጠኛ ዳንኤል ሮፕስ እ.ኤ.አ 1963 ዓ.ም ‹‹አክሌዥያ›› በሚባል ጋዜጣ፤ ‹‹የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ታውቃላችሁን?›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ሐተታ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡-
‹‹…ወራሪዎች ምድርዋን በግፍ የያዙባት መሆኑን ታሪክ ያወሳል፤ ነገር ግን ሃይማኖት የእንቅስቃሴዋ መሣሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነጻነቷን መልሳ አግኝታለች፡፡ በማዕከላዊው ክፍለ ዘመን ‹‹የካህን የዮሐንስ ግዛት›› በአረመኔው ዓለም ተከቦ የክርስቲያን ምሽግ ሆነዋል እየተባለ ስለ ኢትዮጵያ ይነገር የነበረው ሁሉ ፍጹም ልበ ወለድ ታሪክ አይደለም፡፡ ከሁለት ሺ ሜትር በላይ ከፍታ ያለውን ደጋማና ለምለም መሬት ቁልቁል የሚያዩት ቀይ፣ ጥቁርና ሰርጥነት ያላቸው የእሳተ ገሞራ ውጤት ባሕርይ ያላቸው ጠረጴዛ መሰል ተራራዎች የጊዜን ውሽንፍር እንዳሳለፉትና የባሕር ዓሣም ሳይበገርና ሳይላላ ማዕበሉን እንደሚያሳልፍ ክርስቲያኒቷ ኢትዮጵያም በታሪክ ውስጥ ጠንካራ ስፍራዋን ይዛ ቆይታለች…፡፡››
ይህ ጋዜጠኛ እንዳለው ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለትና ሦስት ሺህ ዓመታት በርካታ ፈተናዎች አጋጥመዋታል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ከተቃጣው አያሌ የውጭ ወራሪዎች ጥቃት አብዛኛው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተሰነዘረ ነበር፡፡ የዚህም ዋነኛው ምክንያት ደግሞ በኢትዮጵያ የረጅም የስልጣኔና የነጻነት ታሪክ ውስጥ የሕዝቡን ብሔራዊ ንቃተ ኅሊና በመቅረጽ ጠቃሚ ሚና የነበራትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን በመምታት ሹማምንቱና ሕዝቡ የኢጣሊያንን የበላይ ገዥነት እንዲቀበሉ ለማስገደድ ነበር፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የተደረገውን የቱርክና የደርቡሾችን ወረራ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ወረራዎችም የከሸፉት በዚህች በተቀደሰች ቤተ ክርስቲያን ጥረትና በተከታዮቿ ምእመናን መሥዋዕትነት ነበር፡፡ በእርግጥም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይህችን ሀገርና ሕዝቦቿን በእውነተኛ ሃይማኖትና ባሕል ገንብታ ባትይዝ ኖር በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት ባሕልዋንና ነጻነትዋን ይዛ ባልተጓዘች ነበር፡፡
ለአድዋ ድል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የነበራት ድርሻና ተሣትፎም የዚሁ ታሪካዊ እውነታ ሌላ መገለጫ መሆኑን ልንስተው አይገባም፡፡ በአድዋ ጦርነት ሕዝቡን ከዳር እስከ ዳር በማስተባበርና ቀዳሚ ሆና በመገኘት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተጫወተችው ሚና ተወዳዳሪ እንዳልነበረው ኢጣሊያውያን ጸሐፊዎችና የታሪክ ተመራማሪዎች በራሳቸው አንደበት የመሰከሩት ሐቅ ነው፡፡ ኢጣሊያዊው ምሁር ኮንቲ ሩሲኒ የተባለው ታሪክ ጸሐፊ እንደዘገበውም፡- ‹‹ከልዩ ልዩ ምንጭ እንዳገኘሁት፣ ከሐበሾችም ጽሑፍ እንደተረዳሁት፣ ጦርነቱ ሲጀመር አፄ ምኒልክ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻ አቲከም፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ሌሎችም የጦር ሹማምንትና መሳፍንቱ ሁሉ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በአንድነት ሆነው ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በአድዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሲያስቀድሱ እንደነበር…፡፡›› ዘግቧል፡፡
ቤተ ክርስቲያንዋ ሕዝቡ ሃይማኖቱንና ክብሩን ሊነጥቁት ከመጡ ወራሪዎች ነቅቶ ሀገሩን እንዲከላከል በማስተማር ቆይታለች፡፡ የአድዋን ጦርነት በቅርብ ሆነው የተከታተሉ በርካታ ጸሐፊዎች እንዳሉት ብዙዎቹ የኢጣሊያ የጦር መሪዎች የኢትዮጵያ ሠራዊት በከባድ መድፎች ጩኸት ብቻ ተደናግጦ ይበተናል የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ ጦርነቱ ሲጀመር ግን የተገላቢጦሽ ነው የሆነው፡፡ አብዛኛው ጦርና ጎራዴ የታጠቀውና ‹‹ያልሰለጠነ ነው›› የተባለው የኢትዮጵያ ሠራዊት በእግዚአብሔር ኃይል ተማምኖ መድፍና መትረየስ የያዘውን የኢጣሊያን ጦር እያሳደደ መውጫ መግቢያ ያሳጣው ጀመር፡፡ በማለት የዓይን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የአድዋ ድል የተገኘው የጊዮርጊስ እለት የካቲት 23 1888 ዓ.ም ነበር፤ አፄ ምኒልክም ጦርነቱ እስከሚጀመርበት የመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ በአድዋ ማይጓጓ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሆነው አምላከ ጊዮርጊስ ከእሳቸውና ከሠራዊታቸው ጋር እንዲሆን በጸሎት እየተማጸኑ እንደነበር በወቅቱ የነበሩ ሰዎች መስክረዋል፡፡ የአፄ ምኒልክ ጸሐፊ የሆኑት ጸሐፌ ትእዛዝ አለቃ ገብረ ሥላሴ ስለ አድዋ ድል በጻፉትና እማኝነታቸውን በሰጡበት የመጽሐፉ ክፍል ድሉ ከእግዚአብሔር የተገኘ እንደሆነ ከመግለፃቸውም በላይ የክርስቲያኖች ደም በከንቱ ስለ መፍሰሱ የተሰማቸውን ሐዘኔታም በመጋቢት 23 1888 ዓ.ም ለፈረንሳዊው ሙሴ ሸፍኔ በላኩለት ደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡
‹‹… ከአላጌ ጦርነት በኋላ፣ ጣሊያኖችን ጦርነት ይቅር፣ የክርስቲያንም ደም በከንቱ አይፍሰስ፣ እርቅ ይሻላል ብላቸው እምቢ ብለው መጥተው በጥጋባቸው አድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ፡፡ እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም፡፡ ነገር ግን በግፍ የመጡ ሰዎች ናቸውና እግዚአብሔር ግፉን አነጣጠረን…፡፡››
ለሞስኮብ ንጉሥ ኒቆላዎስም መጋቢት 23 1988 ዓ.ም በጻፉት ደብዳቤያቸውም፡-
‹‹እንደ አውሮፓ ነገሥታት ሥራት ሁሉ ጠብ መፈለጋቸውን ሳያስታውቀኝ፣ እንደ ወምበዴ ሥራት ሌሊት ሲገሰግስ አድሮ ሲነጋ ግምባር ካደረው ዘበኛ ጋር ጦርነት ጀመረ፤ ጥንት ከአሕዛብና ከአረመኔ አገራችን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ከእኛ ባይለይ በእግዚአብሔር ኃይል ድል አደረግሁት…›› በማለት ድሉ የእግዚአብሔር መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ታሪክ የሚያስተምረን ሐቅ ቢኖር በዘመናቸው ሁሉ እግዚአብሔርን ጋሻና መከታ በማድረግ የኖሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ባለ ድልና ኃያላን እንደሆኑ ነው፡፡ በዛች ታናሽ ጠጠር ጎልያድን የጣለ ዳዊት ድሉን የሰጠው ኃይሉና ብርታቱ ሳይሆን የእግዚአብሔር ክንድ እንደሆነ የሚያስረግጥ ነው፡፡ በክርስትና ሕይወታችን ለምንዋጋው ብርቱ ጦርነት ኃይልና ብርታት የሚሆነን፡- ኃያልና ሕያው የሆነው ከስሞች ሁሉ በላይ ስም የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ የጌታችን ስም ነው፡፡ መጽሐፍ እንደሚል፡- በሰው ልማድ ምንም እንኳን የምንመላለስ ብንሆን፣ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋምና፣ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፣ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው…›› 1ቆሮ 10፣ 3-4፡፡
የክርስትናውን ጦርነት ለመዋጋት፣ እስከ መጨረሻውም በመጽናት፣ የጽዮንን የድል ዝማሬ ለመዘመር እንችል ዘንድ፡-
በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታን፣ የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ የለበስን እንሆን ዘንድ ያስፈልገናል፡፡ ወገባችንንም በእውነት ታጥቀን፣ የጽድቅንም ጥሩር ለብሰን፣ በሰላምም ወንጌል ተዘጋጅተን በመዘጋጀት በእግሮቻችን የቆምን፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልናጠፋበት የምንችልበትን የእምነትን ጋሻ፣ የመዳንን ራስ ቁር የመንፈስ ሰይፍ ሆነውንም የእግዚአብሔርን ቃል ልንታጠቅ ይገባናል፡፡ ኤፌ 5፣10-17፡፡
ዘመኑ ብርቱ ውጊያ ያለበት ቢመስልም ኃይለኞች ነን ማን ይችለናል የሚሉ በምድራዊ አቅማቸው በእውቀት፣ በሀብታቸው የሚተማመኑ እኛን የሚያስጨንቁበት ቢሆን እንኳ ድል ያለው በእግዚአብሔር እንጂ በኃይል መመጣጠን አለመሆኑን ጥንት ከዳዊትና ከጎልያድ፣ በቅርቡ ታሪክ ደግሞ ከአድዋ ጀግኖችና ከኢጣሊያ ሠራዊት ልንማር ይገባናል፡፡ ድል ያለው በሠራዊት ብዛት በመሣሪያም ልቀት አይደለምና የዛሬው ክርስቲያን ወገብህ አይላላ! የዛሬው አገልጋይ ከአሳዳጆችህ የተነሣ አትደንግጥ፤ የዳዊት አምላክ ያንተም አምላክ ነው፡፡ የጦር መሪህ ክርስቶስ ያለህን አስታውስ፡- ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ›› የተባለልህን ነን (ዮሐ. 16፡33)፡፡ የተሸነፈን ጦር ሕጻንና ሴት ሳይቀር ይማርከዋል እንዲሉ ለድል የማንዋጋ ምርኮ ሰብሳቢ እንደሆንን በማሰብ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ጨካኝ ጎረቤት፣ ክፉ አለቃ፣ የማይደክማቸው አሳዳጆች፣ ስም የሚያጠፉ ምቀኞች ቢበዙ እንኳ ድሉ የጌታ ነው፡፡ መሣሪያ የያዙ ሳይሆን ጌታን የያዙ ያሸንፋሉ፡፡
እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፣ ስሙም እግዚአብሔር ነው!