የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንዲህ ቢሆንስ …? /9/

“በአእምሮዬ ውልብ የሚሉ የኃጢአት አሳቦች አሉ ። አሳቦቹ ምኞት ቀጥሎ ፈቃድ እንዳይሆኑ እሰጋለሁ ። ይህ ስሜት ውስጤ ላይ ሲነሣ በክርስትና የምዘልቅ አይመስለኝም ። ወደ ቀድሞ ሕይወቴ ብመለስስ እያልሁ እፈራለሁ” እያልህ ይሆን ? የክርስትናን ጉዞ የጀመርከው በልጅነት ጸጋ ነው።እግዚአብሔር ከሰጣቸው ጸጋዎች የበላይ የሆነው የልጅነት ጸጋ ነው ። ያንተ ልጅነት እንደ ክርስቶስ ያለ ልጅነት አይደለም ፣ የእርሱ ልጅነት አብን በመልክ የሚመስልበት ፣ በባሕርይ የሚተካከልበት ነው ። ያንተ ልጅነት የጸጋ ሲሆን የተወለድኸውም ከሥላሴ ነው ። ይህ ልጅነትህ እግዚአብሔርን በመምሰል የተፈጠርህበት መዐርግ ነው ። ይህ ልጅነትህ በክርስቶስ እንደገና የተመለሰልህ ርስትህ ነው ። ሳይንስና እምነት ፍጹም የተለያዩ ናቸው ።ሳይንስ በውርደት ይጀምራል ፣ አንተ እንስሳ ነበርህ ይላል ፤ እምነት ግን አንተ በእግዚአብሔር መልክ ተፈጥረሃል በማለት በክብር ይጀምራል ። ሳይንስ የሚቀጥለውም በውርደት ነው ፣ እምነት ግን መንግሥቱን ትወርሳለህ ይላል ። ከእግዚአብሔር መወለድ ትልቅ ክብረት ነው ። ልጅ በታላቅ ፍቅር ይወደዳል ፣ አንተም በአጋፔ ፍቅር ተወደሃል ። ልጅ ይወርሳል ፣ አንተም ወራሽ እንድትሆን ተጠርተሃል ። ልጅ ቢያጠፋ ልጅነቱ አይፈርስም ፣ ኅብረቱ ግን በይቅርታ ይታደሳል ። አንተም ብታጠፋ ንስሐ የተባለ የሕይወት ሳሙና ተዘጋጅቶልሃል ። ልጅ የሚወደደው ፍጹም ስለሆነ አይደለም ፣ ወደ ፊትም ጥሩ ይሆናል ተብሎ አይደለም ። ልጅ ስለሆነ ነው ። አንተም የምትወደደው ልጅ ስለሆንህ ነው ።
አእምሮ ማለት እንደ አደባባይ ነው ። በአደባባይ ዛሬ የሚያልፉት እነማን እንደሆኑ በርግጠኝነት መናገር አይቻልም ። በአእምሮም የሚታሰበው እንዲሁ ነው ። በደጃችን የሚያልፉትን ሁሉ ጎራ በሉ አንልም ፣ በኅሊናችን የሚያልፈውን ሁሉም ማስተናገድ የለብንም ። በደጃፋችን ላይ ክፉ ሰዎች ሊያልፉ ይችላሉ ፣ በኅሊናችንም ክፉ አሳቦች ሊያልፉ ይችላሉ ። በደጃፋችን ላይ የሚያልፉ ክፉ መሆናቸውን ስናውቅ በራችንን እንዘጋለን ፣ በኅሊናችንም ክፉ አሳብ ሲመጣ በጸሎት ልባችንን መጠበቅ ይገባናል ። “ወፎች በጭንቅላታችን ላይ እንዳይበሩ መከልከል አንችልም ፣ አናታችን ላይ ግን ጎጆአቸውን እንሥራ ቢሉ አንፈቅድላቸውም ።”
ሰይጣን ክፉ አሳቦችን እያመጣ የሚሟገተን የመጀመሪያው አሳቡን ተቀብለን ወደ ምኞትና ፈቃድ እንድንወስደው ነው ። ሁለተኛው “እንዴት እኔ ይህን አስባለሁ ?” በማለት እንድንሸማቀቅ ነው ። በዚህ ክፉ አሳብ ሁነህ እንዴት ትጸልያለህ ፣ እንዴት ከክርስቲያኖች ጋር ትገናኛለህ ይለናል ። ነገር ግን ባንጸልይም ያለነው በእግዚአብሔር መዳፍ ላይ ነው ። ዓለምን በመሐል እጁ የያዘው ጌታ ነው ብለን ካመንን እኛም ያለነው በመዳፉ ላይ ነው ። ክርስትና ሁለት ነገሮችን ሁልጊዜ ይጠይቀናል ። የመጀመሪያው የምናኔ ሕይወትን ነው። ይህም ዓለምን መናቅና በነጻ ሰዎችን ማፍቀር ነው ። ሁለተኛው ተጋድሎ ነው ። ከክፉ አሳብ ፣ ከክፉ ሰዎችና ከክፉ ዘመን ጋር እንታገላለን ።በአእምሮአችን የሚመጡትን ክፉ አሳቦች የጦር ዕቃችን በሆነው በእግዚአብሔር ቃል ፣ በጸሎት ፣ በጌታችን ስምና ሥልጣን ልንታገል ይገባል። መጽሐፍ ተጋደሉ ይላል ። ከክፋት ጋር ካልተጋደልን ከሰዎች ጋር እንጋደላለን ፣ ከክፉ ምኞት ጋር ካልተጋደልን ከፍቅር ጋር እንታገላለን ።
በአእምሮአችን የሚያልፉት አሳቦች ሁሉ የእኛ ላይሆኑ ይችላሉ ። ስለዚህ ነቅተን በእግዚአብሔር ስም መገሠጽ ይገባናል ። አእምሮአችን ላይ ያለውን አሳብ በእርሻ ላይ እንዳለ እህል መቊጠር ይቻላል ። በእርሻ ላይ ያለ እህል አረም ፣ ገለባ ፣ እንክርዳድ አለው ። አረሙ እህሉ ሳይታጨድ ፣ ገለባው እህሉ ሲወቃ ፣ እንክርዳዱ እህሉ ሲለቀም የሚወገድ ነው ። ሁሉም ጠላት በአንድ ጊዜ አልተወገደም ። እንደ አረሙ የሚመጡ ልዩ ልዩ አሳቦች በእግዚአብሔር ስም ማራቅ ይገባል ። እንደ ገለባው አንዳንድ አሳቦች በምክር የሚወገዱ ናቸው ። እንደ እንክርዳዱ በልዩ እውቀትና በጸሎት የሚወገዱ አሳቦች አሉ ። ውልብ የሚሉብን አሳቦች ከዚህ በፊት አስበናቸው የማናውቃቸው ሲሆኑ እነርሱን ላለማሰብ የምናደርገው ጥረት የበለጠ እንድናስባቸው ሊያደርገን ይችላል ። በእግዚአብሔር ስም በመገሠጽ ሌላ አሳብ ማሰብ ይገባናል ። አንድን ክፉ አሳብ ላለማሰብ መጣር የበለጠ ወደ ማሰብ ያደርሳል ። አሳብ ግን በአሳብ ይሻራል ። እንደ ገለባው ያሉ አሳቦች ደግሞ በልዩ ረገጣ የሚረግፉ ፣ በመንሽ የሚበተኑ ናቸው ። አንዳንድ አሳቦች በመከራና በፈተና የሚወገዱ ናቸው ። መከራ የኃጢአትን እሾህ ያቃጥላል ።መከራና ፈተና የሚያስወግዱት ክፉ አሳብ አለ ። እንክርዳዱ ግን ሁለቱንም ደረጃዎች ያለፈ ሲሆን በባለሙያ በንቁ ዓይን የሚወገድ ነው ። ይህም በጾምና በጸሎት በረድኤተ መንፈስ ቅዱስ የሚወገድ ነው ።
ከአሳብ ሲያልፍ ስሜታችንን የሚነካ ነገር ሊገጥም ይችላል ። ይህ ስሜት እንዴት ተሰማኝ ? ይህ ከተሰማኝ እኔ የተፈጠርኩት ለዚህ ነው በሚል አሳብ ስሜትን እንደ ቃለ እግዚአብሔር ማመን ተገቢ አይደለም ። የተሰማን ሁሉ ትክክል አይደለም ። ያልተሰማን ሁሉም ክፉ አይደለም ። ስሜትን ማመን ከባድ ነው ። ስሜት አሁን ተጋግሎ ኋላ የሚበርድ ለጸጸት አሳልፎ የሚሰጥ ነው ። ስሜት መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ የለውም ።
ሕይወት የትግል እንጂ የመዝናኛ ሜዳ አይደለችም ። ትግል ሲመጣ ከፈራህ የበለጠ እጅ እየሰጠህ ትመጣለህ ። በድፍረት በገደል አፋፍ ላይ የሚሮጡ አሉ ፣ በፍርሃት በሜዳ ላይ የሚወድቁ አሉ ። በገመድ ላይ የሚጓዙ ደፋሮች ባሉበት ዓለም ከወንበር ላይ የሚወድቁ ፈሪዎች አሉ ። ፍርሃት ለጠላት ምልክት የሚሰጥ ነው ። ፍርሃት የሰይጣን መግቢያ በር ነው ።
ክርስትናን የሚያስጀምር እግዚአብሔር እንደሆነ የሚያስፈጽምም እርሱ ነው። ከጠላት ብቻ ሳይሆን ከራስህም ያድንሃል ። የእግዚአብሔር ፍቅር አቅም ሁኖ የፈራኸውን ትረግጣለህ ፣ ያሸነፈህን ድል ትነሣለህና በርታ ።
ወደ ክርስቶስ መገስገስ 14
ተጻፈ አዲስ አበባ
ጥቅምት 20 ቀን 2011 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ