የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወደ ኋላህ አትይ / ክፍል 3

                                                      ጳጉሜን 5 2003 ዓ.ም. (September 10, 2011)

                                                 ክፍል 3 
‹‹ወደ ግብፅ እንመለስ››
                                          (ዘኁ.14÷4)፡፡
የደቡብ አፍሪካ ሕዝቦች በአፓርታይድ የጭቆና ቀንበር ለአራት መቶ ዓመታት እንደማቀቁና በዘመናችን ነጻነትን እንደ ተጎናፀፉ እናውቃለን፡፡ በዚህ ቁጥር ልክ ከዛሬ ሦስት ሺህ ዓመት በፊት የእስራኤል ልጆች በግብፅ አገር ለ430 ዓመታት ባሮች ነበሩ፡፡ ነጻ የወጡት ግን በነጻነት ትግል አይደለም፡፡ የነጻነታቸው ንጉሥ ራሱ እግዚአብሔር ነበረ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአብርሃም የሰጠውን ቃል አስቦ ዳግመኛም የእስራኤልን የልቅሶ ጩኸት ሰምቶ በሙሴ መሪነት ከግብፅ ምድር አወጣቸው፡፡
የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ሲወጡ ንጉሣቸው እግዚአብሔር ነበር፡፡ ነገር ግን እስራኤላውያን በፈርዖን ላይ ያላጉረመረሙትን በእግዚአብሔር ላይ ማጉረምረማቸው እጅግ ይገርማል፡፡ የፈርዖንና የእግዚአብሔርን አገዛዝ ብናነጻጽረው፡-
    ፈርዖን                              እግዚአብሔር
·        የቅን ገዢአቸው                               – የነጻነታቸው ባለቤት
·        ገራፊያቸው                                    – አሳራፊያቸው
·        በሥራ ጫና የሚያስጨንቃቸው              – የዕፎይታ ዘመን የሰጣቸው
·        እየሠሩ ያስራባቸው                           – ሳይሠሩ የመገባቸው
·        በፀሐይ ቃጠሎ የገረፋቸው                   – በደመና ጥላ የጋረዳቸው
·        የወላድ መሐን ያደረጋቸው                    በኩራቸውን ከሞት የከለለ
·        ያስለቀሳቸው                                   ጩኸታቸውን የሰማ
የፈርዖንና የእግዚአብሔር አገዛዝ ለማነጻጸር እንኳ የሚከብድ ቢሆንም የእስራኤል ልጆች ግን በእግዚአብሔር ላይ አንጎራጎሩ፡፡ ግብፅ ትሻለናለች፣ ፈርዖን ቢገዛን ይሻላል አሉ፡፡ የማይመረጠውን መረጡ፣ ትላንት ያለቀሱበትን ነገር ናፈቁ፡፡ በብርቱ መከራ ውስጥ አልፈው ስለ ነበር እግዚአብሔር ትልቅ እንክብካቤ አደረገላቸው፡፡ በመከራቸው የጠሩትን እግዚአብሔር በምቾታቸው ሊያመሰግኑት አልፈለጉም፡፡ በረሀውን ገነት አድርጎ በቀኙ የመራቸውን እግዚአብሔርን ታስፈልገናለህ ከማለት እናስፈልገዋለን ወደሚል ትዕቢት፣ ወደ ግብፅ እንመለሳለን ወደሚል ፉከራና ሞልቃቃነት ተመለሱ፡፡
በወዳጅ ፊት የማንናገረው፣ በንጉሥ ፊትም ደፍረን የማንለው ነገር አለ፡፡ በእግዚአብሔር ፊትም ልንለው የማይገባ ነገር አለ፡፡ የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ሊባል የማይገባውን አሉ፡፡ ‹‹እርስ በርሳቸውም፡- ኑ አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ ተባባሉ›› (ዘኁ .14÷4)፡፡
የእስራኤል ልጆች በበረሃ አብዝተው ያረመርሙ ነበር፡፡ ለምን እንዳጉረመረሙ ብንመረምር፡-
1.      ቀጥሎ ልንሞት ነው ብለው አጉረመረሙ (ዘፀ. 14÷11-12)፡፡
2.     የምንጠጣው መራራ ሆነብን ብለው አጉረመረሙ (ዘፀ. 15÷24)፡፡
3.     በራብ ልንሞት ነው ብለው አጉረመረሙ (ዘፀ. 16÷2)፡፡
4.     በጥማት ልናልቅ ነው ብለው አጉረመረሙ (ዘፀ. 17÷3)፡፡
5.     በክፉ ልብ አጉረመረሙ (ዘኁ. 11÷1)፡፡
6.    ብንጠፋስ ብለው አጉረመረሙ (ዘኁ. 14÷2)፡፡
7.     ክፉዎች ለምን ተቀጡ ብለው አጉረመረሙ (ዘኁ. 16÷41)፡፡
በእስራኤል የማረምረም ታሪክ ላይ ተመሥርተን ማጉረምረምን ስንተነትን፡-
1.      ያልመጣ ነገርን እንደ መጣ አድርጎ የመረበሽ ስጋት፤
2.     ለመጸለይ እንኳ ጊዜ አጥቶ ለመላምት ግን መቸኮል፤
3.     ቀጥሎ የሚሆነውን ባለመጠበቅ የችኩልነት መልስ፤
4.     ከራስ አልፎ ለሌሎች ማሰብ የሚመስል የተቆርቋሪነት ስሜት፤
5.     መርካት አቃተኝ የሚል ብሶት፤
6.    ምክንያት በሌለው ነገር ጨለምተኛ አስተሳሰብና ንግግር፤
7.     እግዚአብሔር የማፍቀር እንጂ የመፍረድ ሥልጣኑን ለምን ይጠቀማል? የሚል አላዋቂነት ነው፡፡
ርዕስ አድርገን በተጠቀምበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እንዳነሣነው ወደ ኋላ ከሚመልሱ ነገሮች አንዱ ማጉረምረም እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በዚህ ክፍል ላይ የእስራኤል ልጆች፡- ‹‹ኑ፣ አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ ተባባሉ›› (ዘኁ. 14÷4)፡፡ እንዲህ ያሉበት ምክንያት ምንድነው? ስንል በእግዚአብሔር ትእዛዝ ከፊታቸው የሚወርሷትን ምድር እንዲሰልሉ ዐሥራ ሁለት ሰላዮች ተላኩ፡፡ ስለላው ያስፈለገው የምድሪቱን መልካምነት ዐይተው ለጉዞው ጉልበት እንዲያገኙ ነው፡፡ ነገር ግን ከዐሥራ ሁለቱ ሰላዮች ሁለቱ ኢያሱና ካሌብ የእምነት ቃል ሲናገሩ ዐሥሩ ግን የፍርሃት ድምጽ ይዘው መጡ፡- ‹‹…በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኃያላን ናቸው÷ ከተሞቻቸውም የተመሸጉ እጅግም የጸኑ ናቸው፤ ደግሞም የዔናቅን ልጆች አየን›› አሉ (ዘኁ. 13÷27-29)፡፡
እነዚህ ሰላዮች የተላኩበት ዓላማ የምድሪቱን መልካምነት እንዲያዩና የሕዝቡን ልብ በተስፋ ኃይል እንዲሞሉ ነበር፡፡ የእምነት ሰባኪዎች ሊሆኑ የተጠሩት ግን የፍርሃት ሰባኪ ሆኑ፡፡ የተናገሩት የጠላቶቻቸውን ምሽግና ብርታት ነው፡፡ የብርቱዎች ብርቱ የሆነው፣ ተሸንፎ የማይገባው እግዚአብሔር ግን አልታያቸውም፡፡ የተላኩት በተስፋ ደስ እንዲላቸው ነው፡፡ የተናገሩት ግን መጪውን አደጋ ነው፡፡ ከተላኩት የሚበዙቱ ወይም ዐሥሩ ጠላቶቻቸውን አዩ፣ ሁለቱ ኢያሱና ካሌብ ግን ከዚህ በፊት የረዳቸውን፣ ዛሬም ክንዱን ለረድኤት የማያጥፍባቸውን ጌታ አዩ፡፡ በተለይ ካሌብ፡- ‹‹ማሸነፍ እንችላለንና እንውጣ እንውረሰው›› አለ (ዘኁ. 13÷30)፡፡ በዚህ ጊዜ የሕዝቡ ልብ በፍርሃት ቀለጠ፡፡ ወደ ፊት ለመግፋት ይረዳል የተባለው ስለላ ወደ ኋላ የሚመልስ ፍርሃትን አመጣ፡፡ ሕዝቡ የስጋትን ድምፅ በተቀበለበት ጆሮ የእምነትን ድምፅ መቀበል አቃተው፡ በዚህ ጊዜ ወደ ግብፅ እንመለስ አለ፡፡ ከግብፅ ምድር በታላቅ ጩኸት እንደ ወጡ ረሱ፡፡ የበለጠ ዐይተው በትንሽ ነገር ደነገጡ፡፡ ከፊታቸው እየቀደመ ያለውን እግዚአብሔርን ናቁና፡- ‹‹ኑ& አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ ተባባሉ›› (ዘኁ 14÷4)፡፡
ሲያስፈራቸው የነበረ የግብፅ ባርነት ዛሬ ማስፈራሪያ አደረጉት፡፡ ወደ ግብፅ ቢመለሱስ ብለን እንጠይቅ፡-
·        ግብፃውያን ከቀድሞ ይልቅ አስጨንቀው ይገዟቸዋል፤
·        ከግብፅ ሲወጡ የተከፈለው ባሕር አሁን አይከፈልላቸውም፤ እግዚአብሔር ተአምራትን የሚያደርገው ወደ ፊት ለሚሄዱት ነውና፡፡
·        እግዚአብሔርን ማምለክ አይችሉም፣ በግብፅ ሆኖ እግዚአብሔርን ማምለክ አይቻልምና፤
·        በአንድነት በመሪ የወጡት የሚመለሱት ግን በአለቃ ነውና ይበተናሉ፡፡ መሪ አንድ ሲያደርግ፣ አለቃ ይበትናልና፡፡
የእስራኤል ልጆች ወደ ኋላ ለመመለስ በማሰባቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ቁጣ መጣባቸው፡፡ በዐርባ ቀን ይፈጸም የነበረው ጉዞ ዐርባ ዓመት እንዲጓዙት ሆነ (ዘኁ. 14÷34)፡፡ አለማመን ብርቱ መዘግየትን፣ በምድረ በዳ ተንጠባጥቦ መቅረትን ያመጣል፡፡
እኛስ?
ከእግዚአብሔር መንግሥት ወደ ኋላ እያልን ያለነው በምን ምክንያት ነው? የትኛውም ምክንያት ወደ ኋላ መመለስን ትክክል እንደማያደርገው አስተውለናል? ምናልባት ትላንት የመጣንበትን የኃጢአት፣ የባዕድ አምልኮ ሰፈርና ስቃዩን ረስተን ዛሬ በትንሽ ትልቁ አቃቂር እያወጣን ይሆን? እግዚአብሔር ግን የነጻነታችን ንጉሥ ነው፡፡ ከነማንነታችን የተቀበለን፣ ማንም የማይችለውን፣ ዘመድ እንኳ የታከተውን ጠባያችንን የቻለልን እርሱ ነው፡፡
ያኔ በኃጢአት በርኩሰት በነበርኩበት ጊዜ ይሻል ነበር፡፡ አሁን ግን ፈተናዬ በዛ እግዚአብሔርም ሲቀርቡት ይርቃል ወይ? እያልን ይሆናል፡፡ መርሳት ባሕርያችን ስለሆነ እንጂ ከዛሬው የድሮው የሚሻል አይደለም፡፡ ከእግዚአብሔር ፈርዖን፣ ከቤተ ክርስቲያንም ዓለም አይመረጥም፡፡ እንደ ተልባ ስፍር በሚንሸራተተው ልባችን በዐርባ ቀን የምንወርሰው ዐርባ ዓመት እንዳይራዘምብን ከዚህ ከዳተኛ ማንነት እንለይ! አፋችን ምስጋናን ያፍስስ፡፡ ማመን የአንድ ቀን ጉዳይ ሲሆን ባመኑት መጽናት ግን የሁልጊዜ ጥያቄ መሆኑን መዘንጋት የለብንም! እግዚአብሔር አምላካችን እርሱን በማመን፣ ልዩ ሦስትነቱን በመቀበል አጽንቶ ይጠብቀን! 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ