የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የምናይበት መስተዋት

“ሁሉ ለንጹሖች ንጹሕ ነው ፤ ለርኵሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም የለም፥ ነገር ግን አእምሮአቸውም ሕሊናቸውም ረክሶአል።” ቲቶ. 1፡15
ሐዋርያው ጳውሎስ ከአይሁድ ወገን የሆነው ጢሞቴዎስን የኤፌሶን ጳጳስ ሲያደርገው ፣ ከአሕዛብ ወገን የነበረውን ቲቶን ደግሞ የቀርጤስ ጳጳስ አድርጎ ሾሞታል ። ቲቶ ጳጳስ ቢሆንም ከመንፈስ አባቱ ከጳውሎስ የሚደርሰው ምክርና ማበረታቻ አልተለየውም ነበር ። ምክር ከሌለ ጉዞው ሁሉ ዋጋ የሚያስከፍል ይሆናል ። ምክር ካለ ለመፈጸም አቅም ቢጠፋ እንኳ አስቦ የሚመክረኝ አባት አለኝ የሚል ስሜት ውስጥን ያስደስታል ። የትኛውም መዐርግና ክብር ላይ ብንቀመጥ ምክር ያስፈልገናል ። መካሪ ከሌለ ዕድሜ ያጥራል ። ምክር ሰባት ጊዜ ተፈትኖ እንደ ተጣራ ብር ንጹሕ ሲሆን ወደ ክብር ማማ ያሸጋግራል ። በሰይጣን ዓለምም ክፉ ምክር ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል ። ኃጢአት ወደ ዓለም የገባው በክፉ ምክርና በክፉ መካሪ ነው ። አቤሴሎም በሚወደው አባቱ ላይ የዘመተው በአኪጦፌል ክፉ ምክር ነው ። ምክር በብርሃንና በጨለማው ዓለም ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ነው ። አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልም ምክር ነው ።
ሐዋርያው ጳውሎስ ለቲቶ የሹመት መስፈርቶችን እየጻፈለት ነው ። ሹመት መስፈርት ያስፈልገዋል ። እውቀት ከመንፈሳዊነት ጋር ያሻዋል ። አሊያ ከሁለቱ አንዱ እንዲኖረው ይገደዳል ። እውቀት ባይኖረው መንፈሳዊ መሆን አለበት ፤ ምክንያቱም የእውቀት ግቡ መንፈሳዊነት ነውና በመንፈሳዊነቱ ይሾማል ። አሊያ አዋቂ መሆን አለበት ፣ ለራሱ ባይኖረውም ለሌላው መንገድ ያሳያልና ። እስከ ዛሬ ስረቁ ያለ ቄስ አልታየም ። ከሁለቱ ንጹሕ የሆነ ሰው ግን መሾም የለበትም ። ሹመት መስፈርቱ ጎሣ ፣ ትውውቅ ፣ ውለታ ፣ ኮታ ፣ ወረፋ ፣ ተረኛ መሆን የለበትም ። ሕይወቱ ደካማ ፣ ብዙ የክስ ፋይል ያለውን ሰው መሾም ለመያዝ ይረዳል ብለው ብዙዎች ያስባሉ ። ባለጌ ግን በምንም አይያዝምና ሙከራው ከንቱ እንደሚሆን በታሪክ ታይቷል ። ከጨዋ መጣላት ክብሩን ስለሚፈልግ አያዋርድም ፣ ባለጌ ግን ክብር የማይፈልግና ክብር የማይሰጥ በመሆኑ ያዋርዳል ። ሥርዓት ለሌለው ሰው የሚሰጥ ሹመትም ፍጻሜው ሹዋሚውን ጥቁር ድንጋይ የሚያሸክም ነው ። ላልተማረ ሰው ሥልጣን መስጠት ለእብድ ሰይፍ መስጠት ነው እንዲሉ ።
መስፈርት የሌለው አገር ፣ መስፈርት የሌለው ቤተ ክርስቲያን ፣ መስፈርት የሌለው ማኅበረሰብ አስፈሪ ነው ። መስፈርት ሲጠፋ ሰዎች ቦታ ተለዋውጠው ይቀመጣሉ ። መስፈርት ሲጠፋ ባለቤት ደባል ፣ ደባልም ባለቤት ይሆናል ። መስፈርት ሲጠፋ አማኝ ይወገዛል ፣ አላዋቂ ይነግሣል ። መስፈርት ሲጠፋ ያልተማሩ የተማሩትን ያርማሉ ። መስፈርት የጠፋበት ዘመን አስፈሪ ነው ። ጌታ ሆይ መስፈርት ከሌለው ዘመንና ትውልድ አድነን!
ሐዋርያው ጳውሎስ በቲቶ መልእክቱ የወቀሳቸው ሰዎች ሁሉን የሚያረክሱ ፣ ምንም እንዳይጥማቸው ሁነው የተሰለፉ ናቸው ። ሁሉን መተቸት ፣ ሁሉን ማውገዝ ፣ ሁሉን ማጣጣል መንፈሳዊ በሽታ ነው ። “ሁሉ ለንጹሖች ንጹሕ ነው ፤ ለርኵሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም የለም፥ ነገር ግን አእምሮአቸውም ሕሊናቸውም ረክሶአል።”
በቆሻሻ መስተዋት የሚያይ ሁሉም ነገር ቆሻሻ ሁኖ ይታየዋል ። ንጹሕ ባልሆነ አእምሮም የሚያስብ ሰው ለእርሱ ሁሉም ነገር የረከሰ ነው ። ይህ ሰው የሚያስፈልገው አካባቢውን ማስተካከል ሳይሆን የሚያይበትን መስተዋት ማጽዳት ነው ። ንጹሕ ላልሆኑ ሰዎች ፍቅር ማስመሰል ፣ ቸርነት ውደዱኝ ማለት ነው ። ንጹሕ ልብ ያላቸው ሁሉን ንጹሕ አድርገው ያያሉ ። አንድ ወዳጄ “ዛሬ አምሮብሃል” ስለው “በቀና ዓይንህ ስላየኸኝ ነው” ይላል ። የቀና ዓይን ካጣን ያማሩት ያስጠሉ ይመስለናል ። “የተማረ ሁሉን ይቀደስ ፣ ያልተማረ ሁሉን ያረክስ” ይባላል ።
ጌታ ሆይ ንጹሕ አድርገኝና ሁሉም ንጹሕ ሁኖ ይታየኝ ። ሰይጣን ሁሉን አርክሶብን ሁሉም ነገር ያጠራጥረናል ። እባክህን የማየውን ሳይሆን የማይበትን ልብ ንጹሕ አድርግልኝ ። በደጉ ስምህ አሜን ።
የሰማይ ድምፅ 2
ሐምሌ 26 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ