የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በመጨረሻው ቀን

“ከሰጠኝም ሁሉ አንድን ስንኳ እንዳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው ።” ዮሐ. 6 ፡ 39 ።
ጌታችን በራሳቸው ፈቃድ እየጠፉ መሆናቸውን እየነገራቸው ነው ። ራሳቸውን በሲኦል ቢያገኙት መላ በማጣታቸው አይደለም ። ፈቃዳቸው እንዲህ ስለሆነ ነው ። ሰው ለመዳንም ለመጥፋትም ነጻ ፈቃድ አለው ። ጌታ ግን አንድም ስንኳ እንዲጠፋ የእግዚአብሔር ፈቃድ አለመሆኑን ተናግሯል ። አንድም ስንኳ ይጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ካልሆነ የሚጠፉትና የሚድኑት አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው አስተሳሰብ ትክክል አይደለም ። ይህ አስተሳሰብ ስብከተ ወንጌልን የሚያዳክም ፣ ትዕቢትን የሚያጎለብትና ኃጢአትን የሚያስፋፋ እንደሆነ በዘመናት ልምድ ታይቷል ። ክርስቶስ ወደ ዓለም የተላከው አብ ዓለሙን እንዲሁ ስላፈቀረ ነው ። ዮሐ. 3 ፡ 16 ። ስለዚህ ለክርስቶስ የተሰጠው የአብ ስጦታ መላው የአዳም ልጅ ነው ። እውነተኛ ስጦታ ሁነው የሚቀጥሉት ግን ያመኑት ናቸው ።
ለመዳን የአዳኙ ሥልጣንና ፈቃድ አስፈላጊ ነው ። ሥልጣን ቢኖረው ፈቃድ ከሌለው መዳን ሊኖር አይችልም ። ፈቃድ ቢኖረውና ኃይል ግን ከሌለው አሁንም ማዳን አይችልም ። ጌታችን ሰውን በማዳን ሂደት ውስጥ ሥልጣንና ፈቃድን መጥቀሱ ለዚህ ነው ። አንድ ሥልጣን አንድ ፈቃድም በመዳን ላይ ተገልጾአል ።
ጌታችን አንድ ስንኳ አይጠፋም እያለ ነው ያለው ። ምክንያቱም ምእመናን የአብ ስጦታ ናቸውና ። ስጦታ የሰጪው የፍቅር መልእክተኛ ሲሆን የተቀባዩ ደግሞ አደራ ነው ። ስጦታ የሚለካው በትልቅነቱ ሳይሆን በሰጪው ፍቅር ነው ። ምንም እንኳ ደካማ ብንሆንም ጌታ ስጦታዬ ናችሁ እያለን ነው ያለው ። የእኛ ድካም ደግሞ ቅጥ የሌለው ለመናገርም የሚያሳፍር ነው ። ለንጽሕና የሚደክም ለዝሙት የሚበረታ ፣ ለመስጠት የሚዝል ለመስረቅ የሚጸና ማንነት ነው ። ይህን ማንነት የወደደው እግዚአብሔር ፣ በፍቅሩም የለወጠው አምላክ ድንቅ ነው ።
ጌታችን የጊዜ መለኪያ አስቀምጧል ። ሰውዬው ካመነበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዕለተ ምጽአት ፣ ከዕለተ ምጽአትም እስከ ዘላለም ዘመን ድረስ ተጠቅሷል ። ዕለተ ምጽአት ምእመናን የክብር ትንሣኤ የሚያገኙበት ሲሆን ከዕለተ ምጽአት በኋላም መንግሥተ ሰማያትን ወርሰው የሚኖሩበት ነው ። በጌታችን ሥጋዌ የተገኙ ነገሮች የመጀመሪያው ድኅነት ሲሆን በድኅነት ውስጥም ጥምቀት ፣ ቊርባንና ትንሣኤ ሙታን ታላላቅ ስጦታዎች ናቸው ።
መላእክት ሁለት ነገሮችን ማየት ይናፍቃሉ ። የመጀመሪያው እግዚአብሔርን ሲሆን ሁለተኛው መንግሥተ ሰማያትን ነው ። ሁለቱንም ሊያዩ የሚችሉት ለሰው ልጅ በሚደረገው ቸርነት ነው ። አምላክ ሰው በሆነ ጊዜ አዩት ። 1ጴጥ. 1 ፡ 12 ። ስለዚህ ዘመሩ ። ሉቃ. 2 ፡13 ። የሰው ልጆችም ተጠቃለው ሲገቡና ትንሣኤ ሙታን ሲሆን ያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት ትከፈታለችና መላእክት ያችን ቀን ይናፍቃሉ ። ገሀነመ እሳት ለሰይጣንና ለሰራዊቱ እንደ ተዘጋጀ መንግሥተ ሰማያትም ለመላእክትና ለምእመናን ተዘጋጅታለች ። ማቴ. 25 ፡ 41 ። /ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ምዕ. 37፡21 ዳግመኛም አንድምታውን ተመልከት/ ።
“ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው ፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ ።” ዮሐ. 6 ፡ 40 ።
እምነት የማይታየውን ነገር የምናይበት መነጽር ነው ። እምነት ማየት ነው ። ጌታችን እኔን ያየ ይላል ። በሥጋ ተገልጦ አማኝም ሰቃይም አይቶታል ። በዓይን ሳይሆን በልብ ፣ በእውቀት ሳይሆን በእምነት ካላዩት ጥቅም አይገኝም ። ያዩት ወገኖች ሁለት ዓይነት ምድብ ውስጥ ገብተዋል ። በሥጋዊ ዓይን ብቻ ያዩት የማያምኑ ቀጥሎም እርሱንና ተከታዮቹን የሚያሳድዱ ሁነዋል ። በእምነት ያዩት ደግሞ እርሱን አምነዋል ተከታዮቹንም አክብረዋል ። የማይታየው አብን በሥጋ በተገለጠው ወልድ አይተነዋል ። የአብ አካሉ ከወልድ ልዩ እንደሆነ ፣ የአብ ባሕርዩ ግን ከወልድ ጋር አንድ እንደሆነ ተገልጧል ። መታመን የአንዱ እግዚአብሔር ገንዘብ ነው ። ወልድን ማመን አብን ማመን ነው ። ወልድን በትክክል የሚያምን አብንም ያምናል ። ወልድን ልጅ ብሎ የሚያምን አብን አባት ብሎ ያምናል ። አባት በሌለበት ልጅ መባል ፣ ልጅም በሌለበት አባት መባል የለምና ።
ጌታችን አይቶ የሚያምን አለ ። ተገንዝቦ ፣ ተስማቶትና ወስኖ የሚያምን የዘላለም ሕይወት ያገኛል ። በዓለም ላይ ከተነሡ የግብረ ገብ መምህራን ክርስቶስ አንዱ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ ። ጌታችን ግን ትምህርት ሰጪ ብቻ ሳይሆን ሕይወት ሰጪም ነው ። የሞራል አብዮተኛ አድርገው ያሰቡትም ሰዎች አሉ ፣ እርሱ ግን ከሞት ወደ ሕይወት ያሻገረን ነው ። በለበሰው ሥጋ ከእኛ እንደ አንዱ ቢሆንም የፈጠረን አምላክም ነው ።
እኔን አይቶ የሚያምን የዘላለም ሕይወት ያገኛል ካለ በኋላ ይህ የአባቴ ፈቃድ ነው ይላል ። በመቀጠል እኔም አስነሣዋለሁ ይላል ። ወልድ መታመንን ሲወስድ ለዚያም ደግሞ የዘላለም ሕይወትን ሲሰጥ እናያለን ። በመጨረሻውም ቀን የማሥነሣት ሥልጣን አለኝ ይላል ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ካሉት አምላክ መሆኑ ግልጽ ነው ። ኦሪት በፍጡር የሚያምንን ረግማለች ። ክርስቶስ ሰው ብቻ ቢሆን ኑሮ እርሱን በማመናችን እንረገም ነበር ። እርሱ ግን አምላክ በመሆኑ በሰማያዊና በመንፈሳዊ በረከት ተባርከናል ። እነዚህ በክርስቶስ ያሉ መታመን ፣ ሕይወት መስጠትና ማሥነሣት በአብ ዘንድም አሉ። የአብ ፈቃድና የወልድ ፈቃድም አንዲት ናት ። ክርስቶስ በምድር ላይ የሚያከናውናቸው ተግባራት የአብ እውቅናና ፈቃድ ያላቸው ናቸው ። የዘላለሙን አምላክ ለሚያምን የዘላለም ሕይወት ይሰጠዋል ። ስጦታው በትልቁ ጌታ ስለ ተሰፈረ እንጂ ስለሚገባን አይደለም ። አምላክ የሆነውን አምላክ ነው ብሎ በማመን ፣ አዳኝ የሆነውን አዳኝ ነው ብሎ በመቀበል ይህን ያህል ጸጋ ማግኘት ከአእምሮ በላይ ነው ።
ጌታችን ለሚያምኑት የዘላለም ሕይወትን እንደሚሰጥ በመደጋገም ተናግሯል ። ምድራዊ እንጀራ ጊዜያዊ ሕይወትን እንደሚሰጥ ሰማያዊው እንጀራ ክርስቶስ ደግሞ የዘላለም ሕይወትን ይሰጣል ። አይቶ ማመን አነጣጥሮ መዝኖ ማመን ነው ። ለሰው ብሎ የሚያምን ሰው አለ ። ካህኑና ሰባኪው ስላየለት ብቻ የሚያምን አለ ። ክርስቶስ ያደረገልን ነገር በትክክል ሊገባንና ፍቅሩም በውስጠኛው ማንነታችን ዘልቆ ሊወጋን ያስፈልጋል ።
መታመን የሚገባውም መታመንን የሚሸከም ጽኑ ዓለት ክርስቶስ ነው ።ሰው በዚህ ዓለም ላይ እየተቀጣ የሚኖረው በሚያምናቸው ሰዎች ነው ። ያመናቸው ይሰበራሉ ። ክርስቶስ ግን የማይሰበር ጽኑ የሃይማኖት በትር ነው። የማይጠፋም የሃይማኖት መቅረዝ ነው ። መብራት ይጠፋል ፣ ፀሐይም ትጠልቃለች ። ክርስቶስ ግን በሚያምኑት ልቡና እንዳበራ ይኖራል ። በተላከው በክርስቶስ ማመን በላከው በአብ ማመን ነው ። ላኪ በሌለበት ተላኪ የለምና ። ላኪና ተላኪ የማይለያዩ ናቸው ። በፍቅር እኩያነት እንጂ በክብር መበላለጥ ያልሆነ የአብ ላኪነት ፣ የወልድ ተላኪነት ድንቅ ነው ። ባልና ሚስት በጋራ የሚያዙአት አገልጋይ አለቻቸው ። ባልና ሚስት እኩል ቢሆኑም አንዱ አንዱን ያዝዛል ። ይህ ለጋራ ቤታቸው ነው ። አብም ወልድን መላኩ መላእክት በሚላኩበት መጠን አይደለም ፣ በእኩያነት ለአንዲት መንግሥት የሆነ ላኪነትና ተላኪነት ነው ።
በወልድ ማመን ሕይወት ሰጪ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስም ማመን ነው። አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በየራሳቸው የቆሙበት ነገር እንዳለ ሁሉ የሚገናዘቡበትና የሚዋሐዱበት ነገርም አለ ። በየራሳቸው የሚገኙበት አካል ፣ ግብር ፣ ስም ናቸው ። አንድ የሚሆኑት ደግሞ በመታመን ፣ በማዳን ፣ በማሥነሣት ፣ በፈቃድ ነው ።
በመጨረሻው ቀን አሥነሣዋለሁ ይላል ። ላመኑት የሚሰጠው የመጨረሻው ዋጋ ነው ። ትንሣኤ በአዳም ምክንያት የመጣው ሞተ ሥጋ መነሣቱን የሚገልጥ ነው ። ዛሬ በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ከሞተ ነፍስ ድነዋል ። ሞተ ሥጋ ሁሉም ሰው ዕድር ገብቶ የሚጠብቀው ነው ። ትንሣኤ ሙታን መዳንን ፍጹም ሲያደርግ የአዳም ርግማን ለመጨረሻ ጊዜ የሚያነሣ ነው ። በመጨረሻው ቀን ሁሉም ይነሣልና እንዴት የአማኞች በረከት ሆነ ብንል ያላመኑ ለሐሳር ሲነሡ ፣ ያመኑ ለክብር ይነሣሉ ። ምድራዊው እንጀራ የደከመውን ሥጋ ያበረታል እንጂ የሞተውን ሥጋ አያሥነሣም ። ሰማያዊው እንጀራ ግን የሞተውን ሥጋ ያሥነሣል ። የጌታችን ሥጋና ደም መቀበል ከክርስቶስ ጋር መዋሐድ ነው ። ክርስቶስ የተዋሐደው ሥጋ ፈርሶ በስብሶ አይቀርም ። ይነሣል ። ከጥንት ጀምሮ የምእመናን በድን በቤተ ክርስቲያን የሚያርፈው በጥምቀት ልጅነትን ፣ በሜሮን መንፈስ ቅዱስን ፣ በቊርባን ሕይወትን ያገኘ ሥጋ የእግዚአብሔር ንብረት ስለሆነና የትም ስለማይጣል ነው ። ካህናትም የምእመናን በድን ያረፈበት ላይ እየኖሩ ይጸልያሉ ። እንዴት ያለ ፍቅር ነው ! በቤተ ክርስቲያን ሞታችንም ክቡር ነው ። “ክርስቲያንና ዶሮ በሞታቸው ይከብራሉ” የሚባለው ለዚህ ይሆን ?
በመጨረሻው ቀን አሥነሣዋለሁ ከሚል ይልቅ ዛሬ በጸጋ ፣ በገንዘብ ፣ በዝና አሥነሣዋለሁ ቢል ብዙ ሰው የሚደሰት ይመስላል ። የመጨረሻዋ ቀን ግን የማትመሽ ቀን ናት ። ከቊጥር ውጭም የሆነች ዘላለም ናት ። በዚያ ቀን መክበር ደስ ይላል ። መነሣታችን እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ክብር ደግሞም የደሙን ዋጋ የሚገልጥ ሲሆን ማሥነሣቱ ደግሞ የክርስቶስን ሥልጣን የሚያሳይ ነው ። የትኛውም ጠቢብና ንጉሥ ይህ ሥልጣን የላቸውም ። የጠቢባን ጠቢብ ግን የሞት መድኃኒት አለው ። የነገሥታት ንጉሥ ግን በሞት ላይ የበረታ ነው ።
“አሥነሣዋለሁ” ራሳችን ስንነሣ እንወድቃለን ፣ ሰዎች ሲያነሡን ቶሎ እንጠፋለን ። እግዚአብሔር ሲያስነሣን ግን ለዘለላም እንነግሣለን ። የተነሣነው በራሳችን ነው ወይስ በሰዎች ነው ?  በኃይሉና በቁጣው የገነነ ሰው የወደቀ ቀን አይነሣም ። በሰዎች የገነነም ከንቱና የገዛ ልቡን የከሰረ ነው። በእግዚአብሔር የተነሣ ግን በዘላለም ድንኳን የሚያበራ ነው ።
“የመጨረሻው ቀን”የተባለው የዚህ ዓለም ውጣ ውረድና የትውልድ ቀጣይነት ደግሞም የሰውና የአጋንንት ክፋት የሚያበቃበት ፣ ጻድቃን ተፈርዶላቸው ፣ ኃጥአን ተፈርዶባቸው ወደ መረጡት የሚሄዱበት ቀን ነው ። ያ ቀን ለአማንያን ዕለተ ወርቅ ነው ። ለማያምኑ ደግሞ ይግባኝ የማይጠየቅበት ፣ ንስሐ የማይገባበት ፣ ሁለተኛ ዕድል የሌለበት ቀን ነው ። ሁሉም ነገር መጨረሻ አለው ። ዛሬ የሚመጡ ነገሮች መጨረሻ ቢመስሉም መጨረሻው ግን በክርስቶስ ምጽአት የሚሆን ነው ። ለመጨረስም እርሱ ያስፈልጋል ። ዓለም የተጀመረ ነውና ይፈጸማል ። ያልተጀመረ አይፈጸምም ፣ የተፈጸመም የተጀመረ ነው ። ዛሬ መጀመር መልካም ነው ። የመጨረስ አንደኛው ጫፍ መጀመር ነው ። ዛሬ መፈጸምም ለትላንት ጅምር ዋጋ መስጠት ነው ። የምናየው ግፍና መከራ የሚጨርስበት ቀን አለ ። ክርስቶስ በመጀመሪያው ምጽአቱ ሞትን ገደብ እንደ ሰጠው በሁለተኛው ምጽአቱ መከራንም ገደብ ይሰጠዋል ። በራሱ የሚያልቅ ግፍና መከራ የለም ፣ ክርስቶስ ግን የመከራ ድንበሩ ነው ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ