የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መልካሙ የወይን ጠጅ

መልካሙ የወይን ጠጅ
ወይን ውድና ጣፋጭ ፍሬ ነው ፡፡ ይህ ውድና ጣፋጭ ፍሬ በእስራኤል ምድር እስካሁን ተትረፍርፎ ይገኛል ፡፡ በማንኛውም ድሃ ሰርገኛ ቤት ይህ ወይን ይቀርብ ነበር ፡፡ ወይን የማይቀርብበት ግብዣም እንደ ተሟላ ግብዣ አይቆጠርም ነበር ፡፡ ወይን ጠጁ ሁልጊዜ የፈላ ላይሆን ይችላል ፡፡ ለጋና በአገራችን እንደ ብርዝ ያለ የዕለት ጭማቂም ሊሆን ይችላል ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውኃውን ወይን ጠጅ በማድረጉ ሁለት ዓይነት አመለካከቶች ይንጸባረቃሉ ፡፡ የመጀመሪያው ፤ የመጀመሪያውን ተአምር ላይ እንዴት የሚያሰክር መጠጥ አደረገ የሚል ነው ፡፡ ሁለተኛው ፤ ጌታችን እንኳ ወይን ጠጅን ባርኮ ሰጥቷልና መጠጣት ተገቢ ነው የሚል ነው ፡፡ ጌታችን ከሁለቱም አስተሳሰብ ልዩ ነው ፡፡ እርሱ ሁሉን የሚያደርገው ከዘላለማዊ ቅድስናው ተነሥቶ ነው ፡፡ እነዚህን ሁለት አስተሳሰቦች መዳኘት ያስፈልገናል ፡፡
1-  በቃና ዘገሊላ ያንን ተአምር ካደረገ በኋላ  ሰዎች የመጠጣት ፍላጎታቸው አልተነሣሣም ፡፡ እንደውም ደቀ መዛሙርቱ በእርሱ አመኑ ፡፡ የሰሙትም ሁሉ በታላቅ መደመም ውስጥ እንደሚገቡ ጥርጥር የለውም ፡፡ ተአምራቱ ለበለጠ ጠጪነት ከማነቃቃት ወደ እምነትና ቅዱስ ፍርሃት ይመራል ፡፡ ይህ የተአምራት ጠባይ ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬም ይህንን ክፍል የሚያነቡ ወገኖች በተአምራቱ ሊደነቁና የእኔንም ታሪክ ይለውጣል ብለው ተስፋ ሊያደርጉ ይገባል ፡፡ ጌታችን ያከበረው ጋብቻውን እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል ፡፡
2-  ጌታችን በተአምራት የለወጠው ወይን ጠጅ መልካም የተባለለት ነው፡፡ ሰዎች የሚያቀርቡት መልካም ወይን ጠጅ አለ ፡፡ ከዚያ የበለጠ መልካም ነው ፡፡ ምክንያቱም ተአምራት ከተፈጥሮ በላይ በሆነ ድንጋጌ የሚሠራ ኃይል ነው ፡፡ ለምሳሌ አንድ በሽተኛ ሲፈወስ ከበሽታው በፊት እንደ ነበረው ጤንነት ሳይሆን ከዚያ በላይ በሆነ የሕይወት ሰላም ይሞላል ፡፡ ውኃውም ወደ ወይን ጠጅ ሲለወጥ ወይኑ በተፈጥሮ ከነበረው ጣዕም በላይ መልካም ይሆናል ፡፡
3-  ጌታችን በዚያ ግብዣ ላይ ያቀረበው የሚያሰክረውን ወይን ጠጅ አይደለም ፡፡ አንድ ወይን የሚያሰክር ለመሆን የሰው እጅ ያለበት ሂደት አለው ፡፡ ከጥንስስ ጀምሮ እስከሚቀዳ የሰው እጅ አለበት ፡፡ ጌታችን ግን የለወጠው ወይን ተፈጥሮአዊ ይዘቱን የጠበቀውን ወይን ጠጅ ትኩስ የወይን ጭማቂ ነው ፡፡
4-  ጌታችን ስለ ሥጋ ጉድለታችንም ግድ ይለዋል ፡፡ እርሱ የሥጋና የነፍስ ፈጣሪ ነው ፡፡ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን ብለን የምንጸልየው ለሥጋችን ነው ፡፡ በዚህ ጸሎት ውስጥ እግዚአብሔር ለሥጋችንም አምላክ መሆኑን ፣ በረከታችን ከሰማይ እንደሆነ ዳግመኛም የዕለት ኑሮን በመኖር ከነገ ጭንቀት እንድንድን ይመክረናል ፡፡ ስለዚህ ጌታችን በቃና ዘገሊላ የሥጋ ጉድለትን በርግጥ ሞልቷል ፡፡ የነፍሳችንን ጉድለት ስለሚሞላበት ፣ እውነተኛውን ወይን ደሙን ስለሚሰጥበት ስለ ቀራንዮም በዚሁ ሰርግ ላይ አስታውሷል ፡፡ ዛሬም በጉድለታችን ሊሞላን እርሱ ታማኝ ነው፡
5-  ጌታችን መጠጣትን እያበረታታ አይደለም ፡፡ ጉድለትን እየሞላ ፣ ሰርገኞቹንም ከሐፍረት እያዳነ ከሁሉ በላይ እናቱን እያከበረ ነው ፡፡ ክርስቲያኖች ከሚያሰክር መጠጥ ቢከለከሉ በጣም የተሻለ ነው ፡፡ ይልቁንም መነኮሳትና ዘመናቸውን ለእግዚአብሔር የሰጡ ናዝራውያን ፈጽመው መራቅ ይገባቸዋል ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስካር ያመጣውን ስብራት ስናይ ፈጽመን ልንርቅ እንዲገባን ያስገነዝበናል ፡፡ ጻድቁ ኖኅ ከጥፋት ውኃ ድኖ ከብርጭቆ አልኮል ግን አልዳነም ፡፡ ሎጥ ከሰዶም እሳት አምልጦ ከሥጋ እሳት ከፍትወት ውስጥ የገባው በመጠጥ ነው ፡፡ መጠጥ የፈቃድ እብደትን ያውም የሚገዛ እብደትን የሚያመጣ ነው ፡፡ ይልቁንም በዛሬው ዘመን ሰዎች ከመጠጥ ፈጽመው መራቅ ይገባቸዋል ፡፡ የዛሬውን ሰው የሚገልጥ የካርቶን ሥዕል መሥራት ብንችል ጭንቅላቱ እስከ ወገቡ የደረሰ ፣ የሰለሉ እጅና እግሮች ያሉት ብለን መግለጥ እንችላለን፡፡ የዛሬው ሰው ጭንቅላቱ በብዙ ነገሮች ተወጥሯል ፡፡ በዚህ ላይ መጠጥ መጨመር በቀላሉ እንዲወድቅ ያደርገዋል ፡፡ ከባድ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎችና ብስጩዎች ፈጽመው ሊርቁ ይገባል ፡፡ ጠጪዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ይፈልጋሉ ፡፡ ስለ ዘላለም ሕይወት ያለውን ጥቅስ መያዝ አይችሉም ፡፡ “ወይን ያስተፌሥሕ ይላል ቃሉ” በማለት ሲናገሩ ይደመጣሉ ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ፡- መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና” ይላል /ኤፌ .5፡18/ ፡፡
ይሙላባችሁ የሚለውን ቃል ማሰብ መልካም ነው ፡፡ የሚፈስስ የሞላው ነገር ነው ፡፡ መሞላት በቁጥጥር ሥር መዋል ነው ፡፡ በወይን ጠጅ ቁጥጥር ሥር አትዋሉ ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር ዋሉ እያለን ነው ፡፡ መጠጥ ልማድ ነው ፡፡ ከዚያ ይልቅ መደበቂያና ደስታን በአቋራጭ መፈለጊያ ነው ፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን ደስታ ግን ተዘዋዋሪ ጉዳት የሌለው ከራስ ተርፎ ለሌላው የሚፈስስ ነው ፡፡ መጠጥ እስክንጠጣው እንቆጣጠረዋለን ፣ ከጠጣነው በኋላ ግን ይቆጣጠረናል ፡፡ ልክን አውቆ መጠጣት የሚባለው በገደል አፋፍ ላይ እንደመሄድ ነው ፡፡ የገደል አፋፍ ለመቆምም ፣ ለመቀመጥም ፣ ለመራመድም አሳሳቢ ነው ፡፡ መጠጥ ማባከን ነው፡፡ ጥገኛ ደስታን ስለሚወልድ እውነተኛውን ደስታ ያራቁታል ፡፡ ገንዘብን ያባክናል ፡፡ የትዳርን ሰላም ፣ የማኅበረሰብን ክብር ያሳጣል፡፡ የማሰብ አቅምን እያዳከመ ይመጣል ፡፡ ንቃትን እየነሣ በሽታዎችን እያፋፋመ ዕድሜን ያሳጥራል ፡፡ መጠጥ ለሌሎች ኃጢአቶች መንገድ ያመቻቻል ፡፡ ካላሰቡበት የሕይወት ገጠመኝ ላይ ይጥላል፡፡ ጌታ በተአምራት የለወጠው የቃና ዘገሊላው ወይን ጠጅ ትኩስና ከተለመደው ወይን ጠጅ በጥራቱም በጣዕሙም የተለየ ነው ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ