የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እውነተኛው ብርሃን

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሐሙስ የካቲት 24/2008 ዓ.ም.
“ብርሃንም በጨለማ ይበራል ጨለማም አላሸነፈውም” /ዮሐ. 1፡5/፡፡
በዮሐንስ ወንጌል ብርሃን የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ተጠቅሷል፡፡ ብርሃን ሲልም በዋናነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታል /1፡7-8፤3፡19፤8፡12፤9፡5፤12፡36፤12፡46/፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በብርሃንነት የተጠቀሰው በሚከተሉት ምክንያች ነው፡-
1-  የማያሳፍርና የማይጨልም ምሕረት በመሆኑ
2-  የማያዳላና በጨለማ ላይ የሚያበራ ብርሃን ስለሆነ
3-  ሰዎች ባያምኑት እርሱ ክፉ ስለሆነ ሳይሆን ክፋታቸው ስላስቸገራቸው እንደሆነ
4-  ራስን የሚያሳይና ከከሳሽነት የሚያድን ትሑት ብርሃን መሆኑን
5-  ፀሐይ ብትወጣም በሩን የዘጋ እንደማያያት ክርስቶስም ወደ ዓለም ቢመጣም በራቸውን የዘጉ አያዩትም፡፡
በዮሐንስ ወንጌል ብርሃን እውነትንና እውቀትን ያመለክታል፡፡ በዓለም ላይ ብዙ እውነቶች አሉ፡፡ የመረጃ እውነት፣ የማስረጃ እውነት፣ የሳይንስ እውነት፣ የታሪክ እውነት… አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚያድኑ እውነቶች አይደሉም፡፡ አንድ እውነት አለ፡፡ እርሱም መድኃኒት የሆነልን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው /ዮሐ. 14፡6/፡፡ ያለ እውነት ማወቅ የለም፡፡ ያለ እውነት የምናውቀው እውቀት ሐሰተኛ እውቀት ነው፡፡ እውነተኛ አምልኮና እውነተኛ ሕይወትን እግዚአብሔር ይፈልጋል፡፡
ወንጌላዊው ይህን ዓለም ጨለማ ይለዋል፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረውን ዓለም እየኮነነ ሳይሆን ኃጢአት የበከለውን አስተሳሰብ እየገለጠ ነው፡፡ ጨለማ ራስንና ሌላውን አያሳይም፡፡ በጨለማ የተያዘው ዓለምም ራሱን በንስሐ ሌላውን በጸሎት አያይም፡፡ ጨለማ ያሉበትን አካባቢና የሚሄዱበትን መንገድ አያሳይም፡፡ በጨለማ ሳንደርስ የደረስን፣ ደርሰን የቀረን ይመስለናል፡፡ የእግዚአብሔር ብርሃን ያለንበትን የሚያሳውቅ ነው፡፡ ደርሰንም ከሆነ ምስጋናው ለእግዚአብሔር ነው፣ ቀርቶንም ከሆነ የሚያደርሰን እርሱ ነው፡፡ ጌታችን፡- “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ብሎ ሲናገር አንዲት ሴት ስታመነዝር ተገኝታለችና እንውገራት የሚሉ ከሳሾች መጥተው ነው /ዮሐ. 8፡12/፡፡ ጌታችን ራስን የሚያሳይ ብርሃን መሆኑን ገለጠ፡፡ የፀሐይ ብርሃን ሌላውን ያሳያል፡፡ የሕይወት ብርሃን የሆነው ጌታችን ግን ራስን ያሳያል፡፡ እጃችን ተቆርጦና ተንጠልጥሎ ወደ ሐኪም ቤት የምንሄደው ቀጥሉልኝ ለማለት ነው፡፡ ለምን? ስንል አካል ነውና ገላግሉኝ አንልም፡፡ ዛሬ እንደ አካል ለመተያየት ይህ ብርሃን ያስፈልገናል፡፡ እንደ ድርጅት ስንሆን ያንዱ መጎዳት አይሰማንም፡፡ እንደ አካል ስንሆን ግን የሌላው ሕመም ሕመማችን ነው፡፡ እንደ አካል ብንተያይ ኖሮ እንዲህ አንጨካከንም ነበር፡፡ አካልነት ፍቅርን ያመጣል፡፡ አካልነት እንዲመጣ በብርሃን መጠመቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብርሃን ግን አጋላጭ ብርሃን ሳይሆን ሸፋኝ ብርሃን ነው፡፡ አዳምና ሔዋን የለበሱት ልብሰ ብርሃን፣ ራቁታቸውን ሆነው እንዳይተፋፈሩ ያደረገው የቅድስና ብርሃን ይህ ነው፡፡ ነቢዩም ብርሃን ልብስ መሆኑን ሲገልጥ፡- “ብርሃንን እንደ ልብስ ለበስህ ሰማይንም እንደ መጋረጃ ዘረጋህ” ይላል /መዝ. 103፡2/፡፡ ብርሃን ልብስ ነው፡፡ ክርስቶስ ብርሃን ነው ስንል ልብሳችን ነው እያልን ነው፡፡ የሚሸፍነን ብርሃን ነው፡፡ ወደ እርሱ ስንመጣ በምሕረት ይቀበለናል፡፡ የካቶሊኩ ፖፕ ፍራንሲስ፡- “ሰዎች ምሕረትን ለግል መጽናናት ይፈልጉታል፤ ምሕረት ግን ለሰው ልጆች የተሰጠ መሆኑን አይረዱም” ብለዋል፡፡ አዎ ሰዎች ለራሳቸው እግዚአብሔር መሐሪ እንዲሆን፣ ለሌሎች ፈራጅ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፡- “መካሰስ ከተጀመረ እስር ቤት የማይገባ ማንም የለም” ብሏል፡፡ ነቢዩ እግዚአብሔርን፡- “ብርሃን እንደ ልብስ ለበስህ” አለው፡፡ በመቀጠልም “ሰማይንም እንደ መጋረጃ ዘረጋህ” ይለዋል፡፡ መጋረጃ ወደ ጎን ነው፡፡ ከላይ ጣራ እንጂ መጋረጃ እንዴት ይኖራል? የእኛ ኃጢአት እንዳይታይ እግዚአብሔር የሰማይን መጋረጃ ማድረጉን መግለጡ ነው፡፡ የምሕረቱን ብዛት ለመግለጥ ነው፡፡
ፀሐይ ሥራ ታሠራናለች እንጂ አትሠራንም፡፡ ክርስቶስ ግን የሚሠራን ብርሃን ነው፡፡ በምድር ላይ ጨለማ የሚሆነው ፀሐይ ዞር ብላ ሳይሆን ምድር ገልበጥ ስትል ነው፡፡ የሚጨልመን እግዚአብሔር ስፍራ ቀይሮ ሳይሆን እኛ ስፍራ ለቀን ነው፡፡ ወንጌላዊው ሕይወትን በቀላል ዘይቤ ይገልጣታል፡፡ ብርሃንና ጨለማ በማለት በአጭሩ ያብራራታል፡፡ በዓለም ላይ ያሉት እነዚህ ሁለት ማዕቀፎች ናቸው፡፡ ሦስተኛና ገለልተኛ ስፍራ የለም፡፡ ስለዚህ በአንዱ ውስጥ ካለን በሌላው ውስጥ የለንም፡፡ ወይ በብርሃን ነን፣ ወይ በጨለማ ነን፡፡ ጨለማና ብርሃን በመቀዋወም እንጂ በመስማማት ኖረው አያውቁም፡፡ ይህን ሲገልጥ ጌታችን በመጀመሪያው ተስፋ የሴቲቱ ዘርና የእባቡ ዘር እርስ በርስ እንደሚቀዋወሙ ተናግሯል /ዘፍ. 3፡15/፡፡ ብርሃን ከጨለማ ጋር ካልተቃረነ በራሱ ጨለማ ነው፡፡ ብርሃንና ብርሃን አይጣሉም፡፡ በግድ አንዱ ጨለማ ነው፡፡ ብርሃን ብርሃን የሚሆነው ወደ ራሱ ሳያስቀር በሙሉነት ስለሚረጭ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ራሱ የቆጠበው ሳይኖር ፍጹም መሥዋዕት በመሆኑ ብርሃናችን ሆኗል፡፡ ዛሬም ወደ ራሱ የሚቆጥብ ራስ ወዳድ ጨለማ እንጂ ብርሃን መሆን አይችልም፡፡
ኦሪት ዘፍጥረትና የዮሐንስ ወንጌል ተመሳሳይነት አላቸው ብለናል፡፡ በኦሪት ዘፍጥረት 1፡3 ላይ፡- “ብርሃን ይሁን” በማለት ሥራውን ጀምሯል፡፡ እግዚአብሔር በሕይወታችን ሥራውን ሲጀምር ብርሃንን በማወጅ ነው፡፡ ያ ብርሃን ሲመጣ ከጎደለን ያለን ብዙ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ያ ብርሃን የማስተዋል ባለጸጋ ያደርገናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ