መስከረም 1 ቀን 2004[September, 12 2011]
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መስከረም 1 ቀን የዘመን ነገር የአጽዋማትና በዓላት አወጣጥ ከቅዳሴ በኋላ የሚታወጅበት ነው፡፡ የባሕረ ሐሳቡ ሊቅ ሥነ ፍጥረቱንና የአጽዋማትና በዓላቱን አወጣጥ ሲተርኩ መስማት እጅግ ደስ ያሰኛል፡፡ በዓላትና አጽዋማት ሲወጡም አሥርቆት ይደረጋል፡፡ አሥርቆት ማለት የሌሊትና የመዓልት መባቻ የሚታወቅበት መንገድ ነው፡፡
የአጽዋማትና የበዓላቱን አወጣጥ በዝርዝር እንመልከት፡፡
የ7504 ዓመተ ዓለም፣
የ2004 ዓ. ም.
አጽዋማትና በዓላት የሚውሉባቸው ዕለታት
ጾመ ነነዌ ጥር 28 ቀን ሰኞ
ዐቢይ ጾም የካቲት 12 ቀን ሰኞ
ደብረዘይት መጋቢት 9 ቀን እሑድ
ሆሣዕና መጋቢት 30 ቀን እሑድ
ስቅለት ሚያዚያ 5 ቀን ዓርብ
ትንሣኤ ሚያዝያ 7ቀን እሑድ
ረክበ ካህናት ግንቦት 1 ቀን ረቡዕ
ዕርገት ግንቦት 16 ቀን ሐሙስ
ጰራቅሊጦስ ግንቦት 26 ቀን እሑድ
ጾመ ሐዋርያት ግንቦት 27 ቀን ሰኞ
ጾመ ድኅነት ግንቦት 29 ቀን ረቡዕ
እነዚህ አጽዋማትና በዓላት እንዴት ተገኙ?
የተገኙት በመደበኛው የፀሐይ አቆጣጠር ሳይሆን በሁለቱ ብርሃኖች ፀሐይና ጨረቃ ጥምር አቆጣጠር ነው፡፡
በፀሐይ አመት 365 ቀንና በጨረቃ ዓመት 354 ቀን መካከል ያለው የየዓመቱ የ11 ቀናት ልዪነት ለበዓላቱ ማግኛ የሚረዳ በመሆኑ አበቅቴ ይባላል፡፡ ተረፈ ዓመት ማለት ነው፡፡
አበቅቴ በየ19 ዓመቱ የሚመላለስ ዐውድ አለው፡፡ ይህም ዐውደ አበቅቴ ይባላል፡፡ ከአበቅቴ ጋር ተዛምዶ ያለው መጥቅዕ ነው፡፡የጨረቃ ዓመት በነሐሴ ወይም በጳጉሜን ይጀምርና በመስከረም ወይም በጥቅምት 30ኛ ቀኗን የምታከብርበት ዕለት መጥቅዕ ይባላል፡፡ መጥቅዕ ደውል ማለት ሲሆን የአይሁድን አዲስ ዓመት ያመለክታል፡፡ ከመስከረም 15 እስከ ጥቅምት 13 ቀን ድረስ ባሉት 29 ቀኖች መካከል ይውላል፡፡
መጥቅዕ ከመስከረም 15 እስከ መስከረም 30 ሲውል ነነዌ በጥር ይውላል፡፡
ከጥቅምት 2 እስከ ጥቅምት 13 ሲውል ነነዌ በየካቲት ይውላል፡፡
የባሕረ ሐሳብ መነሻው ዓመተ ዓለም መቁጠሪያው ዐውደ አበቅቴ ስለሆነ፡-
መጀመሪያ የ2004 ዓ.ም. ን ዓመተ ዓለም እንፈልጋለን፡፡
5500 + 2004 = 7504 ይሆናል፡፡
አሁን 7504ን ለ 19 አካፍለን ቀሪውን እንይዛለን(እንገድፋለን)
7504 ÷ 19 = 394 ደርሶ 18 ይተርፋል፡፡
ይህም ማለት ዓለም ከተፈጠረበት እስከ 2004 ዓ.ም. ድረስ 394 ዐውደ አበቅቴ ሞልቶ የ395ኛው ዐውድ 18ኛ ዓመት ላይ ደርሷል ማለት ነው፡፡
2004 ተጀመረ እንጂ ስላልተፈጸመ ከ18ኛው ዓመት ላይ አንድ ቀንሰን 17 እንገኛለን፡፡ ይህን ወንበር እንለዋለን፡፡ ባለፉት 17 ዓመታት ስንት አበቅቴዎች(በፀሐይና በጨረቃ መካከል ያለው የ11 ቀን ልዩነት(365-354 = 11)እንዳለፉ ያሳየናል፡፡
በዚህም መሠረት የ2004 አበቅቴ 11 × 17 = 187 ይደርሳል፡፡ እርሱም ለ 30 ይካፈላል፡፡
187 ÷ 30 6 ደርሶ 7 ይቀራል፡፡
አበቅቴው 7 ሆነ ይሏል፡፡
መጥቅዕን ለማወቅ ቀላሉ መንገድ አበቅቴ + መጥቅዕ =30
መጥቅዕ = 30 – አበቅቴ
= 30 -7
= 23
የመጥቅዕ ወሰን በመስከረም 15 እና በጥቅምት 13 መካከል በመሆኑ 23 ደግሞ ከ15 በላይ በመሆኑ መጥቅዕ መስከረም 23 ይውላል፡፡
መጥቅዕ መስከረም 23 መዋሉን ካወቅን በኋላ መስከረም 23 ምን ቀን እንደዋለ ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ እርሱን ለማወቅ ደግሞ የግድ መስከረም 1 ቀን ምን ቀን እንደዋለ ማወቅ አለብን፡፡
መስከረም 1 ምን ቀን እንደዋለ ለማወቅ፡-
ዓመተ ዓለሙን ለዓውደ ፀሐይ እናካፍላለን፡፡ ዓውደ ፀሐይ በየ 28 ዓመቱ የሚደጋገም ሲሆን በየ28 ዓመቱ መስከረም 1 ቀን ላይ እኩል የፀሐይና የጨረቃ መስከረም 1 ቀን ረቡዕ ዕለት ይጀምራል፡፡
ዓመተ ዓለሙን ለዐውደ ፀሐይ ስናካፍል
7504 ÷ 28 = 71 ደርሶ 16 ይተርፋል፡፡
እንደሚታወቀው ሁሉ በአንድ ዓመት ውስጥ 365 ¼ ቀናት አሉ፡፡
በአንድ ዓመት 52 ሳምንታት አሉ፡፡
52 × 7 = 364 ቀን ይሆናል፡፡
በአንድ ዓመት 1 ¼ ቀን ተንጠልጥሎ ይገኛል፡፡
¼ ኛው በ የአራት ዓመቱ 6ተኛ ጳጉሜን ሆኖ ይያዛል
በ አንድ ዓመት 1 ሙሉ ቀን ከተገኘ በ 16 ዓመት 16 ቀን ይገኛል፡፡
በ16 ዓመት ውስጥ ጳጉሜን 6 የምትሆነው 4 ጊዜ ነው፡፡
ስለዚህ 16 + 4 = 20 ቀን
ይህንን 20 ቀን በሳምንቱ ቀናት እናከፋፍላለን፤ 20 ÷7 = 2 ደርሶ 6 ይተርፋል፡፡
ፀሐይና ጨረቃ ከተፈጠሩበት ከረቡዕ ተነሥተን ስንቆጥር ረቡዕ 1 ብሎ፣ ሐሙስ 2፣ ዓርብ 3፣ ቅዳሜ 4፣እሑድ 5፣ ሰኞ 6፣ ማክሰኞ 7 ብሎ ያበቃል፡፡በዚህም መሠረት መስከረም 1 ቀን ሰኞ ውሏል፡፡
መስከረም 1 ሰኞ ስለዋለ መስከረም 23 ማክሰኞ ይውላል፡፡ ተዘዋዋሪ በዓላቱና አጽዋማቱ የሚገኙት መጥቅዕ፣ መጥቅዕ የሚውልበት ተውሳክና የበዓላትና የአጽዋማት ተውሳክ በመደመር ነው፡፡
በዚህም መሠረት የመስከረም 23 ማክሰኞ ተውሳክ እና መጥቅዑን አንድ ላይ እንደምራለን፡፡
የዕለት ተውሳክ ከቅዳሜ 8 ተነሥቶ እሑድ 7 እያለ…. ዓርብ 2 ላይ ይደርሳል፡፡
ስለዚህ የማክሰኞ ተውሳክ 5 ይሆናል፡፡
የማክሰኞ ተውሳክ 5 ከመጥቅዕ 23 ጋር ሲደመር (5+23) 28 ይሰጠናል፡፡ ይህም መባጃ ሐመር ይባላል፡፡ በርሱም ጾመ ነነዌ ይታወቃል፡፡ ነነዌ ጥር 28 ቀን 2004 ዓ.ም. ይውላል፡፡
ዐቢይ ጾም(ሁዳዴ) የነነዌ ጾም ከገባባት ማግስት ጀምሮ ከ14 ቀን በኋላ ይገባል፡፡
28 + 14 = 42፡፡ ይህም 30ው የጥር 12ቱ የየካቲት ሆኖ ዐቢይ ጾም የካቲት 12 ቀን ይገባል፡፡
ደብረዘይት = 28 + 11(41) =39 = መጋቢት 9
ሆሳዕና = 28 + 2(62) = መጋቢት 30
ስቅለት = 28+7(67) = ሚያዝያ 5
ትንሣኤ = 28 +9(69) = ሚያዝያ 7
ረክበ ካህናት = 28 + 3(93) = 31 = ግንቦት 1
ዕርገት = 28 + 18(108) = 46 = ግንቦት 16
ጰራቅሊጦስ = 28 + 28(118) = 56 = ግንቦት 26
ጾመ ሐዋርያት = 28 + 29(119) =57 = ግንቦት 27
ጾመ ድኅነት = 28 + 1(121) = ግንቦት 29 ይውላሉ፡፡
የቀመሩ መንገድ ይህ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት፣ በረከቱና ሰላሙ ዓመቱን ሙሉ አይለየን፡፡