ምእመኑ በታላቅ ምሬትና የነፍስ ዝለት ሁኖ አምላኩን ጠየቀ ፡-
ጌታ ሆይ በሰዎች ላይ የማየው በጎ ነገር “ምነው የእኔ ቢሆን” እላለሁ ። የእኔ አልታይህ እያለኝ በሌሎች ዕድል እጓጓለሁ ። ፍለጋ አያልቅም ወይ ? ትላንት የማልደርስበት የመሰለኝን ዛሬ አልፌ ሄጃለሁ ፣ በጥቂት ስጸልይ በብዙ ተቀብያለሁ ። ጌታ ሆይ ታዲያ የልብ ሙላት የሚሆነኝ ምንድነው ?
እግዚአብሔርም መልስ ሰጠ ፡-
ልጄ ሆይ ራበኝ ለሚለው ጥያቄህ እንደራራሁ አልረካሁም ለሚለው ጥያቄህም ራራለሁ ። መላው የሰው ዘር ራበኝና አልረካሁም በሚል ጥያቄ ለሁለት ተከፍሏል ። ስለ ተራቡ ሰዎች የእርዳታ ተቋማት ፣ የመንግሥታት ስብሰባ አጀንዳ አላቸው ። አልረካሁም ለሚሉ ግን ሁሉ ይፈርድባቸዋል ። ልጄ ሆይ በሰማይ ላይ ያለውን ውብ ቀስተ ደመና ወደ ታች ስበህ በሠዓሊው ሸራ ላይ ማተም አትችልም ። በሌሎች ላይ የምታየውን ውበት ነጥቀህ የራስህ ማድረግ በፍጹም አትችልም ። ሰማያዊውን አምላክ ግን በልብህ መጋበዝ ፣ የክርስቶስን ውበት በዘመንህ መግለጥ ትችላለህ ። ከቀስተ ደመና ውበት ከቆነጃጅትም ድምቀት ይልቅ በጎነት የበለጠ ያምራል ። ቀስተ ደመና ይሰወራል ፣ ቁንጅናም ከንቱ ነውና ይረግፋል ። የእኔ ጽድቅ ግን ለዘላለም ይኖራል ። አንተ ጋ ያለውን በጎ ዕድል ሌላው ይመኘዋል ። ያልበሰለው ማንነትህ የያዘውን እያሳነሰ እንደ ሕፃን በሰው እጅ ባለው ያለቅሳል ። ላንተ የሰጠሁህ የማይኮረጅ ጥበብ ፣ የማይገኝ ልዕልና ነው ። የእኔ በረከት የማይደገም ልዩ ነው ። የሰው አለመርካት በሦስት ነገር ተሸፍኗል ፡- በጥርስ ፣ በልብስና በቤት ። እኔ ግን እያረሩ የሚስቁትን አዝንላቸዋለሁ ። ጥሩ ለብሰው ውስጣቸው የሚበርዳቸውን አለሁ እላቸዋለሁ ። ባማረ ቤት ውስጥ ያለውን ድብቅ ልቅሶም ዘንበል ብዬ እሰማለሁ
ልጄ ሆይ ወደ ራስህ በጣም አትኩረህ አትይ ። በመስተዋት ራሱን በጣም የሚያይ ሞኝ እየሆነ ይመጣል ። ዞር ያለበት እስኪመስለውም የምናብ ዓለም ውስጥ ይገባል ። ራስህን ያለ እኔ ጽድቅ አትየው ። ያልተዘጉ ፋይሎችህ እንደሚያውኩህ አውቃለሁ ። በንስሐና በቃል ኪዳን ዝጋቸው ። አልችልም ብለህ ከመቀመጥህ ይልቅ እችላለሁ ብለህ መውደቅህ ያስደስተኛል ። የልብ ሙላትን የምታጣው ነፍስህ እውቀት ፣ መንፈስህ አምልኮት ፣ አካልህ በጎ ምግባር ሲራብ እንደሆነ እወቅ ። ባዶነት የነፍስ ጠኔ መሆኑን ብዙ ጊዜ አልነገርኩህምን ? ነፍስ በእንጀራ እንደማትጠግብ አላስተማርኩህምን ? ደግሞም ልብህ ከፍቅር ሲባረድ ፣ ይቅር ማለት ሲያቅትህና ይቅር ያልከውን መልሰህ ስታስታውስ እንደምትጎዳ የነገርኩህን ረሳኸውን ? ስለሞላም ስለሚሞላም ደስ አይበልህ ። እኔ አምላክህ ስለሆንሁ ብቻ ደስ ይበልህ ። የሙት ልጆች ማደጊያ ውስጥ ያሉ ደህና ቁርስ ይበላሉ ፣ ወላጅ ካላቸው የድሀ ልጆች ይልቅ በጥሩ ይያዛሉ ። እነርሱ ግን ምነው ወላጅ በኖረኝ ይላሉ ። መዓዛ ካለው ምግብ ይልቅ እኔ እበልጣለሁ ፣ ከጥሩ ውኃ ይልቅ እኔ አረካሃለሁና አይዞህ ልጄ ሆይ ንቃ ፣ ተነቃቃ ።
ምእመኑም ትንፋሹን ወደ ውስጡ አስገብቶ ተረጋግቶ መጠየቅ ጀመረ ፡-
ጌታ ሆይ አንተ ስትናገረኝ እጽናናለሁ ፣ መጽናናቴ ግን ዕድሜ ያጣና ወደ ተውኩት ጉዳቴ እመለሳለሁ ። በሌሎች ላይ የማየውን ኀዘንና ሰቆቃ ከማዘንና ከመርዳት ወደ ራሴ አምጥቼ እታመመዋለሁ ። የሚጠዘጥዘው ሰው ሳይ ሲጠዘጥዘኝ ያድራል ። ደግሞ እንዲህ ብሆንስ እያልሁ ራሴ ያመለጠኝ መስሎኝ በግምት እሰቃያለሁ ። ጌታ ሆይ አታረጋጋኝም ወይ ?
እግዚአብሔርም በጽድቅ መለሰ፡-
ልጄ ሆይ ልደትና ሞት በቅጽበት ነውና ለደቂቃም መረጋጋትህን ውደደው ። እኔ እየሸነገልሁ አልናገርም ፣ ከዓለም ማባበል የእኔ ተግሣጽ ሕይወትን ያሳርፋል ። እኔ የመልሶች መልስ ነኝ ። የውዶችም ውድ ነኝ ። ሁሉ በእኔ ምክንያት ይወደዳሉ ፤ እኔ ግን ስለ ራሴ የምወደድ ነኝ ። መጽናናትህ ዕድሜው አጭር ሲሆን አትደንግጥ ፣ ዘላለማዊ ስጦታ እኔ ብቻ እንደሆንሁ ታውቅ ዘንድ ይህ መናወጥ ባንተ ውስጥ ሆኗል ። ያለኸው የመምጣቴ ዋዜማ ላይ ነውና ቃሎቼ መፈጸም ስላለባቸው ሁከትና ሽብር ይሆናል ። አስቀድሜ ነግሬህ እንዲህ የታወክህ ባልነግርህ ምን ልትሆን ነበር ? የሌሎችን ስቃይ ተውሰው ሲሰቃዩ የሚያድሩ እንዳሉ አውቃለሁ ። የእነርሱ ስቃይ ግን ቤዛ አይሆንምና ሌሎች አያርፉበትም ። እኔ ግን የዓለም ቤዛ ነኝና በቁስሌ ፈውስን ፣ በሞቴ ሕይወትን ሰጥቼሃለሁ ።
ልጄ ሆይ የሰዎችን ችግር ባታስቀር መቀነስ ግን አንተ የምትኖርበት ዓላማ መሆኑን እወቅ ። ሰይጣን እንዲህ ብትሆንስ እያለ ሲያስፈራራህ “እግዚአብሔር ይገሥጽህ ፣ በማይላሉ እጆች ተይዣለሁ” በለው ። ተኝተህም ነቅተህም የምጠብቅህ እኔ ነኝና አትፍራ ። ስሜ ባንተ ላይ ስለ ተጠራ እንዲሁ አልተውህም ። በዋጋ ገዝቼ በነጻ አልለቅህም ። አንተ በጥዋት የፀሐይ ጮራ ደስ ይልህ ይሆናል ። እኔ ግን ባንተ ደስ ይለኛል ። አንተ አቁሳይ ልጅ ነኝ ብትልም ፣ እኔ ግን የደስታ መደምደሚያዬ እልሃለሁ ። አንተ በራስህ ላይ ያለህ ዓላማ ቢጠፋህ እኔ ግን ልገለጥብህ እየሠራሁህ ነው ። የሚመጣውን ጊዜ ትዋጅ ዘንድ ዛሬ በቤተ ሙከራ ውስጥ እያሳለፍኩህ ነውና ልጄ ሆይ በርታ ። እኔ አልታዘብህምና ሁሉንም ንገረኝ ። የድንጋይ ሸክምህን አቅልዬ ንጉሣዊ ህለተ ወርቀ አስጨብጥሃለሁ ። ማቅህን ቀድጄ ወርቅ አለብስሃለሁ ። አንተን ሳይሆን ባንተ ላይ ያለውን የእኔን ፍቅር አያለሁ ። መንገዱን አትፍራ ፣ የምድረ በዳ ወዳጅህ ይኸው አጠገብህ ነኝ ። ይህን ድምፄን ስማና ህልውናዬን ዘምርበት ።
ወደ ክርስቶስ መገስገስ 5
ተጻፈ አዲስ አበባ
መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም.