የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ለምን ?

አባ እንጦንስ ስለ እግዚአብሔር ጥልቅ ፍርድ ሲያስብ ፡- “ጌታ ሆይ አንዳንዶች ገና ወጣት ሳሉ የሚሞቱት ሌሎች ደግሞ ከወጣትነት እስከ ሽበት ብዙ ዘመን የሚኖሩት ለምንድነው ? ጌታ ሆይ አንዳንዶች ምንም የሚላስ የሚቀመስ የሌላቸው ድሆች ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ተርፏቸው የሚደፉ ባለጠጎች ለምን ይሆናሉ ? ደግሞስ ኃጢአተኞች በስኬት ሲኖሩ ቅኖች ግን ለምን ይቸገራሉ ?” ብሎ ጠየቀ ፡፡ አንድ ድምፅ እንዲህ ብሎ ሲመልስለት ሰማ ፡- “እንጦንስ ሆይ ትኩረትህን ራስህ ላይ አድርግ ፤ እነዚህ ነገሮች ለምን እንዲህ እንደሆኑ በእግዚአብሔር እውቀት ውስጥ ያለ ነገር ነው ፡፡ ስለ እነዚህ ነገሮች ማወቅ ላንተ ምንም ጥቅም የለውም ፡፡”
በዘመናት ሁሉ የነበሩ ከነቢይ እስከ ፈላስፋ ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የጠየቁት ጥያቄ ቢኖር “ለምን ?” የሚለውን ጥያቄ ነው ፡፡ ብዙዎችም እንደ ገደል ማሚቱ የተናገሩትን ድምፅ መልሰው ከመስማት በቀር ማረፍ አልቻሉም ፡፡ ፍልስፍና በሰው ተጀምሮ በሰው የሚጠናቀቅ በመሆኑ መጨረሻው ጥርጣሬና ክህደት ነው ፡፡ እምነት ግን በእግዚአብሔር ተጀምሮ በእግዚአብሔር የሚልቅ በመሆኑ ዕረፍት አለው ፡፡ ፍልስፍና ከጥያቄ ወደ ጥያቄ ሲሄድ እምነት ግን ከጥያቄ ወደ መልስ ይሄዳል ፡፡ በእምነት ዓለም እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ነገሮች መልስ አይሰጥም ፣ ራሱ ግን መልስ ነው ፡፡ መልስ ቢሰጥ ሊቅ ነው እንለዋለን ፤ እርሱ ግን ራሱ ጥበብ ነው ፡፡ መልስ ቢሰጥ መምህር ብቻ እንለዋለን ፤ እርሱ ግን ህልውናው ዕረፍት ነው ፡፡
በዚህ ዓለም ላይ በክፉዎች የሚቀኑ አያሌ ናቸው ፡፡ “እኔ እግዚአብሔር ፣ እግዚአብሔር እላለሁ ፤ የተመቻቸው ግን ከሃዲዎቹ ናቸው” የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ ፡፡ ደግሞም በፍትሐዊ አእምሮ ሆነው ክፉዎች እየገነኑ ደጎች እያነሡ ለምን ይሄዳሉ ? የሚሉ አያሌ ናቸው ፡፡ ነቢዩ ዕንባቆም ይህን ጥያቄ አንሥቷል ፡፡ ስለ ፍርድ መጓደል ፣ ማለቂያ ስለሌለው የድሆች መገፋት እግዚአብሔርን ሞግቷል ፡፡ “የእኔ ክፉ ዓይኖች ማየት ያልቻሉትን ግፍ የደጉ ጌታ ዓይኖች እንዴት ችለው አዩ ?” በማለት የጠየቁ ብዙ ናቸው ፡፡ ስድስት ሚሊየን አይሁድ በናዚዎች ሲፈጁ እግዚአብሔር እንዴት ዝም አለ ? በማለት ፍትሕ ፈላጊ አእምሮአቸው መልስ አጥቶ እግዚአብሔር የለም ያሉ አያሌ ናቸው ፡፡  ነገር ግን ግፍና ፍትሕ ሳይኖር ከዓለም አስቀድሞ እግዚአብሔር ነበረ ፡፡ የእግዚአብሔርን እጅ ስንፈልግ እኛስ የድርሻንን ተወጥተናል ወይ ? በዓለም ላይ ያለው ችግርስ እኛ የፈጠርነው ነው ወይስ እግዚአብሔር የላከው ነው ? ከሞቱት ሰዎች ይልቅ እኛ ለምን ኖርን ? ብለን ጠይቀን እናውቃለን?
አንዳንድ ሰዎች የራሳቸውን ድካም ያዩና ከክርስትና ውጭ ያሉ ሰዎችን ብርታትና የመዳን ናፍቆት በማየት እኔ ከእነርሱ በምን ተለይቼ ነው ክርስቲያን የሆንኩት ? የተሻሉ እያሉ የወደቅሁ እኔ እንዴት በእምነት ዓለም ተገኘሁ ? ይላሉ ፡፡ ይህ አመለካከታቸውም ቅድመ ውሳኔ ቢኖር ነው ፣ አስቀድሞ የሚጸድቀውና የሚኰነነው ቢወሰን ነው እንዲሉ አድርጓቸዋል ፡፡ ነገር ግን ሌሎች ለምን ጠፉ ሳይሆን እኔ ለምን ዳንሁ ? ማለት ወደ መንፈሳዊነት ይመራል ፡፡ ጌታችን በሌሎች መሞት ወይም በሌሎች ላይ በደረሰው አደጋ ተገርመው ፣ ምን ቢበድሉ ነው ? ለማለት ዜናውን ይዘው ለመጡት፡- “ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ” በማለት ተናግሯል /ሉቃ. 13፡3/፡፡ ይህ ብቻ አይደለም አሁንም ያሉት በኃጢአታቸውና በእነርሱ መካከል የእግዚአብሔር ምሕረት ጣልቃ ስለ ገባ መሆኑን ስለ ሌሎች መጥፋት ሲያስቡ እነርሱም ካልተመለሱ ከምድራቸው እንደሚነቀሉ ማለትም በ70 ዓ.ም ስለሚመጣው ፍርድ ነግሯቸዋል ፡፡
አዎ እግዚአብሔር አሰጣጡ ለየራስ ነው ፡፡ ለአንዱ የመብላት አምሮትን ለሌላው ደግሞ ምግብን ፣ ለአንዱ ጫማ ለሌላው ደግሞ እግር፤ ለአንዱ እንቅልፍ ለሌላው ደግሞ አልጋ ፤ ለአንዱ መታከሚያ ገንዘብ ለሌላው ደግሞ ጤና ፤ ለአንዱ ቪላ ቤት ለሌላው ደግሞ ሰላም ይሰጠዋል ፡፡ ብቻ ይህ ሁሉ ለምን እንደ ተደረገ ማብራሪያ አልተሰጠንም ፡፡ ምክንያቱም የታዘዝነውን መፈጸም እንጂ ሌላው ስለማይመለከተን ነው ፡፡
አዎ ሌሎች እየራባቸው ነው እኛስ እየመጸወትን ነው ? ሌሎች በወጣትነታቸው እየሞቱ ነው እኛስ ንስሐ እየገነባን ነው ? አዎ ቅኖች እየተገፉ ነው እኛስ እያስጠጋናቸው ነው ? አንዳንዴ የአፍ ወዳጅ እንጂ የተግባር ወዳጅ አይደለንም ፡፡ የራሳችንን ድርሻ ላለመወጣት እግዚአብሔርን ተጠያቂ ማድረግ እንወዳለን ፡፡
 በርግጥ እንደ ቅዱስ እንጦንስ እንደ ነቢዩ ዕንባቆም በቅን ልብ ፡- “ለምን” ልንል እንችላለን፡ እግዚአብሔር ግን የሚሰጠን ምላሽ፡-
 
·    ትኩረታችንን ራሳችን ላይ እንድናደርግ / በእኛ ላይ የበዛውን ትዕግሥቱን በማሰብ ንስሐ እንድንገባ/
 
·   ሁሉም ነገር ከእግዚአብሔር እውቀት ውጭ አይደለም ብለን በእርሱ እውቀት እንድናርፍ
 
·      የታዘዝነውን ማድረግ እንጂ ለምን እንደዚህ ሆነ ? የሚለው ጥያቄ ምንም እንደማይጠቅመን እንድንገነዘብ ነው ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ