የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

“ማን ያንከባልልልናል ?”

 “እርስ በርሳቸውም፡- ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል ? ይባባሉ ነበር” ማር. 16፡3
ክርስቶስ ሲቀበር ደስታቸው የተቀበረ ፣ ተስፋቸው የወደቀ ብዙዎች ነበሩ ። ያድነናል ያሉት ሲሞት ፣ እስራኤልን ይቤዣል ያሉት በግፈኞች እጅ ሲወድቅ የብዙዎች ልብ ንቃቃት አበጅቶ እንባና ደም ማፍሰስ ጀምሮ ነበር  ። ቅዱሳን ሴቶች ኀዘናቸውን ለመጨረሻ ጊዜ ለመግለጥና የክርስቶስን ትዝታ በልባቸው ለማኖር ወደ መቃብሩ ገስግሰዋል ። እርሱ ግን ዛሬም ሕያው ነውና የትዝታ አምላክ አይደለም ። ሉቃስን ቀለዮጳ ተስፋ ቆርጠው ፣ ዓለም ጥንትም ለደግ አትሆንም ብለው ወደ ኤማሁስ እየገቡ ነበር ። ከተስፋ መቍረጣቸው ጋር ያድሩ ዘንድ አልፈለገም ። ተስፋ መቍረጥ ለደቂቃ እንኳ ከባድ ነው ። በራሳቸው ሳይሆን በአምላካቸው ተስፋ መቍረጣቸው ደግሞ የበለጠ አስጨናቂ ነው ። እህል ቢያንቅ በውኃ ይውጡታል ፣ ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡታል ? ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡታል ? ሐዋርያትም ተስፋ ቆርጠው ማኅበሩን በትነው ወደ ጥብርያዶስ ሊጓዙ ፣ ማኅበረ ወንጌል የኅብረት ሥራ ማኅበር ሊሆን ተቃርቦ ነበር ። ትንሣኤው ግን ሴቶችን ከመቃብር ስፍራ ወደ ሕያዋን ሰፈር ያሮጠ ፣ ሉቃስና ቀለዮጳን ከኤማሁስ በምሽት ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰ ፣ ማኅበረ ሐዋርያትን ያጸና ነው ። በትንሣኤ ድል የተነሣው ተስፋ መቍረጥ ነው ። ክርስቲያን ያዝናል ፣ ስሜት አለውና ። እንዳዘነ ግን እንዳይቀር ክርስቶስ አለው ። የክርስቲያን አንድነት ይነቀነቃል ፣ እንዳይበተን መንፈስ ቅዱስ ይታደገዋል ። እንዳዘንን ፣ እንደ ተበተንን ፣ ተስፋ እንደ ቆረጥን ብንቀር ምን እንሆን ነበር ?

ሴቶች በዚያ ማለዳ ወደ መቃብሩ የገሰገሱት ቅዱስ ሥጋውን ሽቱ ቀብተው ለመሰናበት ነበር ። እርሱ ግን የሚሰናበቱት ሳይሆን አብረውት የሚኖሩት ሕያው ነው ። ሴቶችን ያስጨነቃቸው አብረዋቸው ወንዶች ስለሌሉ ድንጋዩን ማን ያንከባልልልናል ? ብለው ነው ። ከዚያ የበለጠ ነገር ሆኗል ። ሞት ድል ተነሥቷል ። ሲነሡ የፈሩት ሲደርሱ የለም ። በርቀት ሁሉም ነገር አስፈሪ ነው ፣ ሲደርሱበት ግን ቀላል ነው ። ከብዙ ዓመታት በፊት ይህች ቀን አስፈሪ ነበረች ፣ እንደርሳለን የሚል አሳብ አልነበረንም ። እግዚአብሔር ግን ያየልንን ፍርሃታችንም አይነጥቀንም ። ወንዶች የሚያንከባልሉት ድንጋይ ሲያስጨንቃቸው ነገሥታት የማያንከባልሉት ሞት ተንከባለለ ። አቅማቸውን አስበው ቢቀሩ ኑሮ ድንጋዩም ሞትም ተንከባሎ አያዩም ነበር ። አልችልም ብሎ ከመቅረት መጀመር መልካም ነው ። እስራኤል በጌሤም እያሉ ቀይ ባሕር አልተከፈለም ፣ ሲደርሱ ግን ተከፈለ ። የካህናቱ እግር ዮርዳኖስን ሲረግጥ ፈሳሹ ቆመ ። የነገው ባሕርም የሚከፈለው ዛሬ ላይ ሳይሆን ነገ ላይ ነው ። ከቀኑ በፊት አሳብና የአሳብ ፍልሚያ ነው ፣ በሰዓቱ ግን ለሰዓቱ የሚሆን ኃይልና ብርታት ይመጣል ። እነዚያ ሴቶች ድንጋዩን ሲጠብቁ ተንከባልሎ አገኙት ። ወደ መቃብሩ ዘልቀው ሽቱ መቀባትን ሲያስቡ መነሣቱን ሰሙ ። ትንሣኤ እግዚአብሔር ለልጆቹ እንግዳ ሥራ እንዳለው የሚያመለክት ነው ።
“ሰንበትም ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም የያዕቆብም እናት ማርያም ሰሎሜም መጥተው ሊቀቡት ሽቱ ገዙ ።” ሰንበት የሚያልፈው ቅዳሜ ሠርክ ላይ ነው ። ቀን ላይ እንዳይገዙ ሰንበት ያግዳቸዋል ። ሰንበቱ እንዳለፈ ግን ወዲያው በምሽት ሽቱውን ገዙ ። በሕሊናቸው የአይሁድን ቍጣ ፣ የወታደሮቹን ክልከላ አላሰቡም ። ድንጋዩን ማን ያንከባልልልናል ብለው ተጨነቁ ። ሐዋርያት ደግሞ ድንጋዩን ሳይሆን አይሁድና ወታደሮቹን ፈሩ ። አንዱ የሚበረታበት የአንዱ ድካሙ ነው ። ችግራችን ለየራስ መሆኑ ለመረዳዳት መልካም ነው ።በብዙ ያመኑ በጥቂት ነገር እጅ ይሰጣሉ ። የሚያስፈራው ቀን ያላስፈራቸው በማያስፈራው ቀን እጅ ይሰጣሉ ። ብዙ ሰው የጸሎታቸው መልስ በሚወለድበት ቀን ይሞታል ። መግደላዊት ማርያም ሰባት አጋንንት የወጣላት ሴት ናት ። ከምን እንደ ዳነች ታውቀዋለች ። የያዕቆብ እናት ማርያም የሥጋ ዘመድ ናት ። ሰሎሜም የዮሐንስ ወንጌላዊ እናት ናት ። ያዕቆብም መልእክት ጽፏል ። የሰሎሜም ልጅ በአዲስ ኪዳን አምስት መጻሕፍት የጻፈ ነው ። እነዚህ ሴቶች ማንም በማይገኝበት ሰዓት የተገኙ የክርስቶስ ወገኖች ናቸው ። ለአገር የሚሞት ፣ ለልጅ አደባባይ የሚቆም ፣ ለቤተሰቡ ዋጋ የሚከፍል ብዙ አለ ። ለክርስቶስ ቀንበር የሚሸከም ፣ የጨለማውን መንገድ በድፍረት የሚጓዝ ግን በጣም ጥቂት ነው ። እኛስ ብንሆን ለሰው የኖርነውን ያህል ለእግዚአብሔር አለመኖራችን ሐቅ አይደለም ወይ ?
ድንጋዩ የተንከባለለው ክርስቶስ እንዲነሣ አይደለም ። መላእክት መቃብሩ ባዶ መሆኑን ለማሳየት አንከባለሉት እንጂ ። እርሱ በዝግ መቃብር ተነሥቷል ። ድንግል ማርያም የመልአኩን ብሥራትና የልጇን ቃል አምናለችና ከሙታን መካከል አልፈለገችውም ። የቅርብ ቤተሰብ በሌለበት ወደ መቃብር መሄድ አልተለመደም ። በቀራንዮ የነበረችው ድንግል ማርያም በመቃብሩ ስፍራ አልነበረችም ። በልጇ መነሣት አምናለችና ። ወታደሮች ሲጠብቁ መላእክትን ያዩት ሴቶች ፣ ወታደሮችን በድን ሁነው ፣ መቃብሩ ባዶ ሁኖ ሲያዩ ልባቸው ስንጥቅ ብሎ ነበር ። ስጋት የነበረው የአይሁድ ቍጣ ፣ የወታደሮች ጥበቃ ፣ የድንጋዩ ክብደት ሁሉም የሉም ። ክርስቶስ ሲነሣ እነዚህ ሁሉ ፍርሃቶች ድል ተነሡ ። እግዚአብሔር ሲነሣ የፈራናቸው ይፈሩና ያልፈራነው እግዚአብሔርን መፍራት እንጀምራለን ። መልአኩ እግዚአብሔር ኃያል ነው ለማለት በጎበዝ ምሳሌ ተገለጠላቸው ። እግዚአብሔር ወልድ በሥጋ ተሰውሮ እንደ ተገለጠ ፣ መልአኩም በመልአክ አርአያው ሳይሆን በጎበዝ ምሳሌ ተገለጠ ። ሰው የሚችለው ጥቂት ነገር ነው ፣ ሰውን ይቅር በለኝ ስንለው እንኳ የበደልነውን ዝርዝር ነገር መንገር የለብንም ። ምክንያቱም የሰው አቅም ያለፈውንም ጉዳት ለመሸከም ደካማ ነውና ።የመጀመሪያውን ብሥራት ለድንግል ማርያም የነገረ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነበረ ፣ አሁንም ትንሣኤውን ለሴቶች መልአክ አበሰረ ። መልአክ ቢወድቅ አምላክ መልአከ ሁኖ አላዳነውም ፣ ሰው ቢወድቅ ግን አምላክ ሰው ሁኖ አዳነ ። መላእክት ግን በዚህ ቅር አላላቸውም ። ፈቃዱ ፈቃዳቸው ፣ ፍቅሩ ፍቅራቸው ነውና ይወዱናል ። መልአኩም የክርስቶስን መነሣት አበሰረ ።
አትደንግጡ ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ ፤ ተነሥቶአል ፥ በዚህ የለም ፤  እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ ። ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም፦ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው።”
የመልአኩ ክስተት ፣ የድንጋዩ መንከባለል ፣ የመቃብሩ ባዶ መሆን ያስደነግጣል ።ያልጠበቁት ደስታም ከጠበቁት ኀዘን በላይ ክው ያደርጋል ። መቃብሩ ባዶ መሆኑን በእምነት ተቀበሉ አላለም ፣ በዓይን እዩ አለ እንጂ ። እኛ ግን ዛሬ እናምናለን ፣ ነገ እናያለን ። ለጴጥሮስም ንገሩ አለ ። ለካደው ሐዋርያ መልአኩ ከሥላሴ መልእክት ይዞ መጣ ። ጴጥሮስ በሰማይ ይታወቃል ። መላእክት በውድቀቱ አዝነዋል ። ሰይጣን ደስ ብሎት ነበረ ። አሁንም የሰይጣን ማፈር ለሴቶች ተገለጠ ። ንስሐ እንዲህ አድርጋ ሰይጣንን ጉድ ትሠራዋለችና ጠላት አይወዳትም ። ጌታችን በብሥራቱና በትንሣኤ ቅድሚያ የሰጠው ለሴቶች ነው ። ሔዋን የስህተት በር በመሆኗ እጅግ አዝናለችና ። ደም የሚመልስ ልጅ ክርስቶስን ወለደች ። በአንድ ሌሊት ሦስት ጊዜ ለካደ ጴጥሮስ ፣ ሰባት አጋንንት ለነበሩባት መግደላዊት ማርያም ትንሣኤ ተገለጠ ። እግዚአብሔር ንስሐን የሚያከብር ፣ ወድቀው በተነሡ የሚደሰት አምላክ ነው ። ጠላቶቹ ሥጋውን ገደሉ ፣ ፍቅሩን ግን መግደል አልቻሉም ። የማይሞተው ፍቅሩ ጴጥሮስን እንደ ገና አሰበው ።
ወደ ክርስቶስ ለመገስገስ ስናስብ ብዙ ድንጋዮች ከፊት ለፊታችን ይታዩናል ። እንዴት እንደሚነሡ ባይገባንም ጉዞውን ግን ማቆም የለብንም ። የአምላክ ዝምታ የሌለ ያህል ይመስላል ። እግዚአብሔር ደክሞ ፣ ሰው የበረታ ይመስላል ። ግፍ ዛሬም ቀጥሏል ። ምስኪኖች ይበልጥ እየደኸዩ ፣ ግፈኞች እየናጠጡ ነው ። በእኛና በክርስቶስ መካከል ድንጋይ ሁነው የጋረዱን ፣ ጸሎታችንን ከደመና በታች ያስቀሩብን እልከኝነቶች ፣ ራስ ወዳድነቶች ፣ እኔ ብቻ ያልኩት ይሁን ባይነቶች ፣ ለጎረቤት መቃብር የመቆፈር ሴራዎች ፣ አታላይነቶች ናቸው ። በእጃችን ሽቱ ይዘናል ፣ ለሕያውነቱ ሳይሆን ለሞቱ ልንቀባው ፈልገናል ። እግዚአብሔርን የትላንት አምላክ ብቻ ማድረግ ያንን ሽቱ ያስታውሳል ። እግዚአብሔር ድሮ ይሰማኝ ነበር እያሉ መኖር ያን ሽቱ ይገልጣል ። ብቻ ብናመነታም መቆም የለብንም ። ስንደርስ ወታደሮች ወድቀው መልአክ ቆሞ ፣ ድንጋዩ ተንከባሎ በላዩ የእግዚአብሔር የሠራዊት አለቃ ተቀምጦ እናገኘዋለን ።
ለዛሬው ዘመን፡- በሽታ ትልቅ ቋጥኝ ሁኖ እያስጨነቀ ፣ የልጆች ጠባይና ዱርዬነት ወላጆችን ፈሪ እያደረገ ፣ በትዳር ውስጥ ቋንቋው መደባለቁ እያታከተ ይገኛል ። ለሁሉም ጥያቄዎች መልሳችን ጭንቀት ብቻ መሆኑ ፣ የማንሰማውን ምክር ስንጠይቅ መዋላችን ፣ ለምሬት እንጂ ለቅድስና ምንም ጊዜ ማጣታችን ፣ ብሉ ተብለን ለመንፈሳዊ ነገር መለመናችን ትንሣኤን እንዳናይ እያደረገን ነው ። እኛ ድንጋዩ ያሳስበናል ፣ እግዚአብሔርን የሚያሳስበው ድንጋዩ ልባችን ነው ። ሰበር እንበል ። ትንሣኤ ዛሬም አለ ።
ጸሎት
ክብርህ የሚያበራ ፣ ችሎታህ የማይለካ ጌታ ፣ አንተ ካስጨነቀን ነገር በላይ ነህ ። እኛ ይህን አልፈን ወደ ሩጫችን ለመግባት እናስባለን ። እግዚአብሔር ምን እያለኝ ነው ብለን ከልባችን ለመጻፍ እንሰንፋለን ። አንተ ግን የሞተውን ውስጣችንን አስነሣልን ። ስንጓዝ እግራችንን የሚያሳጥሩትን ፣ አንተን ስናስብ የሚጋርዱንን ቋጥኞች በትንሣኤህ ገላግለን ። አመንሁ እያልን እንዳንፈርስ ፣ ቆምሁ እያልን እንዳንወድቅ ለዘላለም ደግፈን ። በሚያበራው ኃይልህ አሜን ።
የመስቀሉ ገጽ 6
ሚያዝያ 14 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ