የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምን ልታዩ መጣችሁ? (ማቴ 11÷8)

         የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ዓርብ ሰኔ 19/2007 ዓ.ም.
በነገሥታት የሚሠራ መንፈስ በተራው ሰው ከሚሠራው መንፈስ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ የነገሥታት መንፈስ ስንጠጋቸው ስህተታተቸውን እንዳያዩ አመስግኑ፣ አመስግኑ የሚል ሲሆን ስንርቃቸው ደግሞ እንዳይራሩ ተራገሙ፣ ተራገሙ የሚል ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት መቆም የሚችሉ ብቻ በሰው ፊት መቆም ይችላሉ፡፡ ለዚህ ነው ዮሐንስ መጥምቅ ንጉሡ ሄሮድስን በግልጽ በመቃወም ወደ ወኅኒ የወረደው፡፡ ሌሎች ነገሥታትን የሚቃወሙት በሕዝብ ድጋፍ እነርሱ ለመንገሥ ነው፡፡ ዮሐንስ ግን የእግዚአብሔርን ክብርና የእውነትን ልዕልና በማሰብ ብቻ ይገሥጽ ነበር፡፡ እውነትን መናገር ብቻ አይበቃም፣ እውነት ለምታስከፍለው ዋጋም ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
መልካም ሰው ነኝ፣ ስለዚህ ማንም ሊነካኝ አይችልም ማለት አንችልም፡፡ መልካምነትም በክፉዎች ያስከስሳልና፡፡ የአይሁድ ካህናት ኢየሱስ ክርሰቶስን ለሞት አሳልፈው የሰጡት የእርሱ ንጹሕ አኗኗር ራሳቸውን ያለማቋረጥ ያሳያቸው ስለነበር ነው፡፡
ሰዎች በእኛ ላይ የሚነሣሡት ያለምክንያትም ነውና ከሰዎች ነቀፋ ነጻ ለመሆን የምናደርገው ጥረት ሙሉ በሙሉ ላይሳካ ይችላል፡፡ ዋናው ግን በሕሊናና በእግዚአብሔር ፊት ነጻ መሆን ነው፡፡ በአደባባይ በነጻነት የሚያመላልሰው በቂ የመንግሥት ጥበቃ ሳይሆን ነጻ ሕሊና ነው፡፡ ሰዎች ሁሉ ከሚያወድሱን ሕሊና ነጻ ናችሁ ቢለን ይሻላል፡፡

ብዙዎችን ያስተማሩ ለእነርሱ የፍቅር አስተማሪ የላቸውም፤ ብዙዎችን የመከሩ ያለ አጽናኝ ብቻቸውን ተገርፈዋል፡፡ ብዙዎችን የመሩ ከመንገዱ ሲወጡ ገፍታሪ እንጂ መላሽ የላቸውም፡፡ ያበሏቸው ሰዎች ቀድመው ያሳድዷቸዋል፡፡ ክርስትና ከሚያቀዳጀን ድል አንዱ በማንም ውድቀት አለመደነቅ ነው፡፡ በክርስቶስ ዓይን ስናይ ሰዎች ሁሉ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እናስባለን፤፤ ‹‹ትንንሾች ግን በትልልቆች ውድቀት ደስ ይላቸዋል››፡፡ ጌታ ኢየሱስን ያጠመቀ፣ ብዙዎችን በንስሓ የመለሰ፣ ብዙ ተከታዮች ያሉት፣ ስለእውነት ወደ ወኅኒ የወረደ፣ ዮሐንስ አሁን እምነቱ ደከመና ‹‹የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?›› (ማቴ.11÷3) አለው፡፡ ስላጠመቀው ኢየሱስ እንግዳ ሆነ፡፡ ድካሜን አውቀዋለሁና ‹‹ጌታ ሆይ÷ ቀምሼህ እንዳልቀመሰ፣ አውቄህ እንዳላወቀህ እንዳልሆን እርዳኝ›› እላለሁ፡፡ ‹‹ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፡ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፣ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፣ ሙታንም ይነሣሉ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል በእኔም የማይሰናከል ሁሉ ብፁዕ ነው፡፡ (ማቴ.11÷4-6)፡፡

ጌታ እነዚህ ተአምራቶች ለዮሐንስ ንገሩት ያለው እንዲደነቅ ወይም እውቅና እንዲሰጥ አልነበረም፡፡ ከእነዚህ እንደ አንዱ ቢሰማው እንኳ መፍትሔ እንዳለው ሊገልጥለት ነው፡፡ ቀጣዩን ደቂቃ ማሰብ ባለመቻል መሳሳት እንደ እኔ ልምዳቸው ለሆኑት ዕውሮች፣ ክርስቶስ ማየትን ይሰጣል፡፡ ማሰብ እንጂ ማድረግ የማይሆንላቸውን የልብ አንካሶች መራመድን ያድላቸዋል፡፡ ምንም የሚታይ በጎ ነገር የለንም የሚሉትን ራስን ኮናኞችን መልክ ያድላቸዋል፡፡ እውነት የማይሰብራቸውን ደንዳኖች በቀላሉ የሚነካ የሥጋ ልብ ይሠጣቸዋል፡፡ በሙታን ዓለም ገለልተኛ ሆነው ለሚኖሩት መቀላቀልን ያጎናጽፋቸዋል፡፡ ለድሆችም ዳቦ ለዘለቄታው የሚስገኘውን የወንጌል መፈታት ያድላቸዋል፡፡ ዛሬም በእምነታቸው ለደከሙት ይህንን እናውራላቸው፡፡ ለደከመ አንዲት ቃል ሕይወቱ ነች፡፡ በጨለማ ያሉ ጭላንጭል ይፈልጋሉ፡፡
ባሕላችን ይሁን አዳማዊ ውድቀታችን ለሰዎች ለራሳቸው ስህተታቸውን ከመንገር ማማት ይቀለናል፡፡ የሚከብደው ግን የቱ ነው? ጉዳዩን ለባለቤቱ ለራሱ መንገር ወይስ ለማይመለከታቸው በመንገር የሌሎችን ሕሊና ማርከስ? ለሌሎች የሰውየውን መልካምነት ማውራት ተገቢ ከሆነ ስህተቱን ማውራት ግን ለምን ተከለከለ? ስንል ሐሜት የሌሎችን ኃጢአት መናዘዝ ስለሆነ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ የዮሐንስን እምነት ለማገዝ ከላከ በኋላ ለቀሩት ሕዝቦቹ ትልቅ ሰው መሆኑን ተናገረ፡፡ ኢየሱስ አጉልቶ የሚያየው ትልቁን በደል ሳይሆን ትንሹን መልካምነት ነው፡፡ ስህተቱን ለባለቤቱ ሲነግርም ምን ተሰማው ብሎ አያዳምጥም፡፡
ሕዝቡንም ‹‹ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ?›በማለት ጠየቃቸው (ማቴ.11÷7)፡፡ ኑሮን ልከኛ የሚደርገው የወጡበት መንፈስ ነው፡፡ መጨረሻውን የሚወስነው መጨረሻው ሳይሆን መነሻው ነው፡፡ መነሻ ይታያል፡፡ እኛስ ምን ልናይ ወጥተናል? የአደባባይ ሰባኪዎችን መፈለግስ ሕይወትን ከጥማት ይፈውስ ይሆን? ወደ ቤተ ክርስቲያን የመጣነው ምን ልናይ ነው? እግዚአብሔርን የሚያይ አይሰናከልም፡፡ ደስተኛም ይሆናል፡፡ እባክህ አድለን!

 

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ