“ሥራህ ድንቅ ነው፥ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።” (መዝ ፻፴፱ : ፲፬)
የዓለም የሠራተኞች ቀን በታላቅ ድምቀት ይከበራል። የሰው ልጆችን የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ኑሮአቸውን በሥራ ላይ መመሥረታቸው ነው። ሥራ ሰው ሲፈጠር የታቀደለት ዓላማ ነው። ሥራ በረከት ነው ። እግዚአብሔር የእጅን ሥራ ይባርካል። በምኞት የሚኖሩትን ሳይሆን የሚሠሩትን ይወዳል። ሃይማኖትም እንቅስቃሴ እንጂ ተራ ተስፈኛነት አይደለም። በዚህ ዓለም ላይ የሚከፈልና የማይከፈለው ሥራ አለ። ለራሳችን ፣ ለቤተሰባችን የምናከናውነው የማይከፈል ፣ ነገር ግን እርካታ ያለው ሥራ አለ። ብዙ ድካም ቢኖረውም ደከመኝ አንልበትም። በፍቅር የሚሠሩት ሥራ ጉልበት ይጨምራል። የሚከፈል ሥራ ደግሞ በምድር ለሥጋችን፣ በሰማይ ለነፍሳችን የምናከናውነው ግብር ነው።
የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክ ተፈጠረ ማለት ሠራተኛ ነው ማለት ነው። እግዚአብሔር ከሚጠራበት ስም አንዱ “ሠሪው ጌታ” የሚል ነው፡፡ እኛ የሠሪው ልጆች ነን። ሐዋርያው ጳውሎስም “ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና” ይላል። የእግዚአብሔር የሥራ ባልደረቦች ነን። ሠራተኛው እርሱ ነው፣ ሥራውም የእርሱ ነው። ለሠራተኞችም ዋጋ የሚሰጥ እርሱ ነው። ሠራተኛው እግዚአብሔር ሠራተኞችን ይወዳል። እንደ እርሱ ጌታ፣ እንደ እርሱ ሠራተኛ የለም። ጌትነት ማለት ሠራተኛነት ነውና ወገኔ ተነሣ !
ሰዎች የተለመደ ሥራቸውን በየዕለቱ ያከናውናሉ። አስደናቂ ሥራን ግን በሕይወት ዘመናቸው አንድ ጊዜ እንኳ ላይፈጽሙ ይችላሉ። እግዚአብሔር ግን በዘወትር ሥራው ድንቅ ነው ። ሥራው የማይኮረጅ ነው። ሥራው እንከን የማይወጣለት ነው። ሥራው ጸንቶ የሚኖር ነው። ሥራው ምስጋናን የሚያመጣ ነው። እግዚአብሔር ሥራውን በድንቅ ይፈጽማል። በአብዛኛው የእኛ አገር ሥራ የአፈጻጸም ችግር አለበት። ወጪው ያው ቢሆንም ማማር ግን የለውም። እግዚአብሔር ግን ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ይሠራዋል። ነገርን ሁሉ ስንል ሙላትንም ጉድለትንም፣ ችግርንም ደስታንም ለመልካም ያደርገዋል። እግዚአብሔር ለሥራው የጊዜ ሰሌዳ አለው ። የብዙዎቻችን ማጉረምረም ነገሮች ሁሉ በእኛ ጊዜ ለምን አልሆኑም? የሚል ነው። እግዚአብሔር ይሠራል፣ በራሱ ጊዜ ይሠራል።
ያልፈረደ በሚመስለን ሰዓት እንኳ በድንቅ እየፈረደ ነው። እርሱ ልብንና መንፈስን እየወጋጋ የሚቀጣ ነው። አዎ ሥራ ድንቅ ነው። ባናውቀው፣ ባይገባን፣ ባናስተውለው እንጂ እርሱ ሥራ ያቆመበት ሰከንድና የሰከንድ ሽርፍራፊ የለችም። ዓለምን በውበት የፈጠረ፣ ዓለምን በጥበብ እየመራ ነው። እርሱ ሲሠራ ከፍታው ዝቅተኞች ቤት ለመድረስ አይከለክለውም ። ሥራው ድንቅ ነውና ከሞተ የእህል ዘር ፍሬን ይሰጣል። ፈሳሽን ቋጥሮ በማኅፀን ጽንስ ያስቀምጣል። አንዱን በልደት ሲያመጣ ሌላውን በሞት ይወስደዋል። ብዙ በማይወለድበት አገር የአረጋውያን ዕድሜ ይረዝማል። ብዙ የሚወልዱት በብዛት ይሞታሉ። ለእኛ የማይገባን ብዙ ሥራ አሉ። እኛ የኮካ ኮላን ምሥጢር እንኳ አላወቅንም። ሥራው ምሥጢር ቢሆንብን አይደንቅም። የሚያጽናናን አንድ ነገር አለ። እግዚአብሔር ለእኛ መልካም ነው።
የሥራውን ድንቅነት ነፍሳችን ማወቅ አለባት። በማወቅ ውስጥ እምነት፣ ፍቅር፣ ምስጋና፣ መገዛት ይጨምራል። እግዚአብሔር ሲያጎርሰን ልናውቅ ይገባል። ላልነቃ ሰው ማጉረስ ሰውዬውን መግደል ያመጣል። ሳይነቁ የጎረሱ ሞተዋል። ነፍሳችን ድንቅ ሥራውን ማወቅ አለባት። ፀሐይ ስትወጣና ስትጠልቅ ውበቷን ማድነቅ፣ እግዚአብሔርን ማመስገን ያልቻለ ምንም ነገር ሊገነዘብ አይችልም።
ከእነ እገሌ መሞት የእኛ መኖር ይደንቃል። ለማረፍ ሌሊቱን፣ ለመሠማራት ቀኑን ሲሰጠን ድንቅ ነው። የደመቀው ከተማ ማታ ላይ ፀጥ ይላል። ያ ሁሉ ወገን የት ገባ ያሰኛል? ሰብሳቢው እግዚአብሔር ነው። እንኳን ነግቶ ፣ እንኳ መሽቶ አልቀረ! እግዚአብሔርን ማወቃችን፣ በቤቱ መኖራችን፣ ቃሉን መናፈቃችን ይህ ሁሉ የእርሱ ድንቅነት ነው። የእርሱን ድንቅ ሥራ ተሸክመን እንዞራለን። እንቅልፍ ምንድነው? ስለ እንቅልፍ እርሱን ማድነቅ አይገባም ወይ? ልባችን ከተፀነስንበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ትመታለች። ግን አይተናትም፣ መርተናትም አናውቅም። ለልብ ዕረፍት ፣ ለጆሮ ጣዕም ፣ ለዓይን ውበት ፣ ለአፍንጫ መዓዛ ያለው የእግዚአብሔር ሥራ ድንቅ ነው።
መዝሙራችንም:-
እግዚአብሔርን አመስግኑት
ሥራው ግሩም ድንቅ ነው በሉት
ሰማይን ያለ ምሰሶ
ምድርንም ያለ መሠረት
ያጸናው እርሱ ነው
ሥራህ ድንቅ ነው በሉት
የባሕርን ጥልቀት የመጠነ
ዳርቻዋን የወሰነ
እግዚአብሔርን አመስግኑት
ሥራህ ድንቅ ነው በሉት
ማዕበል ነፋስን የሚገሥጽ
ፍጥረቱ ለስሙ የሚታዘዝ
ትጉህ እረኛ ድካም የሌለበት
እግዚአብሔርን ሥራህ ድንቅ ነው በሉት
ንጹሐ ባሕርይ ነው ሁሉን የሚገዛ
የነገሥታት ንጉሥ አልፋና ኦሜጋ
ዘለዓለም እርሱ የማይለወጥ
እግዚአብሔርን ሥራህ ድንቅ ነው በሉት
ጥበብን የሚገልጥ ጥበበኛ
ፍርድን የሚያደርግ እውነተኛ ዳኛ
እንደ እርሱ ያለ ከቶ አይገኝም
እግዚአብሔር ግሩም ነው ዘለዓለም
አሜን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 15 ቀን 2017 ዓ.ም