“በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ ።” ኤፌ. 4፡3።
ሰላም ማሰሪያ ፣ አንድነት ጥበቃ ይፈልጋል ። ሰላም የስብሳባ ውሳኔ ፣ የአንድ ወገን ጥረት ፣ የመልካም ምኞት መግለጫ አይደለችም ። ሰላም ታስራ የቆመች ናት ። ማሰሪያው ሲላላ ብዙ መናጋት ይከሰታል ። ሕፃናቱ ፣ ወጣቶቹ ፣ ጎልማሶቹ ፣ ሽማግሌዎቹ የተሳሰሩበት ገመድ አለ ። ሕፃናቱ አብረው አፈር ፈጭተው ፣ ቡሄ ጨፍረው ማደጋቸው እንዲተሳሰሩ ያደርጋል ። ወጣቶች ችቦ ለቅመው ፣ ኳስ ተጫውተው አብረው መኖራቸው ሰላምን እንዳትሄድ አስሮ ይይዛታል ። ጎልማሶቹ ማኅበራቸውን ማጠናከራቸው ፣ ስለ ሀገር ማሰባቸው ሰላምን ይጠብቃታል ። ሽማግሌዎቹ ማስታረቃቸው ፣ መገሠጻቸው ለሰላም ማሰሪያ ነው ። ሕፃናቱን ከተፈጥሮ ለይተን አፈር እንዳይፈጩ ስንከለክላቸው በሽታ የማይችሉ ፣ የሚኖሩበትን ዓለም በጭምብል የሚጨብጡ ሆኑ ። እርስ በርሳቸው እንዳይጫወቱ ብለን የሰጠናቸው መጫወቻ ዕቃ ወዳድ እንዲሆኑ ፣ ለሰው ፍቅር የሌላቸው ፣ ዓይናቸው ለረጅም ሰዓት ቴሌቪዥንና ስልክ ላይ በማፍጠጥ ታማሚ እንዲሆን አደረግን ። ዘመድ እንዳይመጣ በር በመቆለፋችን ሰው የማይለምዱ ፣ ብቸኝነት የሚያጠቃቸው ሕፃናትን አተረፍን ። ሰላም በብዙ ማሰሪያ የተያዘች ናት ። ሰንበቴው ፣ ማኅበሩ ፣ በዓላቱ ፣ መስቀሉ ፣ ጥምቀቱ ሰላም የታሰረችበት ገመዶች ናቸው ። ልሂድ ስትል ተብትበው ስለያዙአት ሰላም ቆይታለች ። እነዚህ ገመዶች መላላት ሲጀምሩ ደግሞ ሰላም እየጠፋ መጣ ።
ሰላም ገመድ ትፈልጋለች ፣ ሰላም ራስዋም ገመድ ናት ። ሰላም በብዙ ማሰሪያዎች ተይዛ ያለች ናት ። ብዙ የሚፈልጋት ስላለ ሰላም ልሂድ እያለች ታስቸግራለችና አስረን ማቆየት ያስፈልገናል ። አብረን ለመኖር ዋጋ መክፈል ፣ ማኅበራዊነት እንዲጸና የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ፣ በሰርግም በልቅሶም መተባበር ያስፈልገናል ። አንደኛውን ስናመልጥ አንደኛው ገመድ እንዲይዘን አድርገን ሰላምን መተብተብ አለብን ። ሰላም ራስዋም ገመድ ናት ። አስራ ትይዘናለች ። እንዳንለያይ ፣ እንዳንበታተን ፣ እንዳንወድቅ ትይዘናለች ።
“የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” ይላል ። አንድነት ጥበቃ ይፈልጋል ። ጥበቃውም ትጋት ያለው መሆን አለበት ። ብዙ ዓይነት አንድነት አለና “የመንፈስን አንድነት” አለ ። የሥጋ አንድነት አለ ፣ ዘረኝነት ፣ የሀብት እኩያነት ያጠላበት አንድነት አለ ። የአእምሮ አንድነትም አለ ፣ በሰው ቍስል እንጨት የሚሰድ ፣ ድሀ ከምድር መወገድ አለበት ብሎ የሚያስብ ፣ ምድርን የጥቂቶች ብቻ ለማድረግ የሚመክር አንድነት አለ ። ይህ አንድነት ቢፈርስ የተሻለ ነው ። ሐዋርያው በትጋት ጠብቁ ያለው የመንፈስን አንድነት ነው ። ጥበቃና ትጋትን እስቲ እናስባቸው ። ጥበቃ በቀንና በሌሊት የማያቋርጥ ነው ። አንድነትም ያለማቋረጥ ልንጠብቀው ይገባል ። አብረን ሆነን መናቆራችን የሚያስከፍለን ዋጋ ቢኖርም መለያየት ደግሞ ከዚህ በላይ ዋጋ ያስከፍለናል ። በመለያየት ውስጥ መጠፋፋት ብቻ ይኖራል ። በመለያየት ውስጥ ማነስን እንወልዳለን ። ኃይላችን ይባክናል ። በአንድነት ውስጥ በጥቂት መሣሪያ ስናሸንፍ ፣ በመለያየት ውስጥ ግን ብዙ ቢኖረንም ድል የለንም ። ጥበቃ የቀኑን ፀሐይ ፣ የሌሊቱን ቍር የሚታገሥ ነው ። አንድነትንም ከስሜት እሳት ፣ ዘመናዊነት ከሚያመጣብን ቀዝቃዛነት በላይ ልንጠብቃት ይገባል ። አንድ የሆንነው በእግዚአብሔር እንጂ በፍላጎታችን አይደለም ። የእግዚአብሔርን ማሰሪያ እንቍረጥ ስንል እንጎዳለን ። አንድነት ጥበቃ ያስፈለጋት የቀን ወራሪ ፣ የሌሊት ሰባሪ ስላለባት ነው ።
የአንድነት ምልክቶቻችንን አጥብቀን መያዝና ለዚያም መገዛት ያስፈልገናል ። የሚጠብቁ በትጋት ግን የማይጠብቁ ንብረት ያዘርፋሉ ። ዘረፋ ሲፈጸም የሰረቀው ብቻ ሳይሆን የተዘናጋው ዘበኛም ይጠየቃሉ ። ሌባ መዝረፍ እንደ ሥራው ነው ። ሌባ እንዳይመጣ ማድረግ አንችልም ። ተግተን ከጠበቅን ግን አንድነታችንን ማትረፍ እንችላለን ። አብረው የነበሩ ሕዝቦች ዛሬ የተለያዩትን ብናስብ ምንም ትርፍ አላገኙም ። በመለያየት ውስጥ የሚጠቀሙት የሚጠሉን እንጂ የሚወዱን አይደሉም ። በመለያየት ውስጥ ግዛታችን ያንሳል ። አንድ የሆኑ ሕዝቦችን ለሁለት ከፍለን እንደ ተነፋፈቁ ሳይገናኙ እንዲሞቱ እናደርጋለን ። አንደኛው ለአንደኛው ስጋት ይሆናል ። ሰሜን ኮሪያ በጦር መሣሪያ ስታይል ፣ ደቡብ ኮሪያ ደግሞ በኢኮኖሚ አይላለች ። አንዳቸው ለአንዳቸው ግን ስጋት ናቸው ። አንድ የነበሩ ሕዝቦች ስለሚተዋወቁ አይከባበሩም ። የሚያነሱት ጦርነትም የሞኝነት ሁኖ ብዙዎችን ያስፈጃል ። በመለያየት ውስጥ ልጆቻችንን ጠላትህ እገሌ ነው በማለት ስለምናሳድጋቸው አእምሮአቸው ሰላም አይኖረውም ።
ሰላም ከሄደች በኋላ መመለስ ከባድ ነው ። ጤና ሳለ ቀላል ፣ ከሄደ በኋላ ግን ብዙ ሕክምና አይተን የማናገኘው ነው ። አንድነትም ብዙ ሰራቂ አለበትና በትጋት ልንጠብቀው ይገባል ። እኛ ያልጠበቅነውን አንድነትም ማንም ሊጠብቀው አይችልም ። ማሰር ፣ መጠበቅ ፣ መትጋት የሚሉት ቃላት ሰላምና አንድነትን ለሚፈልጉ ሁሉ ወሳኝ ናቸው ። ቤተ ክርስቲያን አንድነትዋን ባጸናች ዘመን ቄሣሮች ሁሉ ይፈሯት ነበር ። አንድነትዋ ሲናጋ ግን እየተደፈረች መጣች ። ምዕራብና ምሥራቅ ተብላ በተከፈለች ጊዜ ሌሎች ሃይማኖቶች ተነሡ ። በአንድነት ለ400 ዓመታት የኖረች ቤተ ክርስቲያን 1600 ዓመታት ደግሞ በመለያየትና በመነቃቀፍ ትኖራለች ። ከተለያየን በኋላ አንድ ለመሆን ጊዜ ይፈጃል ። በቤተ ክርስቲያን መከፈል ያላመነውን ወደ እምነት የማምጣት ተልእኮን ዘንግተናል ። ያለው አገልግሎት በግ የመሰራረቅ እንጂ ፍየሎችን በግ የማድረግ አይደለም ።
ሰላም ማጣት ያስንቀናል ፣ አንድነት ማጣትም ያሳንሰናልና እንንቃ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም.