መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ስሞት አልቅስልኝ

የትምህርቱ ርዕስ | ስሞት አልቅስልኝ

ስሞት አልቅስልኝ ብለኸኝ የነበር ፣
አደግኸው ምነው ዋዛውን ቁም ነገር ።

“መኖር ሞትን ሳይፈሩት ሳይመኙትም ነው” ይባላል ። “ዘጠኝ ሞት ቢመጣ አንዱን ግባ በሉት” ይባላል ። ሰው የሚሞተው አንድ ሞት መሆኑን ለመግለጥ ነው ። ስለዚህ ፈሪ መሆን የለበትም ። ሞትንም መመኘት አይገባም ፣ አኑረህ አሠራኝ እንጂ ውሰደኝ አይባልም ። ምንም ቢለምኑት ሞት አይቀርምና ። መከራ ሲበዛ ግን ሞትን ተመኝተውት እርሱም ይኮራል ። የሰው ሕይወት ሁለት ነው ። በሁለቱ ሕይወት መካከል ሞት ድንበር ነው ። ሰው አንደኛውን ሕይወት ጨርሶ ወደ ሁለተኛው ሲሸጋገር ድልድዩ ሞት ነው ። ሁለተኛው ሕይወት ዘላለማዊና አስደሳች ነው ። የዚህ ዓለም መራራነት ያንን ዓለም እንድንናፍቅ ያደርገናል ። ብዙ ሰዎች ከምናውቀውና ከማናውቀው ችግራቸው ጋር እየታገሉ ነው ። ለማን ላውራው ? ማንስ ይረዳኛል/ይገነዘብልኛል ? ብለው ከራሳቸው ጋር ጉባዔ የተቀመጡ ፣ ስብሰባ የሚያካሂዱ ፣ ብቻቸውን የሚያወሩ ፣ በአሳብ ባሕር የሰጠሙ ፣ ከሰው መካከል ተቀምጠው ቀልባቸው የከዳቸው ፣ ለራሳቸው እያለቀሱ የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው ።

በዓለም ላይ የደጎች ዕድሜ ማጠር በጣም አሳዛኝ ነው ። ደጎች አይበረክቱም ፣ እኛ እንደምንፈልጋቸው ሰማይም ይፈልጋቸዋል ። ደጎች በቶሎ የሚሄዱት በሚያዩትና በሚሰሙት ክፉ ነገር የበለጠ እንዳያዝኑ ፣ ደግነታቸውን በክፉው ዓለም ተንኳሽነት እንዳይከስሩ ነው ። እግዚአብሔር ክፉዎችን ለመቅጣት የሚቸገረው የደጎችን ልብ ላለማሳዘን ነው ። የደጎች መነሣት በክፉዎች ላይ መከራው ያለ ከልካይ እንዲዘንብ ያደርገዋል ።

ብዙ መልካም ሰዎች ዛሬ ላይ የሉም ። ከቆሙት ደጎች በመቃብር ውስጥ ያሉት ደጎች ይበዛሉ ። ታዲያ አንዳንድ ቀና ሰዎች ሞተው እንኳ እንደምናስባቸውና እንደምንወዳቸው እርግጠኞች ናቸው ። ስሞት አልቅስልኝ ይላሉ ። በርግጥ ክፉዎች እየበዙ ስለሆነ የሞቱትን ደጎች በየቀኑ ከማሰብ ውጭ አማራጭ የለንም ። ስሞት አደራ እያሉ የሚነግሩን ሰዎች ምን እየተሰማቸው እንደሆነ መመርመር አለብን ። ስሞት አደራ የሚሉን ሰዎች በእኛ ፍቅር ከሞት በኋላም እምነት አላቸውና አክባሪዎቻችን ናቸው ። ስሞት አደራ የሚሉንን ሰዎች ዝም ብለህ ነው ፣ ሟርተኛ ነህ ፣ ኧረ አትሞትም እያልናቸው ብዙዎች ሞተዋል ። እነርሱ ሄደው ዝናቸውና ፎቶአቸው ብቻ ቀርቷል ።

ብዙ ወጣቶች ከነ ሕልማቸው ተቀብረዋል ። እንደ ጠዋት ጤዛ ሳያረፍዱ ረግፈዋል ። ለዚህች ዕድሜ ከኖሩት በላይ ዋጋ ከፍለዋል ። እነዚህን ሳስብ በጣም አዝናለሁ ። ሰውን ላለማስቀየም ይጠነቀቁ የነበሩ እነዚያ ጉብሎች ዛሬ ስልካቸው አይሠራም ። እነዚያ ተቀባዮቻችን በራቸው ተዘግቷል ። የምንወደውን ሰፈራቸውን ዛሬ ጉዳይ ቢገጥመን እንኳ ለመሄድ ጠልተነዋል ። ውዶቻችን የሉምና ። ልቅሶቸውን በሳቃቸው የሸፈኑ ፣ ብሶታቸውን “ደኅና ነኝ” በሚል ድምፅ የሰወሩ ፣ ስቃያቸውን የሌሎችን ሕመም በማሰብ የረሱ እነዚያ ተሳቃቂዎች ዛሬ የሉም ። ታዲያ አያያዛቸውን ያውቁት ኖሮ ፈገግ እያሉ ስሞት እንዲህ ብለህ አልቅስልኝ ብለውን ነበር ። ቀልዱ የምር ሁኖ ዛሬ እናዝናለን ። ከሚለፈልፉ ፣ ከሚያለቅሱ ሰዎች በላይ የሚስቁትን ሰዎች ማገዝ አለብን ። ሳይታወቅላቸው ፣ መታመማቸው ሳይሰማ ሞታቸውን የምንሰማው እነዚያን ሳቂታዎች ዛሬ መፈለግ አለብን ። የሚስቁት ደስ ብሏቸው ሳይሆን እኛ እንዳይከፋን ተጨንቀው ነው ።

ሰው ጠብቀኝ የማይባል ከእኛ የበለጠ ቀጠሮ ያለው ነው ። ሰው ምድር እያለመ ውሎውን ሰማይ ሊያደርገው የሚችል ነው ። ሰው ስለ መተኛቱ እንጂ ስለ መንቃቱ ዋስትና የለውም ፣ ስለ መውጣቱ እንጂ ስለ መመለሱ ከእጁ የወጣ ጉዳይ ነው ። ብቻ እውነተኛ ፍቅር የሚያሳዩን ፣ በምን ደስ እንደሚያሰኙን የሚጨነቁትን እነርሱን ተቀዳሚ ጉዳያችን እናድርጋቸው ። የመኖር ትርፉ መዋደድ ብቻ ነው ። ወዳጅን ሳያዳምጡት እንደ ማጣት ያለ የእሳት ጅራፍ በምድር ላይ የለም ። ባለፉት ወገኖቻችን ላይ የሠራነውን ስህተት እንዳንደግመው ካሉት ጋር እንስማማ ።

አልቃሽ ፣ ንስሐ አባት ፣ የሚያምኑት ወዳጅ “ስሞት አደራ” ይባላሉ ። ንስሐ አባትን ቀብሬን ያስተካክሉልኝ ይባላል ። የሚያምኑትን ወዳጅ የልጆቼን ነገር አደራ ይሉታል ። አልቃሽንም እንዲህ ብለህ አልቅስልኝ የሚል ልማድ አለን ። መቼም ሲሞት የሚያስለቅሰን በቁሙ ያስደሰተን ሰው ነው ፣ ታዲያ አስለቃሹ ያ አደራ ያለው ድንገቴ ሰው ሞተና እንዲህ ብሎ ገጠመ፡-

ስሞት አልቅስልኝ ብለኸኝ የነበር ፣
አደግኸው ምነው ዋዛውን ቁም ነገር ።

ጌታ እግዚአብሔር ሆይ የሞቱትን አሳርፍልን ፣ ያሉትን አጽናልን ። የሰውን ዋጋ ከሚያውቅ ዘመን ላይ አድርሰን !

ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ