በዘንድሮ ዘመን ሰዉ ምን ተነክቷል ፣
ጀግና ሞተ ሲሉት መደንገጥን ትቷል ።
ፍርሃት የሥነ ልቡና መቃወስ ሲሆን ምንም ነገር አለመፍራትም ሌላኛው ሕመም ነው ። ተገቢ ፍርሃቶች አሉ ። ተገቢ ፍርሃቶችን መፍራት የጤንነት ምልክት ነው ፤ መፈራት የሚገባውን ነገር መፍራት መንፈሳዊነት ነው ። ዕረፍት የሚሰጥ ፍርሃት አለ ፣ እርሱም እግዚአብሔርን መፍራት ነው ። ከእውቀት በፊት የሚማሩት እውቀት አለ ፣ እርሱም ፈሪሀ እግዚአብሔር ነው ። እግዚአብሔርን መፍራት የሌለበት ማንኛውም እውቀት ለምድር መከራ አምጪ ነው ። በአገራችን ያልተማረው የጠበቀውን አገር የተማረው ያፈረሰው ፈሪሀ እግዚአብሔር ስለሌለ ነው ። አገርን ታህል መሰረጊያና መቀበሪያ እናፍርስ አናፍርስ እያለ የሚጫወቱት ተማርን የሚሉ ሰዎች ናቸው ። ሊያስፈራ ሊያስደነግጥ የሚችል አንድ ነገር አለ ። እርሱም የጀግና መሞት ነው ። ጀግና ማለት በፍቅር የተሠራ ፣ ለፍቅር የሚሠዋ ማለት ነው ። ጀግና ማለት ፍርሃትን ያሸነፈ ፣ እግዚአብሔርን በመፍራት ግፍን የተጸየፈ ነው ። ጀግና ለእውቀት ያደላ ፣ በልኩ የሚጣላ ነው ። ጀግና አገሬ ለእኔ ትኑርልኝ ሳይሆን ለአገሬ ልኑር የሚል ነው ።
ጀግንነት በተሰማሩበት መስክ ስለ ሌሎች መኖር ነው ። ጀግንነት ራስ ወዳድነትን አጥፍቶ ፣ እኔ ብቻ ይድላኝን ንቆ ፣ ለእውነትና ለፍቅር በመቆም የሚገኝ ነው ። ጀግና የሞት ስሙ እንኳ ሞተ ሳይሆን ተሠዋ የሚል ነው ። ጀግና ስሙን ፣ ሥራውን ፣ ፍቅሩን ፣ አርአያነቱን ፣ እንዲሁም ፍቅሩን ትቶ የሚሄድ ነው ። ጀግና ያለፈበት መንገድ ዱካው ያስታውቃል ። ተወለደ ሞተ የሚልን የሕይወት ጉዞ የተጸየፈ በልደቱና በሞቱ መካከል የሚሮጥ ጀግና ይባላል ። ጀግንነት በጦር ሜዳ ብቻ የሚገኝ ትልቅነት ሳይሆን ሕይወትም ጦር ሜዳ ናትና ራስን መግዛትም ትልቅ ጀግንነት ነው ። ብቻ ጀግና ሁልጊዜ በእውቀትና በፍቅር የሚያድግ ፣ የሕይወት ፍልስፍናው የሚጣፍጥ ነው ። ሰው ጣዕመ ዓለምን በሦስት ነገር ይንቃል ። የመጀመሪያው በመንፈሳዊነት ፣ ሁለተኛው በፍልስፍና ፣ ሦስተኛ በጀግንነት ነው ። ስንቱ ጎበዝ አጠገቡ ሲወድቅ አይቷልና ጀግና ለንብረት ስሱ አይደለም ። በዓለም ላይ ትልቅ ደካማነት እገሌ ሞቶ እኔ ለዘለቄታው እኖራለሁ ብሎ ማሰብ ነው ።
የበላይን ጭካኔ ፣ የበታችን አልገዛም ባይነት የሚገሥጹ አባቶች ጀግና ናቸው ። የመጣው ሁሉ የማይስማማቸው ፣ የሰው ሞት እንቅልፍ የሚነሣቸው ፣ እያስተማሩ የሚገሥጹ ፣ ዓለምን እየናቁ ዓለምን ናቁ የሚሉ እነርሱ ጀግኖች ናቸው ። ያጠፋን ለመገሠጽ ፣ የሳተን ለመመለስ ፣ የተጣላን ለማስታረቅ ጥብዐት/ድፍረት ይፈልጋል ። ቆርጦ ያልወጣ ማስተማር ፣ ማስማማት ፣ ማስታረቅ አይችልም ። የሁሉን ፍቅር የሚፈልግ የሁሉንም ጥላቻ ያተርፋል ። የሚያከብሩት ፣ የሚያፍሩት ፣ ለእውነት የወገነ ፣ ተዉ ልክ አይደላችሁም የሚል አባት ሲሞት መደንገጥ ይገባል ። እግዚአብሔር አገርን ያለ መካሪ እንዳያስቀር መማጸንም ያስፈልጋል ። ደግ ሰው ሞቱ ዕረፍቱ ሲሆን ለቀሪው ግን ጉዳቱ ነው ። በዚህ ዘመን አባት ሲሞት ፣ ሽማግሌ ሲታጣ ፣ ሊቅ ዐረፍተ ዘመን ሲገታው የሚደነግጥ ጠፍቷል ። ይህ የመነካት ወይም የመታመም ምልክት ነው ። ታዋቂን እንጂ አዋቂን የሚቀብር ሰው እንኳ እየጠፋ ነው ።
በዘንድሮ ዘመን ሰዉ ምን ተነክቷል ፣
ጀግና ሞተ ሲሉት መደንገጥን ትቷል ።
ክርስቲያን ጀግና ነው ። ጀግና የሚገድል ሳይሆን ለመሞት የማይሳሳ ነው ። ጨካኝ ለመግደል ደፋር ለመሞት ግን ስሱ ነው ። በሚሊየን የሚቆጠር ሰው የገደሉ እነርሱ ግን ሞትን ፈርተው ሲርበተበቱ ፣ በየጢሻው ሲደበቁ ታይቷል ። ክርስቲያን የሆነ ፣ በክርስቶስ ያመነ ለመግደል የሚፈራ ለመሞት ግን የሚደፍር ነው ። በእኛው ዘመን ሰማዕትነት በደጅ ቀርቦአል ። አካል ነንና አካሎቻችን ሲቆረጡ ይሰማናል ። ክርስቲያን መሆን ለመገደል ብቸኛ ምክንያት እየሆነ ከመጣ ቆይቷል ። የአንድን ሐዋርያ ደም ያላፈሰሰች አገር ዛሬ ክርስቲያኖች ሲገደሉባት ያሳዝናል ። ክርስትና ሰው ሁኖ ፣ በሰው ልክ ለመኖር እንኳ የሚያስፈልግ ሃይማኖት ነው ። ክርስትና የሚፈጥረው ማኅበራዊ ትስስር ፣ የሚያስገኘው ሥልጣኔ የዓለም ጉዞ የመሰከረው ነው ። በኢትዮጵያ የሚጎበኘው በአብዛኛው የቤተ ክርስቲያን አሻራ የሆነው ሥልጣኔ ፣ እንዲሁም የተቀደሱት አብያተ ክርስቲያናት ናቸው ። ቤተ ክርስቲያናችን እየተጠላች እንኳ እንጀራ ናት ። በየስፍራው የሚሞተው ክርስቲያን ወገናችን ሞቱ ሊያስደነግጠን ይገባል ። ካልደነገጥን ሕመም ላይ ነን ማለት ነው ። “ዳር ሲነካ መሐል ዳር ይሆናል” እንዲሉ በሁሉም ደጅ ላይ መቅረቡ የማይቀር ነው ። የምእመናን ሞት የሚያስደነግጣቸው አባቶች ያስፈልጉናል ። ልጁ እየሞተ የሚተኛ አባት የለምና ። ተዉ ማለት ገዳይንም መታደግ ነው !
በዘንድሮ ዘመን ሰዉ ምን ተነክቷል ፣
ጀግና ሞተ ሲሉት መደንገጥን ትቷል ።
አቤቱ እኛ ልንኖርለት የከበደንን ክርስትና እየሞቱለት ያሉትን ወገኖች ከድካማቸው አሳርፋቸው ። ከሰማዕታቱም በረከት አሳድርብን !
ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም.