መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ፈተና ውስጥ

የትምህርቱ ርዕስ | የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ፈተና ውስጥ

በአገሪቱ ስም የምትጠራ ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት ። የሮሜ ቤተ ክርስቲያን ፣ የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ፣ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ተብሎ በመጽሐፍ እንደሚጠራው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተብላ ትጠራለች ። መጽሐፉ በኤፌሶን አንዲት ቤተ ክርስቲያንን እንደሚያውቀው በኢትዮጵያም አንዲት ቤተ ክርስቲያን እንዳለች እናምናለን ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚለው መጠሪያ የራሱ ፍቺና ታሪክ አለው ። ኦርቶዶክስ የሚለው ስያሜ በ325 ዓ.ም. በኒቂያ ጉባዔ ምሥጢረ ሥላሴን ለማጽናት የተገናኙት አባቶች የሰጡት የክርስቶስን ዘላለማዊ አምላክነት ያወጀ ስያሜ ነው ። ተዋሕዶ የሚለው መጠሪያም በ431 ዓ.ም. በኤፌሶን ጉባዔ የተሰየመ ሲሆን የምሥጢረ ሥጋዌን ትምህርት ያጸና ስያሜ ነው ። ቤተ ክርስቲያን የሚለው ስያሜ አንድነትን የሚገልጥ ፣ ምሥጢራትን የመፈጸም ተልእኮዋን የሚያስረዳ ነው ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ልዩ የሚያደርጋት መገለጫ አላት ። ይኸውም እንደ ሮም ፣ እንደ ግብጽ ከአረሚነት ወደ ክርስትና የመጣች ሳትሆን ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ሐዲስ የተሸጋገረች ቤተ ክርስቲያን ናት ። በብሉይ ኪዳን ዘመን መጻሕፍተ ኦሪት በኢትዮጵያ እንደ ነበሩ ፣ ሕዝቦችዋም አንዱን አምላክ ያመልኩ እንደ ነበር ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ምስክር ነው (የሐዋ. 8፡26-40)። ሁለተኛ ጠባይዋ የአንድን ሐዋርያዋ ደም ያላፈሰሰች ፣ ወንጌልን በብሩህ ገጽ ፣ በሰፊ እጅ የተቀበለች ቤተ ክርስቲያን ናት ። ሦስተኛው ጠባይዋ የአገሪቱን አንድነት ለዘመናት ጠብቃ የቆየች ናት ። አራተኛው አምልኮዋና ሥርዓትዋ ለእግዚአብሔር በልዩ የተዘጋጀ እንጂ ከዓለም በውሰት የመጣ ፣ ወይም ዳንኪራን ወደ መዝሙር የለወጠ አይደለም ።

ይህን መልእክት ስንጽፍ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ አደጋ ውስጥ እንዳለች መረዳትና ቀድመን ማልቀስ ስለሚገባን ነው ። በግብጽ ያሉ ክርስቲያኖች በክርስቲያንነታቸው ብዙ መከራ ሲቀበሉ የኢትዮጵያ ነገሥታት ጣልቃ ይገቡ ፣ ዓባይን እንገድባለን ፣ ዘምተን የክርስቲያንን ሞት እናስቀራለን እያሉ ይፎክሩ ነበር ። እንደሚያደርጉት ስለሚያውቁ የግብጽ ሡልጣኖች የክርስቲያኖችን ሞት ያቆሙ ነበር ። ዐፄ ቴዎድሮስ ኢየሩሳሌም በኦቶማን ቱርክ በመያዝዋ ያዝኑና ነጻ ለማውጣት ይፈልጉ ነበር ። የአባቶቼን ርስት ኢየሩሳሌም ነጻ አወጣለሁ ብለው ለንግሥት ቪክቶሪያ ደብዳቤ እንደ ጻፉ ታሪክ ይነግረናል ። ኢትዮጵያን አንድ ካደረጉ በኋላ ቀጣይ ራእያቸው ኢየሩሳሌምን ነጻ ማውጣት ነበር ። እንዲህ ተብሎም ተገጥሞላቸው ነበር፡-

ታጠቅ ብሎ ፈረስ ፣ ካሣ ብሎ ስም ፣
ዓርብ ዓርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም ፤

የጥንቱ ኢትዮጵያውያን ነገሥታትና አባቶች ለግብጽ ክርስቲያኖች መጠቃት ሲያዝኑና እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን በአገሩ የሃይማኖት ነጻነት የለህም ተብሎ ሲገደል የሚቆጭ መጥፋቱ በጣም ያሳዝናል ። ኢየሩሳሌም ድረስ ሄደው ቅዱሳን መካናትን ነጻ ለማውጣት ያስቡ የነበሩ አባቶች በነበሩባት አገር ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል የደነገጠ አለመገኘቱ አደጋው ከፍ ያለ መሆኑ ያሳያል ።

በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው ግራኝ መሐመድ እንኳ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያን ባየ ጊዜ በመደነቅ ከማፍረስ ተቆጥቦአል ። ይህች ቤተ ክርስቲያን የሚጠላትን እንኳ የምታራራ ፣ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ናት ። የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ከማንም በላይ ያላወቋት የገዛ አባላትዋ ናቸው ። በመላው ዓለም የታወቀች የተከበረች ቤተ ክርስቲያን ናት ። ላለፉት አምስት መቶ ዓመታት የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል ብዙ አልተሰማም ። በእኛ ዘመን ግን እየተሰማ ነውና በጣም ማሰብና ችግሩ ምንድነው ማለት ያስፈልጋል ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መናጋት ለአገሪቱ ከፍተኛ አደጋ ይዞ ይመጣል ። በክርስትና ስም የሚንቀሳቀሱትና ይህችን ቤተ ክርስቲያን እንደ እርግጠኛ ጠላታቸው የሚያዩአትም ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ስትናጋ እነርሱም በጽንፈኞች የመጥፋት አደጋ ውስጥ መሆናቸውን አልተገነዘቡም ። ከሁሉ በላይ እንጀራዋን እየበሉ ያሉት የቤተ ክርስቲያን መጎዳት የነገ ረሀባቸው መሆኑን አላስተዋሉም ። ክብራቸው የሚቆየው ያከበረቻቸው ቤተ ክርስቲያን ስትከብር ብቻ ነው ። ራሳችንን ለመመርመር ፣ ዘመኑን ለመዋጀት እየባከነ ቢሆንም ጊዜው አሁን ነው ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ