መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የበደለኝነት ስሜት

የትምህርቱ ርዕስ | የበደለኝነት ስሜት

አንድ ሰው ጥፋት አጥፍቶ የሚሰማው የበደለኝነት ስሜት ሁለት ነገሮች እንዳሉት ማስረጃ ነው ። የመጀመሪያው ሕሊና ሲሆን ሁለተኛው መንፈሳዊነት ነው ። የበደለኝነት ስሜት ስህተታችንን ማመናችን ፣ ሌሎችን ይቅርታ ለመጠየቅ መወሰናችንን ያሳያል ። ስህተትን ማመን ለብዙ ሰው ቀላል አይደለም ። ኃጢአት በዓለም ላይ እንደ በዛ የምንገነዘበው ሁሉም ሰው እኔ ትክክል ነኝ ብሎ ማሰብ ሲጀምር ነው ። አዳምና ሔዋን ከበደላቸው በላይ በደላቸውን አለማመናቸው ለሞት እንዳበቃቸው እናውቃለን ። ስህተትን አለማመን ለትውልድ የቅጣት ውርስ የሚያመጣ ነው ። ስህተት በይቅርታ ካልተገደበ ለሺህ ዓመታት የመፍሰስ አቅም አለው ። ለዚህም 5500 ዘመን የወረደውን የአዳምን የኃጢአት ጅረት ማሰብ እንችላለን ። ስህተቱ ከተሠራ ከ500 ዓመት በኋላ ይቅርታ ተጠይቋል ። 1633 ጋሊሊዮ ባነሣው አሳብ ተፈርዶበት የነበረ ቢሆንም በ1992 ፍርዱ ተገቢ አለመሆኑን አምና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይቅርታ ጠይቃለች ። ስህተትን አለማመን በደል እንዳይቆም ያደርጋል ፣ ቂምን ያነግሣል ፣ በቀልን ያነሣሣል ፣ በትውልድ መካከል ጦርነትን ይወልዳል ፣ ለትችት ሲዳርግ ይኖራል ። ይቅርታ ብሎ መማጸን ግን የበደልን ፋይል ይዘጋል ። እግዚአብሔር በተነሣሕያን ወይም ንስሐ በሚገቡ ሰዎች ይደሰታል ።

ይህች ዓለምም ብዙ ክፉ ነገሮች ቢኖሩአትም ይቅርታ የተጠየቀበትን ነገር ድጋሚ አታነሣም ። በይቅርታ የተዘጋ ፋይልን የሚያነሡ ሰዎች ከዓለማዊ አስተሳሰብ እንኳ ያነሡ ናቸው ። እኩይ ፍልስጣ ተብሎ የሚጠራ የሰው በደልን እየተከታተለ የሚጽፍ ሰይጣን አለ ይባላል ። እኩይ ። ፍልስጣ እንኳ ሰውዬው ንስሐ ከገባ የጻፈውን በሙሉ ይሰርዛል ። ንስሐ የገባን ሰው መውቀስ ከእኩይ ፍልስጣ መባስ ነው ። በርግጥ ሰይጣን በዕድሜ የሚበልጣቸው በተንኮል የሚበልጡት ሰዎች እንዳሉ ብንናገር ማጋነን አይሆንም ። በመንፈሳዊ ዓለም ይቅርታ የሚገኘው በእግዚአብሔር ምሕረትና በቀራንዮ አደባባይ በፈሰሰው ክቡር ደም ነው ። ሰው ለራሱ የሚያደርገው ይቅርታ ተገቢ አይደለም ። ይቅርታን ሊሰጥ ሥልጣን ያለው እግዚአብሔር ነው ። የበደልነው ሰውም ይቅርታ የመስጠት ሥልጣን አለው ። ብዙ የተተወለት ነውና ተበዳዩ የሌላውን ጥቂት ለመተው ማሰብ አለበት ። ይቅርታ አለማድረግ የበደለንን ሰው ከቤታችን አባረን በልባችን ያለ ክፍያ መኖሪያ መስጠት ነው ።

የበደለኝነት ስሜት ቢኖር ኖሮ አሁን እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶች ሊበርዱ ፣ ዓለም የምሥራች ሊሰማ ይችላል ። አንዳንድ የተራዘሙ ጦርነቶች የዓለም መሪዎች ስህተታቸው እንዳይወጣ የሚፈበርኩት ሊሆን ይችላል ። የሰው ልጅ በስህተቱ ይቅርታ ከመጠየቅ የሚሊየኖችን ሕይወት ማጥፋት መርጧል ። ወይ አዳም ከማለት ወይ እኔ ማለት በጣም አስፈላጊ ነው ። ሰዎች መጸጸታቸው የጤናማነት መለኪያቸው ነው ። ፈጽሞ የማይጸጸቱ ፣ እነርሱ በድለው ይቅርታ እንዲጠየቁ የሚፈልጉ ሰዎች የአእምሮ መታወክ እንዳለባቸው የተረጋገጠ ነው ። ሰው የሆነ ሁሉ ስሜት አለውና ይሰማዋል ። እንስሳት እንኳ ሲያጠፉ ባለቤታቸውን ማየት ያፍራሉ ። ከውሻ ያነሰ ስሜት መያዝ ተገቢ አይደለምና መንቃት ያስፈልገናል ። የጸጸት ስሜት የሌላቸው ሰዎች እኔ ልሳሳት አልችም ብለው ራሳቸውን አምላክ ያደረጉ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች ብዙ ትምህርት ያመልጣቸዋል ። ሰው የሚማረው ከክፍል ይልቅ ወድቆ በመነሣት ነው ። የሕይወት ትምህርት አስተማሪው ራሱ እግዚአብሔር ሲሆን ትምህርቱም የማይጠፋ ነው ። የማይጸጸቱ ሰዎች የብዙ ሰዎችን ሕሊና ሰብረው የሚኖሩ ናቸው ።

የጸጸት ስሜት የሌላቸው ሰዎች በግፍ የሰከሩ ሰዎች ናቸው ። ሕሊና እንደ ማንኛውም የአካል ክፍል የሕመምና ብሎም የሞት ዘመን አለው ። ሕሊና ከግፍ ብዛት የተነሣ ይሞታል ፤ ሕሊና ሲሞት ጸጸት ይቆማል ። የማይጸጸቱ ሰዎችን የሚያባልጉ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ናቸው ። እነዚህ ከአስተዳደግ የተጎዱ ሰዎች የተለያዩ አቅሞችን በእጃቸው ስለሚጨብጡ በድለው ይቅርታ ይጠየቃሉ ። ሁሉም ሰው ጥፋተኛ ፣ እነርሱ ግን ትክክል መሆናቸውን ለራሳቸው ያሳምናሉ ። ተሳስታችኋል ያላቸውንም ሰው እስከ ሞት ድረስ ያሳድዳሉ ።

ከመሬት ተነሥቶ የበደለኝነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎችም ትክክለኛ አስተሳሰብ ላይ አይደሉምና ማሰብ አለባቸው ። ይህች ዓለም ከመጠን በላይ በሚኩራሩና ከመጠን በታች በሚሸማቀቁ ሰዎች የተሞላች ናት ። በብዙ ወቀሳ ያደጉና የገዛ የትዳር ጓዳቸው ሁልጊዜ የሚወቅሳቸው ሰዎች በጥፋተኝነት ስሜት ውስጥ ይኖራሉ ። ንስሐ ገብተው እንኳ ይቅር እንዳልተባሉ ይሰማቸዋል ። ራሳቸውን ያንን ጥፋት በማሰብ ለመቅጣት ይነሣሣሉ ። በዚህ ምክንያት ለጭንቀትና ለእምነት መዳከም ይዳረጋሉ ። ሰው ለሠራው ስህተት ራሱ መቀጣትና ሒሳብ ማወራረድ ቢችል ኖሮ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞት ባላስፈለገው ነበር ። ደግሞም ንስሐ ገብተው ይቅር አልተባልኩም ብለው የሚያስቡ ሰዎች በእግዚአብሔር መሐሪነት ላይ ጥርጣሬ አሳድረዋልና ያሁኑ ስህተት ይከፋል ። ለበደላቸው ወደ ምሕረቱ መጡ ፣ ምሕረቱን ካላመኑ በምን ይድናሉ ?

በበደለኝነት ስሜት ውስጥ የምትኖረው አንተ ወገኔ ከማንም የተሻለ በጎነት አንተ ውስጥ አለ ። ባልሠራኸው ስህተት ራስህን አታሰቃይ ። ትልቁ ችግርህ በሠራኸው በጎ ሥራም የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማሃል ። ሰላምታ ሰጥተህ ቀዝቀዝ ያለ ሰላምታ ነው ወይ የሰጠሁት ? ብለህ ራስህን ትቀጣለህ ። ለብቻህ ምግብ አቅርበህ መብላት ራሱ እንደ ጥፋት ሆኖ ይሰማሃል ፣ ለራስህ ምንም ነገር ለማድረግ የሰዎች ፈቃድ እንደሚያስፈልገው ታስባለህ ። ብዙ ውርጅብኝ ስታስተናግድ ስለኖርህ ፣ አንተን ለመቆጣጠር የሚፈልጉ ሰዎች ስለገጠሙህ ፣ የሚያበረታታ ወዳጅ ስላላገኘህ ፣ ከረጅም መጎዳት በኋላ ሽቁጥቁጥና ፈሪ ሰው ሆነህ ተሠርተሃል ። ዛሬ ግን ያንተ ቀን ነው ! ከዚህ ስሜት ውጣ ። ከዚህ ውስጥ ስትወጣ ባንተ ፍርሃት ያነገሥካቸውን ሰዎች ከዙፋናቸው ታወርዳለህ ፣ ልካቸውን እንዲያውቁና ትሑት እንዲሆኑ ታደርጋለህ ።

አምላከ ቅዱሳን ሁላችንን ያግዘን !

ሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ