መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ራስን ማዳመጥ

የትምህርቱ ርዕስ | ራስን ማዳመጥ

መጽሐፍ፡- “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ይላል ። ባልንጀራህን ውደድ ብቻ ቢል ኖሮ በምን መጠን ብሎ ይጠየቅ ነበር ። እንደ ራስህ ውደድ በመባሉ ግን ልኩ ታውቋል ። ሰዎች ራሳቸውን ይወዳሉ ብለን ስናስብ ተገቢ ባልሆነው ራስ ወዳድነት ነው ። ራስን መውደድና ራስ ወዳድነት የተለያየ ነው ። ራስን መውደድ መቅደሰ ሥላሴ ነኝ ብሎ ራስን ከሥጋዊና ከመንፈሳዊ ጉዳት መጠበቅ ነው ። ከሁሉ በላይ የነጻ ሕሊና ባለቤት ለመሆን መጣር ነው ። ራስ ወዳድነት ግን ጥቅመኛነት ፣ ለገንዘብ መስገድ ፣ የራስን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ ሰዎችን መቅረብ ፣ ተጠቅሞ ሰዎችን መጣል ፣ ምን አገኛለሁ እንጂ ምን እሰጣለሁ የሚልን ልብ መራቆት ነው ። በዓለም ላይ ራስ ወዳዶች ብዙ ናቸው ፣ ራሳቸውን የሚወዱ ግን ጥቂቶች ናቸው ። ራሳቸውን የሚወዱ ሰዎች ለራሳቸው በቅድሚያ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር በእግዚአብሔር ማመን ነው ። ለሚወዱት ከክርስቶስ በላይ የሚሰጥ ነገር የለም ። የሰማይ ቤቱ ፈርሶ የምድር ክብርን የሚያስስ ሰው እርሱ ራሱን የሚወድ አይደለም ።

በቅጡ የሚበላ ራሱን የሚወድ ነው ፣ ሆዳም ግን ራስ ወዳድነት ያጠቃው ነው ። በቅጡ የሚለብስ ራሱን የሚወድ ነው ፣ ዕራቁታቸውን በሚሄዱት መካከል ንጉሥ መስሎ ለመታየት ፣ ድሆችን ለማሳቀቅ ወርቅ የሚለብስ ግን ራስ ወዳድነት የሚዋጋው ነው ። ደግሞም የድሀ ልጅ ወርቅ አይለምድም ተብሎ ይተረትበታል ። ራሱን የሚያዳምጥ ራሱን የሚወድ ነው ፣ ራሱን ብቻ የሚያዳምጥ ግን ራስ ወዳድነት ያጠቃው ነው ። ስሜቱን የሚፈትሽ ራሱን የሚወድ ነው ፣ ስሜታዊ ሁኖ ሌላውን የሚጎዳ ግን ራስ ወዳድነት የለከፈው ነው ። ሰው በተፈቀደው መጠን ራሱን የማይወድ ከሆነ ባልንጀራውንም መውደድ አይችልም ። በእግዚአብሔር ስናምን እግዚአብሔርን ተቀበልን ማለት ነው ፣ ቀጥሎ ራሳችንን እንቀበለዋለን ፣ በመጨረሻ ሰዎችን በክርስቶስ እንቀበላለን ። ባልንጀራን የመውደድ ውኃ ልኩ ራስን መውደድ ነው ። ባልንጀራውን ለማዳን የሚሞክር ፣ የራሱ ሕይወት ግን አደጋ ውስጥ የሆነ ፣ ባልንጀራውን ወተት እያጠጣ እርሱ ግን አልኮል መጠጥ የሚጠጣ ፣ የራሱን ቤት አፍርሶ የባልንጀራውን ትዳር ካላቀናሁ የሚል እውነተኛ አይደለም ። ሰው አስቀድሞ ራሱን መውደድ አለበት ። ራሱን በትክክል መውደድ የሚችል ባልንጀራውን ይወዳል ። የሞላ ነገር በግድ ይፈስሳል ። የእግዚአብሔር ፍቅር በውስጣችን ሲሞላ ወደ ሌሎች መፍሰስ ይጀምራል ።

ለራሱ አያውቅበትም ፣ ለራሱ አይሆንም መባል ለሚወዱን ትልቅ የኀዘን መግለጫ ነው ። ለምንወዳቸው ሰዎች ከምንሰጣቸው ስጦታ ይልቅ አሳብ የሆነባቸውን አቋማችንን ማስተካከል ትልቅ ገጸ በረከት ነው ። ለራሱ አያውቅበትም ማለት ለሰው ያውቅበታል ማለት ነው ። ለራሱ የማያውቅበት ሰው ቢሰጥም ተቀባዩ አይደሰትበትም ። ቢረዳም ተረጂው እፎይ አይልበትም ። ከልክሎ ማሳቀቅ ብቻ ሳይሆን ሰጥቶ ማሳቀቅም አለ ። ለራሱ የማያውቅበት ሰው እየሰጠ ይበድላል ማለት ነው ። ከምንም በላይ ሰዎች እኛን ማግኘት ይፈልጋሉ ፣ እኛ የሌለንበትን ነገር ስንሰጣቸው የዘረፉን ያህል ይሰማቸውና ይሸማቀቃሉ ። ሰዎች ስለ ሕይወታችንና ስለ ምርጫችን ጥያቄ እንዳያነሱ በስጦታችን አፍ ማዘጋት ተገቢ አይደለም ። ምንም ይሁን ደግነቱ ይበቃኛል መባልን መፈለግ ራስን ማዳመጥ አለመፈለግ ነው ።

ባለሙያዎች ፣ ዘመናዊ መመርመሪያዎች ከሚነግሩን በላይ ራሳችንን በማዳመጥ ምን ላይ እንዳለን ማወቅ እንችላለን ። እግዚአብሔር ጨርሶ የማይታወቅና ከእኛ ያመለጠ ተፈጥሮ አልሰጠንም ። ራስን በማዳመጥ ውስጥ ብዙ በረከቶችን እናገኛለን ። እየከነፍን ከሆነ እንድንራመድ ፣ እያግበሰበስን ከሆነ እንድንመርጥ ፣ እየተተራመስን ከሆነ እንድናጣራ ፣ እየተደባለቅን ከሆነ ለየት እንድንል ይረዳናል ። ራስን ማዳመጥን ባለመፈለግ ሰዎች ለዘመናት ሽሽት ውስጥ ናቸው ። ሰዎችን መቀበል የቻሉ ሰዎች ራሳቸውን ግን አልተቀበሉትም ። ራስን በማዳመጥ ውስጥ ትርፍና ኪሣራን መመዘን ይቻላል ። የቀረውን ዘመን ገንዘብ ለማድረግ ፣ የምንፈልገውን ከሚያስፈልገን ለመለየት በጣም ይረዳል ። ከራሳችን ጋር ለአንድ ሰዓት እንኳ ቆይታ አድርገን እናውቃለን ወይ ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። ራሳችን ጊዜ ስጠኝ ሲለን ለሃያ ለአርባ ዓመት እምቢ ብለነዋል ። በአገልግሎት ፣ ሰዎችን በመርዳት ፣ በማኅበራዊ ኑሮ እያሳበብን ራሳችንን እንሸሸዋለን ። ራሳችንን ብናዳምጥ ግን ጉልበታም እየሆንን ፣ አላስፈላጊ ሸክሞችን እያወረድን ፣ ለነፍሳችን የሚጠቅመንን እየመረጥን እንመጣለን ።

ራሱን ማዳመጥ የማይፈልግ ሰው በብዙ ነገሮች ቢዚ በመሆን ራሱን ያጠላልፈዋል ። ራሱን ሊገናኝ ሲሞክር በመጠጥ ይሸሸዋል ። ስለ ሰዎች ማውራት ፣ ከፍ ያለ የተቃውሞ ሰው አድርጎ ራስን መሳል ይህ ሁሉ ራስን ከመሸሽ ሊመጣ ይችላል ። ሰዎች ራሳቸውን የሚሸሹት ወንጀል ስለ ሠሩ ሳይሆን ራሳቸውን ስለማያውቁት ብቻቸውን ሲያገኙት የሚያፍሩ ስለሚመስላቸው ነው ። በእውነት ስለ ራሳችን ካለን እውቀት ስለ ጎረቤታችን ያለን እውቀት ይበዛል ። ግርግር ፣ ድግስ ፣ የሙዚቃ ዝግጅት ፣ የተቃውሞ ሰልፎችን መውደድ ራስን ከመሸሽ ሊመነጭ ይችላል ። በየቀኑ ከራሳችን ጋር ማሳለፍ ካልቻልን ደስተኛ መሆን አንችልም ። ራስን ማዳመጥ የሚፈልጉትን ማወቅ ነው ። ሺህ ቤቶች ፣ መቶ መኪናዎች የሚፈልግ ሰው የሚፈልገውን አያውቅም ። ስለዚህ በሚያገኘው ነገር በልቡ ደስታ ፣ በአፉ ምስጋና የለውም ። ብዙ ነጭናጫ ሰዎች ፣ ትዳራቸው ጣዕም ያጣባቸው የሚፈልጉትን ስለማያውቁ ነው ። ካልታወከ በቀር የሚያውክ የለም ፣ ሰላም ያለው ሰላም ይሰጣል ። እነዚህን ሰዎች ራሳቸውን ማዳመጥ እንዲችሉ መርዳት አለብን ። ሰው ለንስሐ የሚበቃው ራሱን ማዳመጥ ሲችል ነው ። ንስሐ ደግሞ አሮጌውን ኑሮ ጥሎ አዲስ ሕይወት የሚሰጥ ነው ።

ራስን ለማዳመጥ በየዕለቱ የጽሞና ጊዜ ማድረግ ፣ የእግር መንገድ መጓዝ ፣ ቀለል ያሉ ሥራዎችን መከወን ፣ ስፖርት መሥራት ፣ በዜማ መሣሪያዎች ብቻ የተቀነባበሩ ዜማዎችን/ክላሲካሎችን መስማት ፣ ብቻችንን የምናሳልፍባቸው የተለያዩ መልካም ቦታዎችን መምረጥ ፣ ለራሳችን ተገቢ እንክብካቤ ማድረግ አስፈላጊ ነው ። አጠገባችን ያሉትም ከራሳቸው ጋር እንዲያሳልፉ ጊዜ መስጠት ተገቢ ነው ። ራስን ለማዳመጥ ትልቁ ነገር በጸሎት ፣ ቃሉን በማንበብ ፣ በማሰላሰል ፣ በመዘመር ማሳለፍ የበለጠው ነው ። ልብ አድርጉ ራሳችሁን ከጣላችሁት ማንም አያነሣችሁምና ራሳችን አዳምጡት ። ፈቃደ እግዚአብሔርን ለማወቅ እንኳ አንዱ መንገድ የልብን ሰላም ማዳመጥ ነው ። ራስን ማዳመጥ ፈቃደ እግዚአብሔርን ለማወቅም አስፈላጊ ነውና እንደ ቀላል መመልከት የለብንም ። ራስን መካድ እንጂ ራስን መጣል ክርስትና አይደለምና ለራሳችን ጊዜ ይኑረን !

ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ