መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ያልታወቀው የወንዶች ችግር » ያልታወቀው የወንዶች ችግር – 1

የትምህርቱ ርዕስ | ያልታወቀው የወንዶች ችግር – 1

የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ ፣
ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ ።

ወታደር የሚለው ቃል ወጥቶ አደር ማለት ነው ፣ አገሩን ቤተሰቡን ላለማስነካት ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ያቀረበ ነው ። የወንድ ልጅ መከራው እርሱ ዘንድ ብቻ የሚቀር ሳይሆን በዋናነት እናቱንም የሚገርፍ ነው ። ወንድ ልጅ በአካል በረሃውን ሲያቋርጥ እናቱም በአሳብ አብራ ታቋርጣለች ። በዚህ ሁሉ ውስጥ የወንዶችን ያልታወቀ ችግር መመርመር አልተቻለም ። ብዙ ወንዶች በከፍተኛ የአእምሮ ጭንቀት ውስጥ ያልፋሉ ። ያጠፉትን እንጂ ያለሙትን ማንም አያስብም ። በወንዶች የሚመራው ዓለም ወንዶችንም የሚበቀል መሆኑ ይገርማል ። ይህ ዘመን ደግሞ ወንድና ሴትን በብዙ መልክ እያራራቀ ገደል እየፈጠረ ያለ በመሆኑ የወንዶች ብቸኝነት እየጨመረ ይመጣል ። ወንዶች ለመጀመር ይጨነቃሉ ፣ የጀመሩት ባለመሳካቱም ለታላቅ ስብራት ይዳረጋሉ ።

በልደት የወንዶች ቍጥር ቢበልጥም በመኖር ግን የሴቶች ዕድሜ ይጨምራል ። የወንዶች ዕድሜ እያጠረ መምጣቱ አጠያያቂ አይደለም ። የሕዝብ ቍጥር ሲወሳም የወንዶች መጠን እያነሰ ነው ። ዘመናዊነት ያመጣው ፣ በእግዚአብሔር ዘንድም ተቀባይነት የሌለው ጾታን መቀየር የወንዶችን ቍጥር ሊቀንስ ይችላል ። በሕይወት ውስጥ ትልቁ ጸጋ የተሰጠንን በደስታ መቀበል ነው ። ራሳቸውን ያልተቀበሉ ወንዶች በሚያደርጉት የጾታ መቀየር ለከባድ ወጪና ጭንቀት ይዳረጋሉ ፣ የሚበዙትም ራሳቸውን በማጥፋት ያጠናቅቃሉ ። የወንድ ጾታ መቀነስ ብቻ ሳይሆን የወንድነት ጠባይም እየጠፋ እየመነመነ ይመስላል ። አንድን ወንድ ወንድ የሚያሰኘው ጠባያት እየመከኑ ነው ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ለዚህ ዓለም መተራመስ ወንዶች ትልቁን አስተዋጽኦ ቢያደርጉም ፣ ራሳቸውንም እየፈጁት ነው ። ብዙ ወንዶች እናታቸውን እንደሚወዱ በመላው ዓለም ፣ በየቀኑ ይናገራሉ ። እናቱን የሚወድ ወንድ እናቱ የምታዝንበትን ጦርነት መሥራት አልነበረበትም ።

በዓለማችን ላይ ያሉ እስር ቤቶች ውስጥ ከ93 እስከ 96 ከመቶ ወንዶችን ይዘዋል ። በአገራችንም ከመቶ እስረኛ አራት ሴቶችን ብቻ ስናገኝ የሚበዛው ወንድ ነው ። የእነዚህ ወንዶች ፍርድም ከወራት እስከ ዕድሜ ልክ ብሎም እስከ ሞት ነው ። ለአንድ ወታደር ድል አድራጊነት የሚረዳው ከወኔው ይልቅ መታዘዙ ነው ። ለወንድ ልጅም በሕይወት ውስጥ ባለድል ለመሆን ምክርን መስማትና መታዘዝ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው ። ጓደኛውን የገደለ ሞት እኔን አይነካኝም ብሎ በጓደኛው ወንበር ላይ የሚቀመጥ ወንድ ልጅ ነው ። ሞት ውጤት እንጂ ዕድል አይደለም ። ዕድሜና ስንቅ እንደ ያዥው ነው ይባላል ። ስንቅም ከቆጠቡት ለወር ካልቆጠቡት ለዕለት ነው ። ዕድሜም ጥንቃቄ ይፈልጋል ። ወደ ሞት መሄድ ጀግንነት ሳይሆን ጌታን መፈታተን ነው ። ምክር አጥቶ ከተጨነቀ ይልቅ ምክርን ገፍቶ ጭንቀት ውስጥ የወደቀ ብዙ ሰው አለ ። ገንዘብ የሚመጣው በሃያ ዓመት ልብ የሚመጣው በአርባ ዓመት ይባላል ። አንድን ነገር ለማወቅ ሃያ ዓመት ይፈጃል ማለት ነው ። ወጣት ወንድ ልጅ መገንዘብ የሚጀምረው ከአርባ ዓመቱ በኋላ ነው ። በጀብደኝነት ያስጨነቃት ሕይወቱን በጥበብ የሚመራት ከአርባ ዓመት በኋላ ነው ። ከአርባ ዓመት በኋላ ሰው መኖር የሚጀምርበት ዕድሜ ነው ። እውነተኛውን ማንነቱን ይቀበላል ። አንድን ነገር ቶሎ መገንዘብ ስለሚጀምር እውቀቱ ቶሎ ቶሎ ያድጋል ። ብቻ እናት ወንድ ልጅዋን ብቁ ለማድረግ ለሃያ ዓመት ትደክማለች ፣ አንዲት ሴት ግን ያንን ወንድ ልጅ በሃያ ደቂቃ ታሞኘዋለች ይባላል።

በአእምሮ ሕሙማን ጣቢያ ብዙ ወንዶች ይገኛሉ ። ራስን በማጥፋት ወንጀልም ወንዶች ሰፊውን ቦታ ይይዛሉ ። ወንዶች ያለመሳካት ውስጥ ሲገቡ አጠገባቸው ያለውን ሰው ማሰብ እስኪያቅታቸው ድረስ ስሜታዊ ውሳኔ ያደርጋሉ ። አስተዳደግና ባሕል ወንዶችን በብርቱ ጎድቷል ። የመጀመሪያው ወንድ ልጅ አይናገርም የሚል ከንቱ ባሕል ነው ። እንዲናገር የተፈጠረ ሰው መናገር የለበትም መባሉ ስህተት ነው ። “ካልተናገረ ብልሃቱ ፣ ካልታረደ ስባቱ አይታወቅም” ይባላል ። በመናገር ውስጥ መፍትሔ አለ ። ለማንም ችግሬን አልነግርም ማለት ጀግንነት አይደለም ፣ ድብቅነት አንድ የአእምሮ እክል ነው ። ችግራችንን የምንነግርበትን ቦታ መምረጥ ግን ይገባናል ። በምድር ላይ የንስሐ አባቶች ፣ መንፈሳዊ አማካሪዎች እንዲሰሙን ጌታ የሰጠን ትልቅ ስጦታዎቻችን ናቸው ። ሁለተኛው ችግር ወንድ ልጅ አያለቅስም የሚለው አባባል ነው ። ከቃላት በላይ የሆነ ስብራትን የምንገልጠው በማልቀስ ነው ። ማልቀስ መፈወስ ነው ። አባቶቻችን ከትልቅ መንፈሳዊ ማዕረግ ላይ ሲደርሱ ያለቅሳሉ ። የሰውን ኃጢአት የክርስቶስን ፍቅር በማሰብ ያለቅሳሉ ። ማልቀስ ጉዳት ሳይሆን ጉዳትን ማስተንፈሻ ነው ። ለማልቀስ ማፈር አይገባም ። የተጨነቀን ሰው እንዲያለቅስ ማገዝ ትልቅ መፍትሔ ነው ።

ሦስተኛው ከአባቶች ጋር ያለው ርቀት የወንዶች ችግር ነው ። ወንድ ልጅ ብልሃትን ከእናቱ ቢማርም ፣ ጀግንነትን ግን መማር የሚፈልገው ከአባቱ ነው ። አባቱ እጁን ይዞ የሕይወትን መንገድ ሊያስተምረው ይገባል ። ብዙ ስህተት ውስጥ የሚወድቁት የእናት ናፍቆት ያለባቸው ልጆች ሳይሆኑ የአባት ናፍቆት ያለባቸው ልጆች ናቸው ። በቤተሰብ ውስጥ ሴት ልጅ ወደ አባትዋ ፣ ወንድ ልጅ ወደ እናቱ የሚለው ድልድል ትክክል አይደለም ። አባቱን የሚጠላ ልጅ እንኳ የወደፊት ትዳሩን የሚመራው እንደ አባቱ ነው ። ወንድ ልጆች አባታቸውን ማግኘትና የሕይወትን ምሥጢር መማር አለባቸው ። አራተኛው የመንግሥታት ማሳደድ የወንዶች ችግር ነው ። በምድር ላይ የሚዘጋጀው የጦር ኃይል ፣ የስለላ ተቋም በአብዛኛው ወንዶችን ታሳቢ ያደረገ ነው ። ወንዶች የፖለቲካ ተጽእኖዎችን በመሸሽ አገራቸውን ጥለው ይወጣሉ ። በየበረሃውና በየባሕሩ ሞትን ፊት ለፊት ይጋፈጣሉ ።

ደርግ እንደመጣ ብዙ ወጣቶች በየመንገዱ መገደል ጀመሩ ። ድንበር ላይ ያሉ ወጣቶችም ወደ ስደት ወጡ ። ከዚያም ብሔራዊ ውትድርና በየቤቱ ወንድ ልጅን እየለቀመ መውሰድ ጀመረ ። ልጄ ቁመቱ አደገብኝ ምን ልሁን እያሉ ወላጆች መጨነቅ ጀመሩ ። ወንድ ልጅን በታላቅ ፍርሃትና ስስት ማሳደግ ስለ ተጀመረ ከዚያን ጊዜ አንሥቶ ወንድ ልጆች አቅመ ቢስ ሆኑ ። ይልቁንም የዜጎቻቸውን ልበ ሙሉነት መመኘት የሚገባቸው ገዥዎች የሚያሸማቅቁ ሆነው ስለ ተገኙ ከንጉሡ ዘመን በኋላ ወጣቶች በፍርሃት ተጎዱ ። አሁን ደግሞ ራሳቸውን ለመደበቅ በሰው አገር ባሕልና ሱስ ውስጥ ተደበቁ ። በሁሉም የጥፋት መንገዶች ውስጥ ወንዶች አሉ ። በመራራት የሚያክማቸው ሳይሆን በጭካኔ የሚፈርድባቸው እጅግ ብዙ ነው ። ወንዶችን የከሰረች ዓለም ነገዋ ያስፈራል ። ለወንዶች የሚራሩ እናቶችም ይህን ታሪክ ለመለወጥ መጸለይና ለሥራ መነሣሣት ያስፈልጋቸዋል ።

ይቀጥላል

ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ