አእምሮ የሌሎችን የአካል ክፍሎች በሽታ ሲገነዘብ የራሱን ግን መገንዘብ አይችልም ። በዚህ መስክ ያጠኑ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት አንድ ሰው አእምሮዬ ጤነኛ ነው ሲል ምናልባት የታመመ ሊሆን ይችላል ፣ ታምሜአለሁ ካለ ደግሞ ደኅና ሊሆን ይችላል ይላሉ ። ብዙ ወንዶች በአእምሮ መታወክ ውስጥ ያልፋሉ ። በሚወስዱት ሱስ ስለምንገምታቸው መራራት ያቅተናል ። መፍትሔ ብለው ያገኙት ያንን በመሆኑ ሱሰኛ ሆነዋል ። መፍትሔውን ግን ቀድመን ስላልነገርናቸው ለማስተማር ስንኩላን ፣ ለመፍረድ ግን ትጉሃን ሆነናል ። ደግሞም የምናመልከው ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአትን የሚጠላ ፣ ኃጢአተኞችን ግን የሚወድ መሆኑን ዘንግተናል ። ይህ ጌታ በሚጠሉት የተከሰሰው “የሁሉ ወዳጅ ነው” ተብሎ መሆኑን እንዘነጋለን ።
ወንዶች እውነትን ከመጋፈጥ ይልቅ መደበቅን ይወዳሉ ። ችግራቸውን አምቀው መያዛቸውን የወንድነት መለኪያና የጉብዝና ማሳያ ያደርጉታል ። ከማይናገሩ ሰዎች ይልቅ ውስጣቸውን በንግግር የሚገልጡ ሰዎች ዕድሜአቸው ሳብ ያለ ነው ። የሰው ልጅ የጨጓራው የሳንባው ሕመም ለራሱ ሲሰማው የአእምሮ ሕመሙ ግን የሚሰማው ለሌሎች ነው ። አንድ ሰው በአእምሮ መታወክ ውስጥ እንዳለ ከባለቤቱ ይልቅ አጠገቡ ያሉት ይረዱታል ። መሰልቸት ፣ ብቻ መሆንን መፈለግ ፣ መኖርን መጥላት ፣ የጠባይ ለውጥ ሲታዩበት በንቃት ያንን ሰው መርዳት ይገባል ። አእምሮ ዋጋ ባልተሰጠው አገር ላይ መኖር ከባድ ነው ። አእምሮአችን ሊታመም የሚችለው በሥራ ላይ ስላለ ፣ ከሌሎቹ የአካል ክፍሎች ይልቅ ስለሚደክም ነው ። ሰው የኩላሊቱን ሕመም ተቀብሎ የአእምሮውን መታወክ መቀበል ካቃተው አስቸጋሪ ነው ። ይልቁንም የአእምሮ መታወክ የመሰደቢያ ርእስ መሆኑ በጣም ያሳዝናል ። አእምሮ የሌለው ሰው የሌላውን አእምሮ የመንካት ብቃቱ ከፍ ያለ ነው ። ጨዋና ባለጌ ቢጣሉ የሚያሸንፈው ባለጌው ነው ። በአደባባይ የሚያስቀረው ምንም ብልግና የለምና ። ጨዋው ግን ለክብሩም ስለሚያስብ ዝም ይላል ። ለተናገረ የሚፈርደው ዓለም ባለጌን ጨዋ ይላል ። የሌላውን አእምሮና አካል የሚጎዱ ሰዎች ከፍተኛ በሆነ የአእምሮ ቀውስ ውስጥ ያሉ ናቸው ። ስድባቸውን ሐቀኝነት ፣ ንቀታቸውን ሁሉን እኩል ማየት ፣ ክሳቸውን ለጽድቅ መቆርቆር ብለው ይጠሩታል ።
ብዙ ወንዶች በአእምሮ መታወክ ውስጥ ያልፋሉ ። ወንዶች በተፈጥሮአቸው ብቸኛ ባይሆኑም እንደ ብቸኛ ራሳቸውን ይቆጥራሉ ። የታፈነ ሕመማቸውን ማንም አያውቅላቸውም ። በኑሮ ውስጥ የጠባይ ለውጥ ስናይ የአእምሮ መታወክ እንጂ ኩራትና ትዕቢት ላይሆን ይችላል ። ብዙ ሚስቶች በአእምሮ መታወክ ውስጥ ወይም ባልታከመ ሕመም ፣ በተነባበረ ጉዳት ውስጥ ስለሚኖሩ ያንን በጠባያቸው ስለሚገልጡት ማንም አይረዳላቸውም ። ባሎች ላይ ድንገተኛ የሆነ የጠባይ ለውጥ ሲመጣ የአእምሮ መታወክ መሆኑን መጠራጠር ይገባል ። ብዙ ወንዶች ይበልጥ በወጣትነት እስከ ጎልማሳነት ድንበር ያሉ ለበጎ ነገር ሁለት ጊዜ ያስባሉ ፣ ለክፉ ነገር አንድ ጊዜ ያስባሉ ። ወንዶች የዓለምን ችግር በሙሉ በገንዘብ የሚወጡት መስሎ ይሰማቸዋል ። ገንዘብ ግን ቁሳዊ ፍላጎትን ማሟያ እንጂ መንፈሳዊ ጥማትን ማርኪያ አይደለም ። እንደውም ገንዘብ በመጣ ቍጥር እርካታ እየሸሸ ይመጣል ። ገንዘብ ደስታን ከመስጠት የደስታ ተዋጊ ነውና ገንዘብ ስናገኝ ወዲያው በጎ አድራጎት መጀመር ፣ ወንጌልን ማስፋፋት ይገባናል ። ወንዶች ወደ ትዳር ሲገቡ ኪሳቸውን እንጂ የአእምሮ ብቃታቸውን አያዩም ። ምንም ነገር ከሚስታቸው ሲመጣ በኪሳቸው ስንት ገንዘብ እንዳለ ብቻ ያስባሉ ። ሚስታቸው ግን የምትፈልገው መደመጥ መሆኑን ይዘነጋሉ ። የወንዶች ተፈጥሮ ነገሮችን ከአጠቃላይ ሁኔታ መመልከት በመሆኑ ዝርዝር ነገርን ይሸሻሉ ።
ገንዘብን የሕይወት ዋስትና ያደረጉት ወንዶች ገንዘብ ሲያጡ በጣም መጨነቅ ፣ መኖርን መጥላት ይጀምራሉ ። በማጣት ፈሪ የሆኑት ወንዶች በማግኘትም ጊዜ አልሰጣችሁም ተብለው በትዳራቸውና በልጆቻቸው መጠላትን ያተርፋሉ ።
ይልቁንም እያንዳንዱ ግንኙነት ከገንዘብ ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው የሚመስልበት የእኛ ዘመን ወንዶችን ፈሪ እያደረጋቸው ነው ። የሚይዟት እጮኛ ፍላጎትዋ ያስደነግጣቸዋል ። ለሰው ሠራሽ ፀጉር ሁለት መቶ ሺህ ብር ስትፈልግ ፣ ውድ ቦታዎች ላይ መዝናናት ስትመርጥ ወንዶች ይፈራሉ ። የዛሬውን ማድረግ መቻል ሳይሆን የነገውን ኑሮ በማሰብ ወደ ኋላ ይላሉ ። ዘመናዊነቱ ለገዛ ቤታቸው ሁለቱም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ፣ ሴቶችም በኢኮኖሚ ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ ያበረታታልና አብሮ ስለማደግ ፣ አብሮ ዋጋ ስለ መክፈል ማሰብ ተገቢ ነው ። ወንድ ልጅ ሕይወቱን ለመሥዋዕትነት ያዘጋጀ ነው ። በሺህ ኪሎ ሜትሮች መኪና እየነዳ በአደጋ የሚወድቀው ፣ በሽፍቶች የሚታገተው ፣ ሁልጊዜ ሞትን ፊት ለፊት የሚያየው ወንድ ልጅ ነውና የእናቶች ጸሎት ፣ የእኅቶች ምክር ፣ የሚስቶች ፍቅር ያስፈልገዋል ። ለአገሩ ዘምቶ የሚሞተው በአጥንቱ አጥር ፣ በደሙ መጋረጃ አገሩን የሚያስከብረው በአብዛኛው ወንድ ልጅ ነው ። ለመሞት ጭካኔ ያለው ወንድ ልጅ ለመኖርና ለመለወጥ ፣ በክርስቶስ አምኖ ለመመላለስም ጭካኔ ያስፈልገዋል ።
ወንዶችን ከሴቶች የሚለያዩ የዓለም ሕጎችም መከለስ አለባቸው ። ወንድና ሴት አንዱ የአንዱ መገኛ ነውና መራራቅ የለባቸውም ። አዳም ለሔዋን አጥርዋ ነው ፣ ሔዋን ለአዳም ረዳቱ ናት ።
በወንዶች ለምን ጨከንን ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። አንድ መቶ ድሆችን እየረዳን ከሆነ አንድ ወንድ ልጅ የለበትም ። ለወንዶች መስጠት ሱስን ማበረታታት መስሎ ይሰማናል ። ብዙ ወንዶች ግን ባልታወቀ ረሀብ ውስጥ ናቸው ። የወንድ ልጅን ችግር የገዛ አባቱ እንኳ አያውቅለትም ። ያች እናት ደብቃ ታጎርሰዋለች ። የሰለጠኑት ወንጀል ውስጥ የገባ ሰው ሲገጥማቸው ወደዚህ ውስጥ ያስገባው ጉዳት ምንድነው ? በልጅነቱ ምን ገጥሞት ነበረ ? እያሉ ችግሩን ከሥሩ ለመንቀል ያጠናሉ ። የክርስቶስ ልብ አለን የተባልን እኛ ግን እንፈርዳለን ። በቀጣይ ዘመናት የሱስ ማገገሚያ ጣቢያዎች ፣ እጅግ የበዙ የመንፈሳዊ አማካሪ ቢሮዎች ያስፈልጉናል ። በእውነት ብዙ ወጣቶች ደኅና ለብሰው እየራባቸው እንደሆነ እኛ አገልጋዮች እናውቃለንና መናገርና ማልቀስ ለማይችሉት ወንዶችም የሚራራ ልብ ያስፈልገናል ።
ይቀጥላል
ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም.